“እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፡- እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” /ዮሐ. 5፡18/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት በመፈወሱ የተበሳጩትን አይሁድ፡- “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” አላቸው ፡፡ አይሁድ ጌታችን የሚናገረውን በጥልቀት ይሰማሉ ፤ የሚሰሙት ግን የክስ ምክንያት ፈልገው እንጂ ለማረፍና ለመዳን አልነበረም ፡፡ ሰንበትን የሻረ ሰው በብሉይ ኪዳን ለሞት የሚያደርስ ቅጣት ይገጥመዋል ፡፡ የምድሪቱን ሰንበት ባለማክበራቸው ለሰባ ዓመታት ከምድሪቱ ተነቅለው ምድሪቱ ዕረፍቷን አግኝታ ነበር /2ዜና. 36፡21/ ፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሐሰት ትንቢት የሚናገርም የሞት ፍርድ ይጠብቀው ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ነኝ የሚለውን ደግሞ ከዚህ በላይ በሆነ ቅጣት ቢቀጡት ይመኛሉ ፡፡ ጌታችን እግዚአብሔርነቱን መግለጡ ከተአምራቱና ሰንበትን ሻረ ከመባሉ በላይ በአይሁዳውያን ጥርስ ውስጥ ያስገባው ጉዳይ ነው ፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሔርነት አምሮት እግዚአብሔር ነኝ ያለ ሳይሆን በርግጥም እግዚአብሔር ነበረ፡፡
ማወቅ ብቻውን ለመዳን አያበቃም ፡፡ ማመንም ያስፈልጋል ፡፡ አይሁዳውያን ጌታችን ምን እንደሚናገር በደንብ ገብቷቸዋል ፡፡ የሚሠራው በእግዚአብሔር እርዳታ ሳይሆን በእግዚአብሔርነት ሥልጣኑ መሆኑን ሲናገር ውስጣቸው ተቆጣ ፡፡ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ ሊገድሉት ፈለጉ ይለናል ወንጌላዊው፡፡ ማንኛውም አይሁዳዊ የዕለት መፈክሩ እግዚአብሔር አባቴ ነው የሚል ነው ፡፡ ጌታችን ግን እግዚአብሔርን አባቴ ያለበት ድምፀት እኩያነትን የሚገልጥ ነበር ፡፡ እኛ እግዚአብሔር አባቴ ነው ብንል በፍቅር ተሰጥቶን እንጂ በክብር ተካክለን አይደለም ፡፡ እንኳን ከእግዚአብሔር ጋር ከምድራዊ አባታችን ጋርም እኩል አይደለንም ፡፡ በዘመን እንቀዳደማለን ፣ በክብር እንበላለጣለን ፡፡ ጌታችን ግን አባቱን አባቴ ሲል በዘመንና በክብር እኩል መሆኑን እየገለጠ ነው ፡፡
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልጅነትና የእኛ ልጅነት ልዩነት አለው ፡፡ የእርሱ ልጅነት የባሕርይ ሲሆን የእኛ ልጅነት ግን የጸጋ ነው ፡፡ የጌታችን ልጅነት ከአብ የተወለደበት ሲሆን የእኛ ግን ከሥላሴ የተወለድንበት ነው ፡፡ የጌታችን ልጅነት እኩያነት ሲሆን የእኛ ልጅነት ግን ተገዢነት ነው ፡፡ የጌታችን ልጅነት የሚሰገድለት ሲሆን የእኛ ልጅነት ግን የሚሰግድ ነው ፡፡ የጌታችን ልጅነት ከዘመን በፊት ሲሆን የእኛ ልጅነት ግን በታወቀ ዘመንና ቦታ በጥምቀት የምንቀበለው ነው ፡፡
ጌታችን ከሞት ከተነሣ በኋላ በመቃብሩ ስፍራ ትፈልገው ለነበረች ለመግደላዊት ማርያም ተገለጠ ፡፡ “ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፡- እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት” /ዮሐ. 20፡17/፡፡ ጌታችን ጠቅልሎ ወደ አባታችን አላለም ፡፡ ወደ አባቴ አለ ፡፡ የእርሱ ልጅነት ልዩ ነውና ፡፡ አብም በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር የምወደው ልጄ አለ እንጂ መጥምቁ ዮሐንስን ዳግመኛም ሐዋርያትን ጨምሮ ልጆቼ አላለም ፡፡ የባሕርይ ልጅነት ከጸጋ ልጅነት ይለያልና ፡፡
አይሁድ በነቢያት የጀመሩትን መግደል የነቢያትን ጌታ ወደ መግደል አሸጋገራቸው ፡፡ ኃጢአትና ግፍ በንስሐና በበጎ ተግባር ካልቆመ ራሱን እያሳደገ ይመጣል ፡፡ ጌታችን ብዙ ጊዜ ሊገድሉት ሲሉ ተሰውሯል ፡፡ ያለ ጊዜው ላለ መሞት ተጠንቅቋል ፡፡ እንኳን ኑሮው ሞቱም በአባቱ ፈቃድ እንዲሆን ፈልጓል ፡፡ በኑሮአችንም በሞታችንም እግዚአብሔርን ማክበር እንዳለብን ሊያስተምረን ይህን አደረገ ፡፡ በሕጻንነቱ ሄሮድስ ሊገድለው ሲል የተሰደደው ፣ ሰይጣን ራስህን ውርውር ሲለው እምቢ ያለው ፣ አይሁድ ሊገድሉት ሲሉ ሁለት ጊዜ የተሰወረው ጌታችን ፤ በጊዜው ግን በአህያና በውርንጫዋ ተቀምጦ በገሃድ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል ፡፡ በመጨረሻ የሞተበት ክስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል ተብሎ ነው ፡፡ ጌታችን በእውነቱ ተከስሶ ሞተ ፡፡ በርግጥም የእግዚአብሔር ልጅ ነው ፡፡ እኛም ስለ እውነት እንጂ ስለ ሐሰት እንዳንከሰስ ሊያስተምረን ይህን አደረገ ፡፡ አይሁድ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል አሁንም የተረዱት እግዚአብሔር ነኝ እንደሚል ነው ፡፡ እግዚአብሔርን አባቴ ሲልም የእኩያነት ድምፅ መሆኑን አስተውለዋል ፡፡ ይህ ሁሉ ማስተዋል ግን ለማመን አልረዳቸውም ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ለማዳን ዝቅ ብሎ ፣ የተገዢውን የአዳምን ሥጋ ለብሶ መጥቷል ፡፡ በምድር ላይም እንደ ሰው እየተመላለሰ እንደ አምላክነቱ ደግሞ ያስተምርና ይፈውስ ነበረ ፡፡ ልጁ ገደል ውስጥ ገብቶ ዝም የሚል ወላጅ ፣ በጥፋቱ ነው ብሎ ጥሎ የሚሄድ አባት የለም ፡፡ ጌታችንም ወደ ምድር የመጣው የገዛ መልካምነቱ አስገድዶት ነው ፡፡ ያለዚህ መልካምነት እርሱ እግዚአብሔር አልተባለም ፡፡ አንድ ንጉሥ ሕዝቡን የከበበ ሽፍታን ተዋግቶ ነጻ እንደሚያወጣ ፤ የከበበንን ኃጢአትና ሞት ሊበትን ጌታችን ሰው ሆነ ፡፡ ልጁ በአደጋ ውስጥ ሳለ መልእክተኛ ልኬ ላድን የሚል አባት የለም ፡፡ ራሱ ተገኝቶ ሊያድነው ብሎም ሊሞትለት ይከጅላል ፡፡ ጌታችንም በመልእክተኛ ሳይሆን ራሱ ሊያድነን መምጣቱ ፍቅሩ ግድ ብሎት ነው ፡፡
እርሱ ያለ ልክ ዝቅ ቢልም ያለ ልክ የከበረ ነው ፡፡ ትሕትናን ያስተምረን ዘንድ የዲያብሎስንም ጉራ ከንቱ ያደርግ ዘንድ እርሱ ዝቅ ብሎ መጣ ፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ጦርነቶች የተወለዱት በትዕቢት ነው ፡፡ እርሱ ግን ሰላም ያላትን ትሕትና ይዞ መጣ ፡፡ ሰዎች ዝቅ ከሚሉ ሞትን ይመርጣሉ ፡፡ ለመሬታዊ ሰው ፣ ከጭቃ ለተነሣው ሰው ዝቅ ማለት ከባድ ሲሆን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ትሑት ሆነ ፡፡ በዝቅታውም አሸነፈ ፡፡ በሞቱም አዳነ ፡፡ በትንሣኤውም ለሙታን ተስፋ ሰጠ ፡፡ በርግጥም እርሱ ማንም የማይቀማው እግዚአብሔርነት አለው ፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ ወደዚህ ዓለም መጥቷል ፡፡ ቃል ከልብ ሳይለይ እንደሚገለጥ እንዲሁም ቃል የተባለው ሎጎስ ከአብ ሳይለይ መጥቷል ፡፡ ክንድ ከአካሉ ሳይለይ ድል እንደሚያደርግ እንዲሁም የአብ ቀኝ የተባለው ክርስቶስ ከአባቱ ሳይለይ አሸንፏል ፡፡ አብም በቀኙ ፣ በክንዱ ስላዳነን አዳኝ ይባላል ፡፡ የወደቀን ለማንሣት ልብ ቢያስብ እንጂ አያነሣም ፡፡ እስትንፋስም ቢያደርስ እንጂ አያነሣም ፡፡ የሚያነሣው እጅ ነው ፡፡ የአብ እጁ የሆነው ክርስቶስ ሰው የሆነው ለዚህ ነው ፡፡ እጅ የሆነው ክርስቶስ ሲያነሣ ልቡ የሆነው አብ ፣ እስትንፋስ የሆነው መንፈስ ቅዱስ አልተለዩትም ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ማመን የክርስትናው ትልቅ ርእስ ነው ፡፡ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት ያላመነ ሰው መዳንን አያገኝም ፡፡ ምክንያቱም በፍጡር ደም ዓለም ሊድን አይችልምና ፡፡ የእርሱን የባሕርይ አምላክነት ከመዳን ጋር በጽኑ አያይዘን ማየት ያስፈልጋል ፡፡ እግዚአብሔርነቱ የተገለጠባቸው ነገሮችን ቀጥሎ እንመልከት ፡-
1- እግዚአብሔር ብቻ ሊያደርገው የሚችለውን እርሱ አድርጓል ፡፡ ይህም በድንግልና መወለድ ፣ በዝግ መቃብር ከሞት መነሣት አንዱ ነው ፡፡ ምነው አልዓዛር ከሞት ተነሥቶ የለም ወይ ቢሉ አልዓዛር በጌታችን ሥልጣን ሲነሣ ጌታችን ግን በራሱ ሥልጣን ተነሥቷል ፡፡
2- ለእግዚአብሔር የተሰጡትን ስሞች ወርሷል ፡፡ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ይድናል ተብሏል /ኢዩ. 2፡32/፡፡ በአዲስ ኪዳንም ይህ ቃል በጌታችን መፈጸሙን ለመግለጥ የጌታን ስም የሚጠራ ይድናል ተብሏል /የሐዋ. 2፡21/፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጣዖታት ልዩ መሆኑን የገለጠው ፊተኛውና ኋለኛው እኔ ነኝ በማለት ነው /ኢሳ. 44፡6/ ፡፡ በአዲስ ኪዳንም አልፋ ዖሜጋ እኔ ነኝ ብሏል /ራእ. 1፡17/ ፡፡
3- በሥልጣን አስተምሯል ፡፡ ነቢያት ሁሉ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል በማለት ተናግረዋል ፡፡ ጌታችን ግን እኔ ግን እላችኋለሁ በማለት አስተምሯል /ማቴ. 5፡21/ ፡፡ ለቀደሙት መመሪያዎችም ሦስት ዓይነት ቅርጽ ማለት አጽንኦት ፣ ማሻሻያና ለውጥ ሰጥቷል /ማቴ. 5፡21-48/ ፡፡ ይህ የእግዚአብሔርነቱ አስረጂ ነው ፡፡
4- ሰይጣን በተከራከረው ጊዜ ጌታ አምላክህን አትፈታተን በማለት ጌታና አምላክ መሆኑን መስክሯል /ማቴ. 4፡7/ ፡፡ ቶማስም ጌታዬ አምላኬ ባለው ጊዜ አመሰገነው እንጂ አልነቀፈውም /ዮሐ. 20፡28/ ፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ስግደትን ተቀብሏል /ማቴ14፡33/ ፡፡ ከሁሉ በላይ ሕጻን ሳለ ሰብአ ሰገል ያቀረቡለትን ስግደት ተቀብሏል ፡፡ ስግደቱ የአክብሮት ነው እንዳንል በዕድሜ ሕጻን ሁኖ ይታያል ፡፡ ደግሞም በበረት የተወለደ ምስኪን አርአያ ነበረው ፡፡ ስግደቱ ግን የአምልኮት ነው ፡፡ እጅ መንሻ ተቀብሏል ፡፡ ነገሥታት ሰግደውለታልና የነገሥታት ንጉሥ መሆኑም ታውቋል ፡፡
5- አማኑኤል የሚለው ስሙ እግዚአብሔርነቱን ይገልጣል ፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ምስሌነ – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ፡፡ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር በረድኤት በተአምራት ነበረ ፡፡ አሁን ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከእኛ ጋር ሆነ ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ባይሆን ኑሮ አማኑኤል ወይም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አይባልም ነበር ፡፡ ይልቁንም ቀዳሚ ልደቱን የተረከው ወንጌላዊው ዮሐንስ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሏል /ዮሐ. 1፡1/፡፡
በእግዚአብሔርነቱ እጅ መንሻ የሚቀርብለትን ጌታ ፣ እግዚአብሔር ነኝ በማለቱ በድንጋይ ሊወግሩት ተነሡ ፡፡ ዛሬም የእርሱን የባሕርይ አምላክነት የማይቀበሉትን መናፍቃን እንቃወማለን ፡፡
– በመለኮቱ ፍጡር ነው ያለውን አርዮስን የዛሬዎቹን የይሖዋ ምስክሮችን ትምህርታቸውን እንቃወማለን ፡፡
– ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ አንድ አካል ያደረገውን ሰባልዮስን የዛሬዎቹን ኦንሊ ጂሰስ የተባሉትን ትምህርታቸውን እንቃወማለን ፡፡
– አምላክነቱን የማይቀበሉትን የአንድ ገጽ አማኞችን አይሁድና እስላሞችንም ትምህርታቸውን እንቃወማለን ፡፡
– የሰውነቱን ትሕትና ባለመረዳት ሰውነቱን አጉልተው አምላክነቱን የሚዘነጉትን ፣ አምላክነቱን ብቻ በማየት የሰውነት ትሕትናውን የረሱትን ፣ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል ፣ አንድ ባሕርይ መሆኑን የማይቀበሉትን ትምህርታቸውን እንቃወማለን ፡፡
– አካል ተዋሕዶ ባሕርይ ሳይዋሐድ አይቀርምና አንድ አካል ሁለት ባሕርይ የሚሉትንም የኬልቄዶን ማኅበርተኞችን ተረፈ ልዮናውያንን እንቃወማለን ፡፡
– የባሕርይ ልጅነቱን ከእኛ የጸጋ ልጅነት አቀላቅለው እኩል ነን የሚሉትን የቀደሙትን አርዮሳውያንን የዛሬዎቹንም ተረፈ ፕሮቴስታንት ትምህርታቸውን እንቃወማለን ፡፡
ዛሬም እግዚአብሔር ነኝ ሲል ድንጋይ የሚያነሡትን ልቡና እንዲሰጥልን እንጸልያለን ፡፡