የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰው ክብር

“ከሰው ክብርን አልቀበልም ፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ እንደ ሌላችሁ አውቃችኋለሁ ። እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም ፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።” /ዮሐ. 5፡42-43/ ።
የሰው ክብርና የእግዚአብሔር ክብር አለ ። የሰው ክብር እንደ ደብዳቤ ሲሆን የእግዚአብሔር ክብር ደግሞ እንደ ማኅተም ነው ። ደብዳቤው ማኅተም ከሌለው እንደማይሠራ የሰው ክብርም የእግዚአብሔር ክብር ከሌለበት አይሠራም ። በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ያልተባለ የሁሉ ታናሽ ነው ። በእግዚአብሔር ዘንድ ባለጠጋ ያልተባለም እጅግ ድሃ ነው ። በሰው ክብርና በእግዚአብሔር ክብር መካከል እንደ ሰማይና ምድር መራራቅ አለ ።
የሰው ክብር አንዳንዶችን ያከብራል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ሁሉንም ያከብራል ። የሰው ክብር “እከክልኝ ልከክልህ” ነውና ምላሽ ካጣ የሰጠውን ክብር ይገፍፋል ። እግዚአብሔር ግን አክብሮ አያዋርድም ። የሰው ክብር በዕድሜ ትልቅ ፣ በሥራ ላቅ በል ይላል ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን ያልተፈጠሩትን ሳይቀር ያከብራል ። የሰው ክብር እንደ ማታ ጀንበር ነው ፣ ቶሎ ይመሻል ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን እንደ ማለዳ ፀሐይ ሙሉ ቀን ወደ መሆን ይቸኩላል ። የሰው ክብር እንደ ገደል ማሚቱ የራሴን ድምፅ ልስማ ይላል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን እስክንረዳው ድረስ ይጠብቃል ። የሰው ክብር “እገሌ ምን አለው ?” ይላል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን በሰውዬው ላይ ያለውን የመለኮት ዓላማ ያያል ። የሰው ክብር በዕድሜ የላቀውን ይቀበላል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን “ሕጻናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ይላል ። የሰው ክብር አዋቂዎችን ይፈልጋል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ሞኞችን ያስጠብባል ። የሰው ክብር ባለጠጎችን ያስሳል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የተራቆቱትን ያለብሳል ። የሰው ክብር ውበት አይቶ ሲያደንቅ ጠባሳ ካየ ይስቃል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን አሟልቶ ያነብባል ። የሰው ክብር ጀማሪዎችን ይንቃል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ፍጻሜውን ያይላቸዋል ። የሰው ክብር ባዶዎች ላይ ይስቃል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ሞልቶ ለእርካታ ያደርጋቸዋል ። የሰው ክብር ጥዋት እንደ ባንዲራ ሰቅሎ ፣ ሲመሽ ያወርዳል ፤ የእግዚአብሕር ክብር ግን ማታ የሌለው ቀን ሁኖ ይኖራል ። የሰው ክብር መልሶ ካላዋረደ እንቅልፍ የለውም ፣ አቤት የታወቁት ታነቁ ! አቤት ዝነኞች ዝምብ ተለቀቀባቸው ! ለአርባ ዓመት አገልግሎታቸው አርባ ርግብ የተለቀቀላቸው ወዲያው አርባ ተናካሽ ውሻ ተለቀቀባቸው ። የእግዚአብሔር ክብር ግን ከቅዱስነቱ የሚወጣ በመሆኑ አክብሮ አያዋርድም ። የሰውን ክብር ያዩ “አንቺ ዓለም አንቺ ዓለም የጀመረሽ እንጂ የጨረሰሽ የለም” አሉ ፤ የእግዚአብሔርን ክብር ያዩ ግን “ክብሩ ሰማያትን ከድኗል ፥ ምስጋናውም ምድርን ሞልቶአል” አሉ ።
የሰው ክብር ለአንገት ሐብል ሸልሞ ቀጥሎ ሐብሉን ሳይሆን አንገቱን ይቆርጣል ። የእግዚአብሔር ክብር ግን ሐብሉንም አንገቱንም ይጠብቃል ። የሰው ክብር የሰጠውን ኒሻን ይነጥቃል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ደካማውን ብርቱ ነህ ይላል ። የሰው ክብር ባለፈው የሰጠነው ክብር በስህተት ነው ይላል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ሰማይን ግብ አድርጎ ይጀምራል ። የሰው ክብር ባለማወቅ ላይ ተመሥርቶ ነው ፣ ሲያውቅ ሜዳሊያ መልሱ ይላል ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን በመጥራቱና በመስጠቱ አይጸጸትም ። የሰው ክብር አቡን ያለውን አቶ ይላል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ልጄ ብሎ ለሁልጊዜ ይጠራል ። የሰው ክብር ያለቀ ቀን ባከበረው መጠን ሳይሆን ከዚያ በላይ ያዋርዳል ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ከፍ እንጂ ዝቅ አይልም ። የሰው ክብር ሰውዬውን ከፍ አድርጎ በሰውዬው ለመጠቀም ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ጥቅም ሳይሆን ፍቅር ነው ። የሰው ክብር የቀጤማ ምርኩዝ ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የጸና ምሰሶ ነው ። የሰው ክብር ዞሮ ለማየት አንገት የለውም ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የአንድ ቀን ታማኝነትን እንኳ አይረሳም ። የሰው ክብር ጃንሆይ ባለ አፉ ሌባ ሲል አይሰቀቅም ፣ ነጠላ አንጥፎ በሰገደ ጉልበቱ ሲራገጥ አይደነግጥም ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን አይዋዥቅም ። የሰው ክብር ከንቱ ውዳሴ ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን መንግሥትን የሚሰጥ ነው ። የሰው ክብር ነፋስ የሚወስደው ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን በሕይወት መጽሐፍ የሚጽፍ ነው ። የሰው ክብር በሙታን መዝገብ “እገሌ እኮ ተበላሸ” ብሎ የሚጽፍ ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ከሕያዋን ቊጥር የማያጎድል ነው ። የሰው ክብር አስብቶ እንደ በሬ የሚያርድ ነው ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን የጠፋውን ልጅ የሚቀበል ነው ። የሰው ክብር ቅዱስ ቢል ቅዱስ እንዲሉት ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን ቅዱስ የሚያደርግ ነው ። የሰው ክብር እንደ አሺሽ እንደ መጠጥ የሚያሰክር ነው ፣ ሲነቁ ሕመምና ጥርጣሬ አለው ። የእግዚአብሔር ክብር ግን አእምሮን የሚያበራ ነው ። የሰው ክብር ትዕቢተኛ የሚያደርግ ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የድሆች ወዳጅ የሚያደርግ ነው ። የሰው ክብር “አንቱ አይቅለሉ” የሚል አንቱንም አይቅለሉንም የማይተው ነው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የሚጎድልና የሚሞላውን ሰው የማይታዘብ ነው ። የሰው ክብር ተረኛ ሰው አለው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን እንደ ጽዋ የማይዞር ነው ። የሰው ክብር “ግን” የሚል አፍራሽ ቃል አለው ፣ የእግዚአብሔር ክብር ግን የእንቧይ ካብ አይደለም ።
የሰው ክብር መልክን እንደሚያሳይ መስተዋት ነው ፣ መስተዋቱ ስንስቅ ይስቃል ፣ ስናለቅስ ያለቅሳል ፣ የሆንነውን እንጂ ሌላ አያሳይም ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን ከሁኔታ ፣ ከቦታና ከጊዜ ውጭ ሁኖ ያስተምራል ። የሰው ክብር እንደ ልጅ ጨረቃ ነው ፣ ገና የተወለደች ጨረቃን አምኖ በምሽት መንገድ የጀመረ ድንገት ይጨልምበታል ፣ በሰው ክብር ልቡ የነሆለለም ሁሉም ነገር ሲለወጥ ግራ ይጋባል ፤ የእግዚአብሔር ክብር ግን ላይጨልም ያበራል ። “ጨለማ የሚባል ነገር የለም ፣ ጨለማ የተባለው የብርሃን አለመኖር ነው” እንደሚባለው የሰውን ክብር የሚያስናፍቀው የእግዚአብሔርን ክብር አለማወቅ ነው ። ይልቁንም አባቶች ፡- “የማያስተውል ሕዝብ ሲያመሰግንህ ምን አጥፍቼ ነው ? በል” እንደሚሉት የሰውን ክብር በጥንቃቄ ማየት ይገባል ። የእግዚአብሔር ክብር ግን ለእግዚአብሔር ክብርን እስከ ሰጠን ድረስ ይኖራል ።  ጌታችን ይህንን የሰው ክብር አልቀበልም አለ። ዓለም ስታከብረው የፈነጠዘ ስታኮስሰው ማፈሩ አይቀርም ። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ከመንበሩ ከአራት ጊዜ በላይ የተሰደደ ፣ በመንበሩ ካገለገለበት በስደት ያገለገለበት ዘመን እንደሚበልጥ ታሪኩ ይናገራል ። አርዮሳውያንና ካህናት መሆን ያማራቸው ነገሥታት ባመጡበት መከራ ወዳጆቹ አዘኑ ። አትናቴዎስን ለማለዘብ “ዓለም ሁሉ ጠላህ አሉት” አትናቴዎስም ፡- “እኔም አስቀድሜ ዓለሙን ጠልቼዋለሁ” አለ ይባላል ። ዓለምን ቀድሞ ያልናቀ ፣ ዓለም ስትንቀው ይደነቃል ።
ሰው በርቀት ያለውን ሰው አያውቀውምና ጉድለቱን ያያል ። ስለዚህ ያከብረዋል ። ያ ሰው ጉድለት ስለሌለው ሳይሆን በርቀት ስለሆነና ማየት ስላልቻለ ነው ። የቀረበውን ሰው ጉድለት ግን ያያል ። ስለዚህ እንዴት ይህን ያደርጋል ይላል ። ሊተቸውና እኔ አውቀዋለሁ ለማለት ይጀምራል ። ከእርሱ እገሌ ይሻላል የሚል ውድድር ይጀምራል ። ነገር ግን እገሌ የሚሻል የመሰለው እገሌ ስላላቀረበው ነው ። ይህ ሰው ግን እንዲህ ያለውን ጉድለት ፈላጊ ሰው በማቅረቡ ብቻ የዋህና ትሑት ነው ። ኑሮውንም ለማሳየት ራሱን በሰው ልክ ያየ ነው ። ከጉድለቱ ይልቅ ማቅረቡ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ አለው ።  የሰው ክብር ይቆጫልና ጉድለትን ይፈልጋል ። እንደ ሕጻን ስጦታ ሰጥቶ ወዲያው አምጡ ይላል ።
“ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፡- የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው ። እርሱ ግን፦ አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ።” /ሉቃ. 11፡27-28/ ። ጌታችን ምስጋናዋን ለምን አልተቀበለም ? ይህች ሴት አመጣጧ በአደባባይ ባመሰግነው ባደባባይ ያመሰግነኛል ብላ ነው ። ጌታ ግን ብፁዕ የሚባለው በኑሮ እንጂ በአዋጅ አለመሆኑን ነገራት ። ጌታችን ሆሳዕና ብሎ ያመሰገነው ሕዝብ ይሰቀል ሲለው አልተደነቀም ። ልብሱን ያነጠፈለት ወገን ልብሱን ሲገፈው አልተገረመም ። ዮሐንስ ይህን ዘግቦልናል፡- “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።”  /ዮሐ. 2።24/።
ጃንሆይ ታስረው ወዲያው የስድብ ናዳ ሲወርድባቸው አንዲት አልቃሽ ሰው ሙቶ ተጠራች ። ደረት ስታስመታ ፡-
“ዓለም ዋሾ ዓለም ወላዋይ ፣
እጃንሆይ ግቢ አልነበርሽም ወይ ?” አለች ይባላል ። ትልልቅ የአድናቆት ፕሮግራሞች ሲዘጋጁልን በጣም መጸለይ ያስፈልጋል ። ሰዎች በቀና ያደርጉታል ፣ ወዲያው በተናገሩትና በጻፉት ነገር መፈተን ይጀምራል። ሰዎች መልአክ ሲያደርጉን “ሰው ነኝ” ማለት አለብን ። ቀኝ ኋላ ዙር ሲሉ ሰይጣን እንዳይሉን ።
 “ማወቅማ እናውቃለን ፣ ብንናገር እናልቃለን” የሚለውን ንግግር የወለደ የሰውን ክብር መፈለግ ነው ። “እውነት ብናገር ሰው ይቀየመኛል ፣ ሐሰት ብናገር እግዚአብሔር ያዝንብኛል ፤ ዝም ብል ይሻለኛል” ያሰኘም ይኸው የሰው ክብር ነው ። የሰው ክብር እንደ ጥዋት ጤዛ ረጋፊ ፣ እንደ ቀትር ጥላም ኃላፊ ፣ እንደ ሠርክ ጀምበል ጠፊ ነው ። ጌታችን ይህን የሰው ክብር አልቀበልም አለ ። የሚጎዳን ሰዎቹ ማመስገናቸው ሳይሆን እኛ በምስጋናው መመካታችን ነው ። አንድ የጨረታ ማስታወቂያ አለ ፡- “ድርጅቱ የተሻለ ከተገኘ በጨረታው አይገደድም።” ሰዎች ራሳቸውን እንደ አካል ማሰብ ትተው እንደ ድርጅት ሲያስቡ አመስግነው ለመራገም በጨረታው አይገደዱም ።  የተሻለ ፍለጋ ይሄዳሉ እንጂ የወደቀውን ለማንሣት አይጥሩም ። ሌላውን ወንድማቸውን እንደ አካል የሚቆጥሩ ግን የወንድሜ ክብሩ ክብሬ ፣ ስድቡ ስድቤ ነው ይላሉ ። ዛሬ ክርስቲያን ወንድማቸውን የሚያዋርዱ የሥጋ ወንድማቸውን ግን በአደባባይ አያዋርዱትም። ይህ የሚያሳየን ለብዙዎች መንፈሳዊ ወንድምነት ከሥጋ ወንድምነት ማነሱን ነው ። በዛሬው ዘመን ብዙ ክርስቲያኖችን ክርስቲያን ከማድረግ ፣ አረማውያንን ክርስቲያን ማድረግ እየቀለለ ይመስላል ። ማስተዋል ይስጠን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ