የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዘለሽ ወደ ልቅሶሽ

“እንግዲህ፡- እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ ? ምንስ ትሠራለህ ?” ቊ. 30
አልቃሽና ዘፋኝ አንድ ቤት ይኖሩ ነበር ። አልቃሽ ፡- “ፊታውራሪ ሙተው ምነው ባለቀስሁ” ትላለች ፣ ዘፋኝ ደግሞ፡- “ፊታውራሪ ልጃቸውን ድረው ምነው በዘፈንሁ” ይላል ። ሁለቱም ምኞታቸውን በጸሎት መልክ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያውጃሉ ። በዚህ ጊዜ ዘፋኝ አልቃሽን መከራት፡- “ሰው ከሚሞት ልጁን ቢድር ይሻላል ፣ ስለዚህ አንቺ ሙያሽን ለውጪና ዘፋኝ ሁኚ ፣ እየተቀባበልን እንዘፍናለን ፤ በዚህም ኑሮአችንን እናሸንፋለን” አላት ። እርስዋም በዚህ ተስማምታ ሥራ ጀመሩ ፤ ነገር ግን የድሮው አልለቅ ብሏት ትንሽ እንደ ዘፈነች ዜማው ወደ ልቅሶ ይሄድባታል ። ዘፋኙም ሥራው እየተበላሸበት ሆነና በንዴት፡- “ዘለሽ ወደ ልቅሶሽ ትገቢያለሽ” አላት ይባላል ። እነዚህም አንጋሾች ትንሽ አዚመው ዘለው ወደ ልቅሶአቸው ገቡ ። የእነርሱ ልቅሶ ምልክት ማየት ነው ። “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው” እንዲሉ ማንም ይሥራው የሚፈልጉት ምልክት ነው ።
ጌታን እናንግሥህ ያሉት ትላንት ምልክት አይተው ነው ። ሁለት ሰው በማይመክት አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አምስት ሺህ ሰው ሲጠግብ እናንግሥ አሉ ። አይተው እንዳላየ በመሆን ዛሬ ደግሞ ምልክት ፈለጉ ። እነዚህ ሰዎች አይተን እንድናምን ምን ምልክት ታደርጋለህ ? አሉት ። የጠየቁትን ጥያቄ ልብ ማለት ያስፈልጋል ። አይተው ለማመን ነው የፈለጉት። የአማኝ ወጉ ደግሞ አምኖ ማየት ነው ። ቅዱስ አውግስጢኖስ ፡- “ሳያዩ ያመኑ ሽልማታቸው ያመኑትን ማየት ነው” ያለው ለዚህ ነው ። ጌታችንም ለሐዋርያው ቶማስ፡- ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ብሎታል ። ዮሐ. 20 ፡ 29 ። የዓለም መፈክሯ “ማየት ማመን ነው” የሚል ሲሆን እግዚአብሔር ደግሞ “ማመን ማየት ነው” ይላል ። በዓለምና በእምነት መካከል ያለው ርቀት በጣም ሰፊ ነው ። ዓለም እንደ ማንነቷ ተጨባጭ ነገር ትፈልጋለች ፣ ቁሳዊ ነገር ላይ ትደገፋለች ። እምነት ደግሞ ውጤቱ ላይ ሳይሆን ሰጪው ላይ ይታመናል ።
የእግዚአብሔር ሰዎች የተባሉ ሁሉ ሳያዩ ያመኑ ሲሆኑ ያመኑትንም በማየት ዋጋቸውን ተቀብለዋል ። አብርሃም በሽምግልና ዘመኑ በሰባ አምስት ዓመት ዕድሜው የጠራውን እግዚአብሔር ሳያመነታ ተከተለው ። እግዚአብሔርን ተገልጦ ያየው ግን በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ከሃያ አራት ዓመት በኋላ ነው ። ሙሴ እግዚአብሔርን ያየው በደብረ ሲና ነው ። ይህም ከሰማንያ ዓመት በኋላ ነው ። ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ የመሰከረው በእምነት ነው ። ጌታ ግን ከስድስት ቀን በኋላ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ፣ ግርማ መንግሥቱን ገልጦ አሳየው ። ሳያዩ ማመን ደስታ አለው ። እምነት የሚባል ነገር ያስፈለገውም የማይታየውን ለማየት እንጂ የሚታየውን ለማየትማ ዓይን በቂ ነው ። እምነት የማይታየውን ማየትና ከሚታየው በተቃራኒ ያለውን ተስፋ ማድረግም ነው ። እነዚህ ሰዎች ግን አይተን እናምንብህ ዘንድ ምን ታደርጋለህ ? አሉት ። ይህ አለማመን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም መፈታተን ነው ።

እግዚአብሔር በማን የሚያዝን ይመስላችኋል ? ክንዱን አይተው እንዳላየ በሚኖሩ ሰዎች ያዝናል ። በእግዚአብሔር ተሻግረው እግዚአብሔር ማነው ? በሚሉ ያዝናል ። አገልጋዮችን ጸልዩልን ብለው ሲደርስላቸው የአገልጋዮች ስም እንኳ በሚጠፋቸው ያዝናል ። ቤተ ክርስቲያንን ማልቀሻ እንዳላደረጉ እንባቸው ሲታበስ በጓሮ ዙረው በሚሄዱ ያዝናል ። ቤታቸው ሲጸና መልሰው የእግዚአብሔርን ቤት በሚያፈርሱ ያዝናል ። ስለ ድሆች አስደናቂ ንግግር አድርገው መልሰው ድሀ ጨቋኝ በሚሆኑ ያዝናል ። ስለ አገር ፍቅር አስተምረው አገር በሚበዘብዙ ያዝናል ። ቅኝ ገዥዎችን አሸንፈው መልሰው ቅኝ ገዥ በሚሆኑ ያዝናል ። በሰዎች እዚህ ደርሰው በራሴ ነው የቆምሁት በሚሉ ያዝናል ። በልተው እንዳልበላ አፋቸውን ጠራርገው በሚቀመጡ ፣ ስጦ ቃሚ በሆኑ ፍየሎች ያዝናል ።
እነዚህ ሰዎች እስካሁን ይናገሩት የነበረው ንግግር የማስመሰል ነበር ። አሁን ግን አንተን አንፈልግህም ምልክትህን ነው ወደ ማለት ደረሱ ። ዋናው ጋ የደረሰ ሰው ምልክት አያስፈልገውም ። ምልክት መዳረሻ እንጂ መድረሻ አይደለም ። የሕይወት ግብ አማኑኤል ጋ ደርሰው ምልክት ፈለጉ ። ከመጀመሪያ ወደ መጨረሻ መሄድ ክብር ነው ፤ ከመጨረሻ ወደ መጀመሪያ መሄድ ግን ውርደት ነው ። ትልቁ ምልክት የእርሱ ድንግልናዊ ልደት ነው። ኢሳ. 7 ፡14 ።
በመቀጠልም እነዚህ ሰዎች ፡- “ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ አሉት ።” ዮሐ. 6 ፡31።
እነዚህ ሰዎች ይህን አሳብ ለምን አነሡ ? ማለት ጥሩ ነው ። ትላንት የበረከተ የዕለት እንጀራ በልተዋል ። አሁን ደግሞ የዘመናት እንጀራ መና ቢያዘንብልን ብለው በማሰብ ነው ። አርባ ዓመት ካሳረፈን በቂ ነው በሚል ስሌት መጥተዋል ። ስለዚህ ዳግማዊ ሙሴ ሁንልህ እያሉት ነው ። ሙሴን ዳግመኛም ክርስቶስን የሳሉበት ሥዕል ስህተት አለበት ። ሙሴን ከሆነው በላይ መና አውራጅ አደረጉት ። ክርስቶስን ከሆነው አሳንሰው አዩት ። ፍጡርን አምላክ ማድረግና አምላክን ፍጡር ማድረግ ሁለቱም መታረም አለበት ። ሌላውና ሦስተኛው ስህተት ሳይሠሩ መና እየበሉ መኖር ፈልገዋል። ሥራ በራሱ መና መሆኑን አላወቁም ። ሥራ የአእምሮ ምግብ ሲሆን ደመወዙ ደግሞ የሆድ ምግብ ነው ። ደመወዝ በወር ሲሆን የአእምሮ እርካታ ግን በየሰዓቱ ነው ። ሆድ ከመብላቱ በፊት አእምሮ ይጠግባል ። ስህተታቸውን በራሳቸው ልመናና ምኞት ውስጥ እየገለጡ ነው ። መና የወረደው በምድረ በዳ ነው አሉ ። እነርሱ ግን መናን እየፈለጉ ያሉት በለማ ከተማ ውስጥ ነው ። የምድረ በዳ መና በከተማ አይወርድም ። መና በምድረ በዳ ባይወርድ ሕይወት አይቀጥልም ነበር ፤ በከተማ መና ቢወርድ ሥራ አይኖርም ነበር ። ሥራ በራሱ የሚካፈልልን ጭንቀት አለ ። ረባሽ ልጅን በመምታት ማሳረፍ አይቻልም ፣ ኃይሉን የሚያበርድበት የጨዋታ ዕቃ በመስጠት ግን ሁለት እርካታ ማግኘት ይቻላል ። አእምሮ ማለት ረባሽ ልጅ ነው ። ማሰብ የማይፈልገውን የሚያስብ ነው ። ማሳረፊያው ሥራ ነው ።
መነኮሳት ከጸሎት በኋላ ወደ ሥራ መሰማራት አለባቸው ። ሚኒስትሮች ከስብሰባና ከቢሮ በኋላ አትክልቶችን መንከባከብ አለባቸው ። ለመዝናናት ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሁሉ ሥራ በራሱም መዝናኛ ነው ። አገርና ቤተ ክርስቲያን የሚለወጡት በሥራ ነው ። በምኞት የተለወጠ አገርና ወገን የለም ። እንደ ባሪያ ከሠራን ኋላ እንደ ጌታ እንበላለን ፣ እንደ ጌታ ከሠራን እንደ ባሪያ እንበላለን ። እባካችሁን ለክለሳ ተመልሰን አንመጣምና ዕድሜአችንን እንሥራበት ።
እነዚህ ሰዎች የፈለጉት ተአምር ከዕለት ወደ ዘመናት የሚሻገር ነው ። መናውን ያውቁታል ፤ መናውን ያወረደው ከፊት ለፊታቸው በትሑት ሰብእና የቆመው ክርስቶስ መሆኑን ግን አላወቁም ። መናውን አውቆ ሰጪውን አለማወቅ እንዴት መጎዳት ነው ? የመናው አድራሻ ከሰማይ መሆኑን አውቀዋል ፣ የተጻፈውንም አውቀዋል ። በርግጥም እንጀራ ከምድር ቢመስልም እንጀራ ከሰማይ ነው ። ለዚህ ነው ፡- የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን የሚባለው ።
የዘመናት መናን መናፈቅ ዛሬ ብዙዎችን ሌባ ያደረገ ነው ። ለዘመናት የሚበቃ ደህና ነገር መያዝ አለብን በማለት ብዙዎች ነፍሰ ገዳይ ሁነዋል ። ለዛሬ በቂ በረከት ነበር ። ለዘመናት በሚሰበስቡ ሰዎች ግን የዛሬ ሰዎች ይራባሉ ። ዛሬን ማደር የማይችሉ ሰዎች ባሉበት ዓለም ላይ ስለሚመጣው ዓመት እንጨነቃለን ። እውቀትና አለማወቅ እየተፈራረቁብን ይመስላል ። እግዚአብሔር መናን የላከው ያጠራቅሙ ዘንድ አይደለም ይበሉ ዘንድ ነው ።መሰብሰብ ይቻላል መብላት ግን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ብቻ ነው ። ብዙ ሰው ለመሰብሰቡ እርግጠኛ ነው ፣ ለመብላቱ ግን እርግጠኛ አይደለም ። ይበሉም ዘንድ እንጀራን ሰጣቸው ይላል ። ሁለት ነገሮችን ያሳየናል፡-
1-  እንጀራ የበሰለ በረከት ነው ። ከተበላ ዝግጁ ነው ። ከተቀመጠ ግን የሚበላሽ ነው ። እግዚአብሔር ለልጆቹ የበሰለ እንጀራ አለው ።
2-  ይበሉም ዘንድ ይላል ። መብላት ከእግዚአብሔር ነው ። ጠቢቡ ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” መክ. 2 ፡25 ። እንጀራ ስጦታ ነውና ሰጪውን ያሳያል ። ስንቶቻችን ዛሬ ስለምንበላው እንጀራ እናመሰግናለን ? እግዚአብሔር ይቅር ይበለን ።
እነዚህ ሰዎች እንደ ተጻፈ በማለት ጥቅስ ጠቅሰዋል ። ጥቅስ የሕይወት መገለጫ አይሆንም ። ሰይጣንም ለራሱ አሳብ ይጠቅሳል ። ሰይጣን የራሱ መጽሐፍ ስለሌለው አሳቡን በማጣመም ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል ።
ጌታችን የእነዚህን ሰዎች የተሳሳተ ልመና ከመንቀፍ ይልቅ እምነታቸውን አረመው ፡- ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም” ዮሐ. 6፡32 ።
ጌታችን ክብር ይግባውና እውነት እውነት እላችኋለሁ አለ ። አጽንዖት እየሰጠ ነው ። እውነተኛ እንጀራ ማለቱም ያጠገባቸው በምትሐት ሳይሆን በአማን መሆኑን ለመግለጥ ነው ። የመናው ሰጪው የሁሉ አባት እግዚአብሔር ነው ። ሙሴ ግን የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው ። ጌታችን ሙሴን እያቃለለ አይደለም ፣ ራሱ ሙሴ የሚሰጣቸውን መልስ እየሰጠለት ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ