የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት እንጀራ

“ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም ።” ዮሐ. 6 ፡ 35 ።
ጌታችንን ሊያነግሡት የፈለጉ እነዚያ ሰዎች ስለ ሕይወት እንጀራ ሲነግራቸው እነርሱ ግን ይሰሙ የነበረው ስለ ዕለት እንጀራ ነበረ ። የዕለት እንጀራን እያሰቡ የጠየቁት ግን የሕይወት እንጀራን ነው ። በመዘናጋት ሲጠይቁ ጌታችን በማስተዋል መለሰ ። በግዴለሽት ሲናገሩ ጌታችን በቁምነገር መለሰ ። በዚህም እኛ የምንማርበትን ነገር አገኘን ። ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት ።” ጌታችን ያ እንጀራ የሚፈለግ ሳይሆን ፈልጎን የመጣው ራሱ መሆኑን ተናገረ ። መልሱ ጥያቄ ከሆነባቸው ጥያቄው እንዴት ሊሆንባቸው ነው ? ጌታችን “እኔ ነኝ” የሚል ፍጽምና ባለው መንገድ ተናግሯል ። እኔ ባይ እርሱ ብቻ ነውና ። እኔ እንዲህ ነኝ ማለት ከፍጡር ወገን ማን ይችላል ? እምነታችን በጥርጥር ፣ ብርታታችን በድካም ይለወጣልና ። እኔ ነኝ ማለት በቀን ሦስት ጊዜ ለምናብደው ለእኛ ተስማሚና ገላጭ አይደለም ። እርሱ ግን እርሱ ነው ። የእግዚአብሔር ጽናት ባይደግፈን ኑሮ ዛሬ አለሁ ለማለት ባልቻልን ነበር ። አድራሻ ባይኖረንም የሁልጊዜ አድራሻችን እርሱ ነው ። ባለጌ ልጅ አድራሻ የለውም ። እዚህ ነው ሲባል እዚያ ይገኛል ። የዋለበት ማደር ፣ ያደረበት መዋል አይችልም ። እናት ግን ቋሚ አድራሻ አላት ። ባለጌው ልጅ አድራሻ ባይኖረውም አድራሻ ያለው ወዳጅ አለው ። እናቲቱ ፈልጋ አታገኘውም ፣ ቋሚ ነገር የለውምና ። ባለጌው ልጅ ግን ፈልጎ አጥቷት አያውቅም ። እናቲቱ ልጇን ፈልጋ ለማግኘት ትደክማለች ፣ እንደ ምንም ከተገኘ ደግሞ አልሄድም ብሎ ያስቸግራታል ። ነቢዩ ይህንን አይቶ እንዲህ አለ ፡- እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ ፥ ስሙ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን ? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ ።” ኢሳ. 7 ፡13 ።

እግዚአብሔር ባለ አድራሻ ነው ፤ ሁልጊዜ በስፍራው ነው ። እኛም ተነዋዋጭና ተለዋዋጭ ነን ። እርሱ ግን፡- እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ያለው ነው ። ሚል. 3 ፡ 6 ። ስንናወጥ ቢናወጥ ኑሮ ምን እንሆን ነበር ?
የአለቃ ገብረ ሃና ሚስት ማዘንጊያ ባላቸው እየወሰለቱ ሲያስቸግሯቸው እርሳቸውም ስህተትን በስህተት ለማጥራት መወስለት ፈለጉ ። ከጎረቤታቸው ጋር ጉዳይ ጀመሩ ። አለቃም በጊዜ መግባትና መተከዝ ላይ ሳሉ ሚስታቸው በር አንኳኩ ። አለቃም በሩን በዚያ ምሽት ከፈቱና “ማዘንጊያ ገብተሸ አልቀሽ ከሆነ በሩን ልዝጋው” አሉ ይባላል ። ይህ ንግግር ሁለት ዓይነት ሰይፍ አለው ። የመጀመሪያው ሚስታቸው በጣም ረጅም ነበሩና ቀውላላነታቸውን ለመንካት ሲሆን ሁለተኛው እዚያ ቤት ገብተሸ አልቀሽ ከሆነ እኔም ቁርጤን ልወቀው የሚል ነው ። አዎ ገብተን የማናልቅ ነን ። ጭንቅላታችን ሲታይ ገቡ ይባላል ፤ ፊታችንን አስወግተን እንመለሳለን ። ትከሻችን ሲታይ መጡ ፣ መጡ ይባላል ፤ መልሰን እንወጣለን ። በእግዚአብሔር ቤት ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ገብተው ያላለቁ ወይም ያልወሰኑ ሰዎችን እናያለን ። መጡ ሲባል ይሄዳሉ ፣ ያቆሙበትን ስለሚያውቁ በዓመቱ ይጀምራሉ ። አደገኛ መንገድ ነው ። እነዚህ ናቸው አምላኬን የምታደክሙ የተባለላቸው ። በር በሩን እያዩ የሚጠብቁ እግዚአብሔርና አገልጋዮች በመምጣታችን ደስ ይላቸዋል ። ወላጅ ናቸውና ሆዳቸው ይባባል ። ስንወለድ ያዩ አይጨክኑም ።
ጌታችን ራሱን “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ” በማለት ገለጠ ። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሰባት “እኔ ነኝ” የሚሉ መገለጫዎችን ጌታችን ተጠቅሟል ። የመጀመሪያው ይህ ነው ። እንጀራ ለእኛ ልዩ ትርጉም ያለው ነገር ነው ። የዘወትር ምግባችን ነው ። ጌታችን እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ አለ ። ሆድን ሳይሆን ነፍስን የማጠግብ ነኝ ማለቱ ነው ። እንጀራ ከጤፍ ፣ ከስንዴ ፣ ከገብስ ፣ ከዘንጋዳ ቢዘጋጅ ያው ሰፊ ነው ። ጌታችንም ሁሉን የሚቀበል ሰፊ ነው ። እቅፉ የማይደፈር ምሽግ ፣ ትከሻዋ የማይጠብ መስክ ነው ። እንጀራ ክብ እንደሆነ እርሱም ዓለሙን የወደደ ነው ። እንጀራ ዓይኑ ብዙ እንደሆነ ጌታችንም ለጥበቡ ስፍር የለውም ። እንጀራ ሞቶ ሕይወት የሚሰጥ እንደሆነ ጌታችንም በሞቱ የዘላለም ሕይወትን የሰጠን ነው ።
በዓለም ላይ የተነሡ ፈላስፎች ፣ ነገሥታትና ባለ ራእዮች ብዙ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ ። እንጀራ እንሰጣለን ይሉ ይሆናል ። እንጀራ ነን ግን ብለው አያውቁም ። ቢሉም ለመሆን አይበቁም ። እርሱ ግን እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ አለ ። ብሉ የሚል ደግ በዓለም ላይ ብዙ አለ ። ብሉኝ ያለ የደጎች ደግ ግን እርሱ ብቻ ነው ። ወደ ራሱ ያቀረበን ትሑት መምህር ብቻ ሳይሆን ራሱን የጋበዘን ደግ አባት ነው ። ምድራዊው እንጀራ ደመ ነፍስን ይደግፋል ። ይህ እንጀራ ደግሞ ሕይወትን ይሰጣል ። እንጀራ ለማግኘት ሰው ሁሉ ይራኮታል ። ይህ እንጀራ ግን ፈልጎን የመጣ እንጀራ ነው ። ምድራዊው እንጀራ ሞቶ ጊዜያዊ ሕይወት  ይሰጣል ። ይህ እንጀራ ግን ሞትን አሸንፎ የተነሣ ነው ። እንጀራ ሁሉ በዝምታው በመዓዛው ብሉኝ ይላል። ይህ እንጀራ ግን ሕያው ነውና ነባቢ እንጀራ ፣ ብሉኝ የሚል ድምፅ ነው ። ምድራዊው እንጀራ ቢበሉት የማይስማማቸው አሉ ። ይህ እንጀራም ለመናፍቃን ሕመም ነው ። ይልቁንም ግኖስቲካውያንና ተከታዮቻቸው ግዙፍ ነገርን እንደ ርኩስ ይቆጥራሉ ። ቅዱስ ቊርባንን እንደ ተራ ማዕድ የሚቆጥሩም ይህ እንጀራ ጥያቄአቸው ነው ። እንጀራ ሲፈለግ ጥያቄ ሲገኝ መልስ ነው ። በጥያቄ የፈለጉት በመልስነቱ የሚያርፉበት ገበታ ክርስቶስ ነው።
እንጀራ መራራ ነው ። ማባያው ግን ጣፋጭ ነው ። እንጀራው መራራ ባይሆን ብዙ አይበላም ነበር ። ክርስቶስም ከመስቀል ጋር የምናመልከው ነው። ክርስትናምመስቀልና ክብር ነው ። የፋሲካው በግም ከመራራ ቅጠል ጋር እንዲበላ ታዟል ። የዚያ ተምሳሌት እንዲሆን በመራራ አፍ ወይም በጦመ አፍ ቅዱስ ቅዱስ ቊርባን ይወሰዳል ።
እንጀራ አፍለኛ ሁኖ በዕለት ይበላል ። ቦክቶ ተነሥቶ በሦስተኛው ቀን ይበላል ። ጌታችንም ሞትና ትንሣኤን ገንዘቡ አድርጎ የልብ ኩራት ፣ የነፍስ ዕረፍት ሁኗል ። ጌታችን ለእነዚህ አንጋሾች ፣ እንጀራን ሕይወት አድርገው ለሚኖሩ ሰዎች “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ” ያለው ለምንድነው ? የማይረካ ፍላጎት ላላቸው ፣ ደረስኩ ሲሉ ሁሉ ለሚርቃቸው መልስ መሆኑን ለመግለጥ ነው ። ዓለም በወደደው እየተቀጣ የሚኖር ነው ። ብዙ ሰው ለምኖ ባገኘው እየተጨነቀ ነው ። “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” እንዲሉ ።
በመቀጠልም፡- ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም ።” አለ ። ዮሐ. 6 ፡ 35 ። ወደ እኛ መጥቶ ሳለ ወደ እኔ የሚመጣ እንዴት አለ ? በሥጋዌ መንገድ ወደ እኛ መጥቷል ፣ እኛ ደግሞ በእምነት ወደ እርሱ መሄድ ያስፈልገናል ። እምነት ወደ እግዚአብሔር መገስገስ ነው ። ከመታወቅ በላይ የሆነውን እግዚአብሔር ሲያውቁ መኖር ነው ። ወደ ክርስቶስ መምጣት የራስን አውቃለሁ ባይነት መካድ ነው ። ዕረፍቴ ባንተ ነው ብሎ አምኖ መቅረብ ነው ። ዝናብ የሌላት ደመና ዓለምን ክዶ በክርስቶስ ግዛት መጠቅለል ነው ። ጌታችን በሰጠው ቃል ኪዳን ወደ እርሱ የሚመጣ ከቶ አይራብም ፤ አይጠማም ።
ጌታችን እንጀራን ተክቼ መብል ታቆማላችሁ እያለ አይደለም ፤ ውኃ ተክቼም ውኃ ታቆማላችሁ ማለቱ አይደለም ። የሕይወት ጥጋብና እርካታ እሆናችኋለሁ እያለ ነው ። ያውም በነጻ ። የሕይወት ረሀብ ምንድነው ? የማርፈው የት ነው ብሎ መጨነቅ ነው ። ዕረፍት ግን የቦታ ፣ የጊዜና የሁኔታ ውጤት አይደለም ። ዕረፍት ከእግዚአብሔር ነው ። የሕይወት ረሀብ መቅበዝበዝ ነው ። የሕይወት ረሀብ የሙከራ ሕይወት ነው ። የዓለም ነገር የፈለጉት ነገር ሲገኝ ደስታው የፍለጋውን ያህል አይደለም ። ጌታ ግን እኔ የሕይወት ጥጋኝ ነኝ አለ ። እርሱ የሕይወት እርካታ ፣ የበቃኝ ኑሮም መሠረት ነው ። ወደ እርሱ መምጣት ግድ ይላል ። ጥጋብና እርካታን ሁሉም ይፈልጋል ። ይህ ግን በክርስቶስ እንደሆነ ለማመን አብዛኛው ይቸገራል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ