“በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፡- እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት” /ዮሐ. 1፡35-37/።
ይህ ጊዜ ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾሞ ከተመለሰ በኋላ በሁለተኛው ቀን ነው። “በነገው” የሚሉ ቀን አመልካች መግቢያዎች ሦስት ጊዜ ተጠቅሰዋል /ዮሐ. 1፡29። ቊ. 35ና 35/። በሦስተኛው ቀን በቃና ዘገሊላ ሠርግ ነበረ። ይህ ሦስተኛ ቀን ጌታችን ጾሞ ጸልዮ በተመለሰ በሦስተኛው ቀን ማለት ነው። ከጌታችን ደቀ መዛሙርት እንድርያስና ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ፣ ፊልጶስና ናትናኤል የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ናቸው። ዮሐንስ እነዚህን ስድስት ደቀ መዛሙርት ሲያዘጋጅ ቆይቶ መሢሑ ሲመጣ እርሱን ተከተሉት ብሎ በደስታ ሸኛቸው። ለደቀ መዝሙርነት ለመብቃትና ለመንፈሳዊ አደራ ለመታጨት ዝግጅቶች ይታያሉ። የብሉይ ኪዳኑ ሳኦል አህያ ፍለጋ ወጥቶ ንግሥና እንዳገኘ፣ የቀሬናው ስምዖን ከመንገድ ተጠልፎ መስቀል እንደ ተሸከመ እያሰብን ሁሉም የእግዚአብሔር አገልጋዮች በዚህ መንገድ የመጡ ይመስለናል። ይህ ሁለት ችግር ያስከትላል። የመጀመሪያው ለቀደሙት አባቶች ክብር የለሽ ያደርገናል። ሁለተኛው ዝግጅትን እንድንንቅ ያደርገናል። ለመንፈሳዊ አደራ ለመብቃት መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልጋል። ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተነሥተን ስንመለከት እንዲሁ አልተመረጠችም። ሕይወቷ በቅድስናና የእግዚአብሔርን ቃል በመመርመር የተሞላ ነበር። የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ሳኦል አህያ ፍለጋ ሄዶ መመረጡ ለደቀ መዝሙርትነት ሳይሆን ለንግሥና ነው። ደቀ መዝሙርነት የነፍስ አደራ በመሆኑ ከንግሥና ይበልጣል። ለመንፈሳዊ አደራ ለመብቃት ዝግጅት ግድ ነው።
የጌታችን ስድስት ደቀ መዛሙርት፡-
1- የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በርግጥ ተመላላሽ ተማሪዎች ነበሩ። ጌታ ከጠራቸው በኋላ ግን የአዳሪ ተማሪ ሆነዋል።
2- በዮሐንስ ጥምቀት የተጠመቁ ነበሩ። የንስሐ ጥምቀት ነውና በንስሐ ዝግጅት አድርገዋል።
3- ዮሐንስ ከሚናገረው በመነሣት ቅዱሳት መጻሕፍትን ይመረምሩ ነበሩ። ለዚህም ናትናኤል በበለስ በታች ሆኖ መጻሕፍትን በመመርመር መሢሑ በእርግጥ ኢየሱስ መሆኑን ለማመሳከር ይሞክር ነበር።
4- ምንም እንኳ በዚህ ክፍል እንድርያስ ጴጥሮስን እንደ ጠራው ብናነብም ጴጥሮስ ግን ዮሐንስ በሚያጠምቅበት በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ነበር። ጴጥሮስ ሰፈር መንደሩ ጥብርያዶስ ባሕር አካባቢ ነው። አሁን ግን ያለው ወደ ታች ወደ ጌልጌላ የአንድ ቀን መንገድ ርቆ ነው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ከንስሐ ጥምቀት በኋላ መሢህን የማግኘት ጥማት ነበራቸው።
“በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፡- እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት” ይላል/ዮሐ. 1፡35-37/። እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት ዮሐንስና እንድርያስ ናቸው። ዮሐንስ ለያዕቆብ፣ እንድርያስም ለጴጥሮስ ይተርፋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለወኅኒ ቤቱ ጠባቂ፡- “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” እንዳለው ክርስቶስ የቤተሰቡን አንድ አባል ካገኘ ግዛቱን እያሰፋ ይሄዳል /የሐዋ. 16፡31/። ዮሐንስ ያዕቆብን ቢጠራ ያዕቆብ ከሐዋርያት የመጀመሪያው ሰማዕት ሆነ /የሐዋ. 12፡2/። እንድርያስም ጴጥሮስን ቢያመጣው ጴጥሮስ ዋነኛ ባለ አደራ ሆነ። ወደ እግዚአብሔር የምናመጣቸው ሰዎች ከእኛ የተሻለ እንደሚሮጡ ማመን አለብን። ይህ ቋሚ ሕግ ነው። የነቢዩ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕ በእጥፍ መንፈስ አገልግሏል። ጌታ ኢየሱስም፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” በማለት ተከታዮቹ የበለጠ እንዲያደርጉ ፈቅዷል /ዮሐ. 14፡12/። ዛሬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ያመጣናቸውና ያስተማርናቸው ሰዎች ከእኛ የመጨረሻ መገለጥና እውቀት ስለሚጀምሩ የበለጠ ማድረጋቸው እሙን ነው። ይህ የሕይወት ሕግ ነውና በደስታ ካልተቀበልነው እንደ ድመት ወልደን ልንበላ እንችላለን።
ዮሐንስ ለመላው ዓለም ነዋ በግዑ እያለ ክርስቶስን ማስተዋወቁን ሰምተናል /ዮሐ. 1፡29/። ይህ ምስክርነቱ ግን እውነተኛ መሆኑን የሚከተሉትን ደቀ መዛሙርት አሳልፎ በመስጠቱ ይታወቃል። ደቀ መዛሙርቱን ያስተማረው ለራሱ ክብርና ጥቅም አልነበረም። ለክርስቶስ ነው። ይተኩኛል ወዴት ይሄዳሉ? የሚል ጥያቄ አልነበረውም። አገልጋይ ጡረታ የለውም። ጡረታው ዐረፍተ ዘመኑ ነው። እስካለ ድረስ ያገለግላል፣ ያለበት ቦታም የአገልግሎቱ መድረክ ይሆናል። ጌታ የሰጠውን መልሶ ሰጠ። በሕይወት ውስጥ ዕረፍት ያለው የሰጠንን መልስን ስንሰጥ ነው። የሰጠንን ደቀ መዛሙርት፣ የሰጠንን ትዳር፣ የሰጠንን ልጆች፣ የሰጠንን ገንዘብ፣ የሰጠንን ክብር መልሰን ስንሰጥ እፎይ እንላለን። አሊያ በመልካሙ ነገር መታወክ እንጀምራለን። ጌታችን፡- “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” ያለው ለዚህ ነው /ማቴ. 5፡3/። በሥጋ ድሆች የሆኑ ብፁዓን አይደሉም። የታደሉ፣ የተመሰገኑና ደስተኞች አይደሉም። እንደውም ግራ የተጋቡ፣ የተነቀፉና ኀዘነተኞች ናቸው። በመንፈስ ድሆች የሆኑ እያላቸው እንደሌላቸው የሚኖሩ፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ሰጥተው እኔ ደካማ ነኝ የሚሉ ናቸው። መጥምቁ ዮሐንስ ይህን ተግባር ፈጸመ።
እግዚአብሔር ለጻድቁ አብርሃም፡- “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ” /ዘፍ. 22፡2/። አብርሃም በዚህ ነገር ውስጥ ብዙ ነገሮችን አስተዋለ፡-
1- ልጁ ጣኦት እንደሆነበት ተረዳ። ስጦታን ያለ እግዚአብሔር ካዩት ጣኦት ይሆናል። በዚያ ነገር መመካት ብቻ ሳይሆን ባጣው ምን እሆናለሁ? ማለትም ጣኦት አምልኮ ነው።
2- ይስሐቅን ቢል ይስሐቅ ያጣዋል፣ እግዚአብሔርን ቢል ይስሐቅን ያተርፈዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ወሰነ።
3- በይስሐቅ ላይ የሣራ መብት እኩል ቢሆንም ለሣራ መንገር አልፈለገም። ምክንያቱም ከአብርሃምም ከሣራም በላይ ይስሐቅ የእግዚአብሔር ነውና። ደግሞም እግዚአብሔር ሲያዝዘው ከማን ጋር ይማከራል? /ገላ. 1፡16-17/።
4- እግዚአብሔር ከሙት አካል ልጅ እንደ ሰጠው አሁን ደግሞ የሞተውን በማስነሣት የበለጠ እንደሚያሳየው አመነ /ዕብ.12፡19/።
መጥምቁ ዮሐንስም ደቀ መዛሙርቱን ለጌታ አሳልፎ ሰጠ። ደርሰው እንዲመጡ ሳይሆን ለዘላለም የእርሱ እንዲሆኑ ሰጠ። እኛ በእጃችን የያዝነው ከርሞ አይገኝም። ለእግዚአብሔር የሰጠነው ግን ሁልጊዜ ይኖራል። ደቀ መዛሙርትን በሚመለከት መምህራን እንደ ድመትና እንደ ጦጣ ያሳድጋሉ። ድመት በጥርሷ ነክሳ ታሳድጋለች። ጦጣ ደግሞ እንዳዘለች ረስታ ትዘላለች። ድመት ልጇን ትፈልጋለች፣ የጦጣ ልጅ ደግሞ እናቷን ትፈልጋለች። ሁልጊዜ እኛ ብቻ ደቀ መዛሙርትን መፈለግ፣ ሁልጊዜ ደቀ መዛሙርት ብቻም እኛን መፈለግ የለባቸውም። በጣም መሰቀቅና በጣም ግዴለሽ መሆን ሁለቱም ተገቢ አይደለም። ወደ ክርስቶስ እየመሩ በመጽናናት ማገልገል ይገባል።
መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ጌታ ከመራቸው ደቀ መዛሙርት አንዱ ዮሐንስ ነው። ወንጌሉን ሲጽፍ ግን ስሙን አልጻፈም። ይህ ትሕትናን ያሳያል። መምህሩ ወደ ጌታ አመለከተ፣ እርሱ ደግሞ ስሙን ሰወረ። የጌታ ደቀ መዝሙር ለመሆን ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ፣ ልታይ ልታይ የሚል ስሜትን ማራቅ ያስፈልጋል። በትክክል ለመላክ በትክክል መስማት፣ ጥሩ መምህር ለመሆን ጥሩ ተማሪ መሆን ግድ ነው። መጥምቁ ነዋ በግዑ በማለት የእግዚአብሔርን በግ በድጋሚ አስተዋወቃቸው። አዳኛችሁ እርሱ ነው በማለት መስቀሉን ነገራቸው። እነርሱም መሥዋዕትነት የሚጠብቀውን ጌታ ለመከተል ቆረጡ። ተምነው መጡ። ካልተመኑ አገልግሎት ከባድ ነውና። ከተመኑ አገልግሎት ደስታ ነው።
እግዚአብሔር እኛንም ያግዘን።