“ናትናኤልም፡- ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን? አለው። ፊልጶስ፡- መጥተህ እይ አለው”
/ዮሐ. 1፡47/።
ፊልጶስ ከቤተ ሳይዳ ከነጴጥሮስ መንደር የተገኘ ሰው ነው። ናትናኤል ደግሞ ከገሊላ ቃና የተገኘ ነው። ጌታ ነገ ወደ ገሊላ ቃና ይሄዳልና የገሊላ ቃና ሰው የሆነውን ናትናኤልን ሊፈልግ መጣ። አንዳንዱን በቀጥታ ያገኘዋል። በድምፅ ያናግረዋል። ድምፁ የፍቅር ቅላፄ ፥ ድምፁ አላሳልፍም የሚል ጠባብ መንገድ ፥ ድምፁ የተለያየ ነገር ይሆናል። አንዳንድ ሰው በቀጥታ ይጠራል። ሌላው ደግሞ በሰዎች በኩል ጥሪ ይደርሰዋል። በየትም ይሁን የጥሪው ባለቤት እግዚአብሔር ነው። በሰዎች የመጡ ያመጧቸው ሲጠፉ ግራ ይጋባሉ። ማንም ያምጣ ጠሪው ግን እግዚአብሔር ነው። በየት በኩል እንደምንገኝ እርሱ ያውቀዋል። እርሱ ብቻ የት ቦታ ሲመቱ አቤት እንደሚሉ ፥ የት ቦታ ሲኮረኮሩ እንደሚስቁ ያውቃል። ካለበት ለመድረስ ዓይናችን ባለማወቅ ፥ እግራችን በሰንሰለት የተያዘ ኃጢአተኞች ነበርንና ካለንበት ድረስ መጣ። ካለንበት መጥቶ ካለበት ወሰደን። አለማወቃችንን ወልደ ዮሴፍ ማለታችንንም አልታዘበም። እንዴት? ብሎም አልገሰጸም። የት ታውቀኛለህ ስንለውም አሁንም ትሑት ነው። ናትናኤልን በፊልጶስ በኩል ጠራው።
ናትናኤል ግልጽ ሰው ፥ የግንባር ሥጋ ነው። ከጌታችን ደቀ መዛሙርት ውስጥ ኋላ ቀነናዊ ስምዖን የተባለ እርሱ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያምናሉ። እነዚህ ሊቃውንት ቀነናዊ ስምዖን ናትናኤል መሆኑን ያመኑት በጠባዩ ተነሥተው ነው። በእርግጥ በጌታችን ደቀ መዛሙርት ዝርዝር ውስጥ ብዙ ጊዜ ናትናኤል የሚለው ስም አልተጠቀሰም። ጌታችን ከተነሣ በኋላ በጴጥሮስ አስተባባሪነት ወደ ጥብርያዶስ ባሕር ከሄዱ ደቀ መዛሙርት ጋር ግን ናትናኤል ተጠቀሷል /ዮሐ. 21፡2/። ናትናኤል ከደቀ መዛሙርት አንዱ ነው። በደቀ መዛሙርት ዝርዝር ውስጥ ግን ስሙ አልተጠቀሰም። ስለዚህ አብዛኛዎች ተርጓሚዎች በርተሎሜዎስ የተባለው እርሱ ናትናኤል ነው ይላሉ። ይህን ሊሉ የቻሉበት ምክንያት አንደኛ ከፊልጶስ ቀጥሎ የሚጠራው በርተሎሜዎስ ስለሆነ ያ ሰው ናትናኤል ነው የሚል ግምት ነው። ሁለተኛው በርተሎሜዎስ ስም አይደለም የተሎሚ ልጅ ማለት ነው። የቤተሰብ ስም ነው ። ስለዚህ ይህ ሰው ናትናኤል ነው ይላሉ። በርተሎሜዎስ የቤተሰብ ስም መሆኑን የኢትዮጵያ ሊቃውንትም ያምናሉ። ናትናኤል የተባለውን ስም የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል ላይ ብቻ ነው። ዮሐንስ ጥሪውንና ኋላም ወደ ጥብርያዶስ ከነጴጥሮስ ጋር መመለሱን ይጽፋል። ስለዚህ ሌሎቹ ወንጌላት በርተሎሜዎስና ቀነናዊ ስምዖን በማለት የጠቀሱት ናትናኤልን እንደሆነ በመገመት አንዱን ስያሜ ይመርጣሉ።
ናትናኤል ቀጥተኛ ሰው ፥ ለእስራኤልም ትልቅ ፍቅር ያለው ደግሞም መጻሕፍት አዋቂ ፥ በየመንገዱ የማይቀየስ ጽኑ ሰው ነው። እንዲህ ያለው ሰው ቀነናዊ ወይም የነጻነት ታጋይ ቢሆን የሚጠበቅ ነገር ነው። ተጣጣፊዎችና ለዘብተኞች ወደዚህ ሊገቡ አይችሉም። ናትናኤል ቊጭት ሲበረታበት እንዲህ ያለው ነገር ውስጥ መግባቱ ግድ ነው። ስለዚህ አባቶች ከጠባዩ በመነሣት ስምዖን ቀነናዊ የተባለው ናትኤል መሆኑን ያምኑበታል። ደቀ መዛሙርቱ በአብዛኛው ባለ ሁለት ስም ናቸው። የናትናኤል ስም ሁለት መሆኑ ልዩ ነገር አይደለም። ምናልባት ይህ ሰው የሮማ መንግሥት ተቃዋሚ ስለሆነ ስሙ እንዲሰወር ጌታ ፈልጎ ይሆናል። ዮሐንስም በወንጌሉ ስሙን የጠቀሰው ወንጌሉን የጻፈው በ90 ዓ.ም ገደማ ስለነበር በዚህ ጊዜ ናትናኤልም በሕይወት ስለሌለ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ምሥጢር አለ። ይህ ምሥጢር ጠፍቶ ነው ዛሬ ይህ ሁሉ መዝረክረክ የመጣው። ይህ ብቻም አይደለም በእግዚአብሔር መንግሥት ወንድምን ከአጥፊዎች መከለል ጎልቶ ይታያል። ደቀ መዛሙርቱ የተለያየ ጠባይ ፥ የተለያየ የእውቀት ደረጃ ፥ የተለያየ ርእዮተ ዓለም ቢኖራቸውም ጌታ ግን ጠባያቸውን እየነቀሰ ሊነቅፋቸው አልወደደም። አብዛኛው ጠባይ የልጅነት ጠባይ በመሆኑ በማደግ የሚሻር ነው። በማደግ የሚሻር ጠባይን በነቀፋና በዱላ ማስጣል አይቻልም። አንዳንዱ ጠባይ በትምህርት ይወገዳል። የሚበዛው ግን በመንፈስ ቅዱስ የሚወገድ ነው። ትምህርቱ የመጣው ከሰማይ በመሆኑ በሰማያዊ ኃይል የሚፈጸም ነው። እሳት እንደሚያቃጥል በልጅነታችን ሲነገረን ኖሯል። ይህ ትምህርት ግን የተሻረው በማደግ ነው። እግዚአብሔር ይህን ጣሉ ብሎ አይታገለንም ፤ ውስጣችንን ሲያሳድገው ግን መጣል ያለብንን እንጥላለን።
ናትናኤል ማለት የስሙ ትርጉም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው። የናትናኤል አድራሻው እግዚአብሔር መሆኑን ቤተሰቡ ያምን ነበር። በርግጥም እንደ ሰየሙት ሆነላቸው። ለልጆቻችን ያለን መልካም ስያሜ አንድ ቀን ራእያቸው ይሆናል።
ናትናኤል ባልንጀራው ፊልጶስ የሙሴና የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ የሆነውን የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኝተነዋል ሲለው የሰጠው ምላሽ የሚደንቅ ነው፡- “ከናዝሬት መልካም ነገር ሊወጣ ይችላልን?” የሚል ነው። ይህ በሁለት ምክንያት ነው።
1- ናዝሬት የሽፍታና የዓመፀኛ ከተማ ነበረች። ከዚህች ከተማ እንዴት መልካም ሊወጣ ይችላል አለ። መሢሑን ሌላ ስም ሰጠው። ያ ስሙ መልካም ነበር። መሢሑ መልካም ብቻ አይደለም ብዙዎችን መልካም የሚያደርግ ነው ፥ ስለዚህ እንዴት ከናዝሬት ሊወጣ ይችላል? የሚል ጥያቄ አቀረበ።
2- መጻሕፍትን ያውቅ ስለነበር ኢየሱስ ከቤተ ልሔም እንጂ ከናዝሬት ይወጣል የሚል ቃል አላነበበምና ከትንቢቱ ጋር የማይገጥም ነው ለማለት ያ መልካም ከናዝሬት እንዴት ይወጣል? አለ።
ጌታ ኢየሱስ ግን በርግጥም የናዝሬቱ መልካም ነው። ተስፋ ከተቆረጣት ከተማ የወጣ ዓለሙን ያጣፈጠ ጨው ነው። እርሱ በጽድቃቸው በሚመኩ ፥ በመጻሕፍት እውቀታቸው በሚኮፈሱ በኢየሩሳሌም ሳይሆን ስም የለሽ ከሆነችው ከናዝሬት ወጣ። የተናቀን ማክበር ፥ ያደፈውን ማጥራት እርሱ ይችላል። እናት ጨዋ ልጇን ለሌላ ታሳቅፍና ዓመፀኛ ልጇን ራሷ ትሸከማለች። ከእርሷ ፍቅር በቀር ማንም አይችለውምና። ጌታም ከእኔ በቀር ማንም አይችላቸውም ብሎ ኃጢአተኞችን ይወዳል። እርሱ ወንድሞች ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም /ዕብ. 2፡13/። አሁን ደግሞ የናዝሬቱ ኢየሱስ ተብሎ ሲጠራ አላፈረም። እርሱ እንኳ በእኛ ካላፈረ እኛ እንዴት በእርሱ እናፍራለን? ሐፍረት ቦታ የተለዋወጠ ይመስላል። ናትናኤል ሁሉንም ነገር የሚቀበለው እንደ ቃሉ ነው።
ፊልጶስ ግን በመጻሕፍት እውቀት የበረታውን ይህን ሰው ሊሟገተው አልቻለምና “መጥተህ እይ” አለው። ኢየሱስን በመስማት ብቻ ማወቅ አይቻልም። ማየትም ያስፈልጋል። ምንጭ ነው ይጠጣል ፥ ኅብስት ነው ይበላል። ንግሥተ አዜብ ሰሎሞንን ባየችው ጊዜ፡- “ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል” እንዳለች ከሰሎሞን የሚበልጠው ጌታ ሲያዩት ይለያል /1ነገሥ. 10፡7፤ ማቴ. 12፡42/። ጻድቁ ኢዮብም በመጨረሻ፡- “መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር አሁን ግን ዓይኔ አየችህ” ብሏል /ኢዮ. 42፡5/። በዚህ ዓለም ላይ ያለብን ቊስለት የሰማነውና የምናየው አልመጣጠን እያለን ነው። ብዙ ጊዜ የምንሰማው የተጋነነውን ነው። በደግም በክፉም ተጋኖ እንሰማለን። ስናገኘው ግን መጠነኛ ነው። ጌታችን ግን ከሰማነው የሚበልጥ ነው። ስለ ጌታችን የሚነገረው ሁሉ ትንሽ ነው። እርሱ የሚታይ ነው።
“ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እርሱ፡- ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ አለ” ጌታችን ወደ እርሱ እስኪደርስ አልጠበቀም። በአደባባይ መሰከረለት። እውነተኛ እስራኤላዊ እውነተኛ የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ተናገረለት። የእግዚአብሔር ሕዝብ ወይም ብእሴ እግዚአብሔር መለኪያው ተንኮል የሌለበት መሆኑንም ገለጠ። ተንኮል የአደባባይና የጓዳ ማንነትን መያዝ ፥ ባለሁለት መታወቂያ መሆን ነው። ተንኮል ለስላሳ አንደበት ሸካራ ተግባር መያዝ ነው። ተንኮል ቅዱስ የመባል ናፍቆት ቅዱስ የመሆን ግን ፍላጎት የሌለበት ነው። ተንኮል ነገሮችን በክፉ ትርጉም መመልከትና ሰውን ለማጋለጥ ኃጢአቱን መፈለግ ነው። ተንኮል ሌሎችን የሚያፋጅ መርዝ እየላኩ መልሶ በአስታራቂነት መሰየም ነው። ተንኮል ኮቴ ሳይሰማ መራመድና ነክሶ መኖር ነው። ተንኮል የበደለውንም ያልበደለውንም ሰው ለመጉዳት መፈለግ ነው። ተንኮል የሌሎች ሰላም የሚረብሸው ነው። ተንኮል እርስ መተማመን እንዳይኖር በሰዎች መካከል ጥርጣሬን የሚዘራ ነው። ተንኮል ያለበት ሰው የእግዚአብሔር ሰው ሊሆን እንዴት ይችላል? የእግዚአብሔር ሰው ብእሴ ሰላም ነው ፥ ተንኮለኛ ደግሞ ጭር ሲል የማይወድ ነው። የእግዚአብሔር ሰው ዋሽቶ የሚያስታርቅ ነው ፥ ተንኮለኛ ደግሞ ፈጥሮ የሚያጣላ ነው። የእግዚአብሔር ሰው ከባቴ አበሳ ነው ፥ ተንኮለኛ ደግሞ እንደ ጋኔን የሰውን ኃጢአት ሲመዘግብ የሚኖር ነው። የእግዚአብሔር ሰው ለማገዝ የሚፈልግ ነው ፥ ተንኮለኛ ደግሞ እንዴት ልጣለው የሚል ነው። ተንኮለኛ በተንኮሉ የሚመካ ነው።
ዛሬ በክርስቲያንነት የሚጠሩ ፥ በአባትነት የተሰየሙ ሳይቀሩ እኔ አድማ ክፍሌ ነው ፥ እኔ ያሰርኩት አይፈታም ፥ ነገር ያደግንብሽ ያሳደግንሽ እንኳን ደህና መጣሽ የሚሉ ንግግሮችን ሲናገሩ ስንሰማ ተንኮልን ከጌታ በላይ እያገለገሏት መሆኑን እንረዳለን።
የእውነተኛ እስራኤላዊ ልኩ ውጫዊ ሥርዓቱ ሳይሆን ውስጣዊ ቅንነቱ ነው። ይህን ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር፡- “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና” ብሏል /ሮሜ. 2፡28/። እውነት መቀመጫዋ ልብ እንደሆነ እንረዳለን። የእግዚአብሔር ሕዝብ መባልን እንደ ዜግነት የምንወስደው አይደለም። በውሳኔ የምናገኘው ነው። መገረዝም ለተገረዘው ልብ መግለጫ ካልሆነ አሳሳች ምልክት ነው። ነጭ ነጠላ ለብሶ ጥቁር ቂም ማሰብ ፥ እየተሳሳሙ መነካከስ እግዚአብሔር የሚወደው አይደለም።
“ናትናኤልም፡- ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው።” በርግጥም ግልጥ ሰው ነው። ግልጥ ሰዎች ከውስጣቸው ምንም የለም። እንደሚናገሩት ናቸው። ንግግራቸው የውስጣቸው መግለጫ እንጂ መሸፈኛ አይደለም። ለዚህ ነው ጌታ ተንኮል የሌለበት ያለው። ጌታ ጠባዩን ጭምር ስላወቀበት አብረኸኝ አልኖርህ እንዴት አወቅኸኝ? የሚል ድምፅ ነው ያሰማው። “ኢየሱስም መልሶ፦ ፊልጶስ ሳይጠራህ፥ ከበለስ በታች ሳለህ፥ አየሁህ አለው” አለው። እንኳን ጠባይህን የወደፊት መሻትህንም አውቃለሁ ማለቱ ነው። በበለስ በታች ቊጭ ብሎ ስለ መሢሑ ያጠና ነበር። ትንቢቱን በሁኔታ ፥ ሱባዔውን በስሌት እያሰላሰለ ነበር። ጌታችን ያወቀለት የኖረውን ጠባዩን ብቻ ሳይሆን መሻቱንም ነው።
ነቢዩ ዳዊት፡- “ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ” ብሏል /መዝ. 138፡16/። አንድ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ ያልተሠራውን ቤት ውስጣዊ ዓይኖቹ እንደሚያዩ እንዲሁም የሠራን እግዚአብሔር አስቀድሞ አይቶናል። የጠራው ብቻ ሳይሆን የሠራው ጌታ ሲናገረው ናትናኤል ከወዴት ታውቀኛለህ? አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አስቀድሞ ያውቀዋል። መሻቱንም ሊያረካ አጠገቡ ቆሟል። የዮና ልጅ ስምዖን በማለት እንኳን ጴጥሮስን አባቱንም እንደሚያውቅ ተናግሯል። አሁን ደግሞ የናትናኤልን ጠባዩንን ፍለጋውንም አወቀለት።
“ናትናኤልም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው” /ዮሐ. 1፡50/። ናትናኤል መሢሑን በእውነተኛ መልኩ ይጠብቀው ስለነበር ባገኘው ጊዜ ማንነቱን ነገረው። የመሻቱ መልስ ፥ የፍለጋው ማብቂያ የእርካታው ጥግ ሆኖ ሲመጣ በሙገሳ ተቀበለው። መምህር ሆይ አለው። በርግጥም ክርስቶስ በቃልም በሕይወትም የሚያስተምር መምህር ነው። ማንኛውም መምህር በሰሌዳ ሊያስተምር ይችላል። በሕይወት እያሳለፈ የሚያስተምር ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ከእርሱ የሚማሩም ሰላማቸው ይበዛል። እርሱ ሲያስተምራቸው ልባቸው ይቃጠልባቸው እንደ ነበር ሉቃስና ቀለዮጳ መስክረዋል /ሉቃ. 24፡32/። እርሱ የሚያስተምረውም በሥልጣን በመሆኑ ከጻሕፍትና ከፈሪሳውያን ይለያል /ማቴ. 7፡28-29/። በርግጥም ልዩ መምህር ነው። ናትናኤልን ጠባዩን ያወቀ ፥ መልካም ማንነቱን ያደነቀ ቅን መምህር ነው።
ናትናኤል “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” አለ። ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በእግዚአብሔር አብ ተመስክሯል። ናትናኤል የዮሐንስ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ይህን ያውቃል። የመጣውን ጌታ መቀበል እንጂ መፈለግ አብቅቷልና የእግዚአብሔር ልጅ ነህ አለው። ይህን ምስክርነት ወደፊት በመመስከር የሚሞገሰው ጴጥሮስ ነው /ማቴ. 16፡16/። ናትናኤል ግን ቀድሞ መሰከረ። ይህ ምስክርነት የሰማይ መገለጥ ነውና ናትናኤል አሁን ያለው በመንፈስ ቅዱስ ብርሃን ውስጥ ነው።
ዳግመኛም “የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። እስራኤልን የሚመራ ፥ የእስራኤል ታዳጊ መሆኑን ገለጠ። ወደ ኋላ እንደምናየው ደቀ መዛሙርቱ መሢሑ የሚመጣው ከሮማውያን ባርነት ነጻ አውጥቶን የዳዊትን ዙፋን ሊመሠርት ነው ብለው ያምኑ ነበር። ይህ ግንዛቤአቸው የተወለደውም በዘመነ መሳፍንት የተነሡ ታዳጊዎች እንደ መሢሕ ይታዩ ነበር። ከጠላቶቻቸው ነጻ አውጥተው በላያቸው ላይ ይነግሡ ነበር። ስለዚህ መሢሑ ይመጣል ሲባል የዳዊትን ዙፋን አስመልሶ በእስራኤል ይነግሣል የሚል እሳቤ ነበራቸው። በይበልጥ ናትናኤል ቀነናዊ ነውና የሮማ መንግሥት በትግል መውደቅ አለበት ብሎ የሚያስብ ነው። ይህ ሰው መሢሑ ምድራዊ ዙፋን የሚመሠርት ነው ብሎ ማመኑ ግድ ነው። ስለዚህ ጌታን የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው። ጌታ ቀጥሎ አሳቡን ከፍ ያደርግለታል።
“ኢየሱስም መልሶ፦ ከበለስ በታች አየሁህ ስላልሁህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ታያለህ አለው” ያ የሚበልጥ ነገር ምንድነው? ከበለስ በታች አየሁህ ካለው የሚበልጥ መገለጥ ፥ የእስራኤል ንጉሥ ከሚለው ናፍቆት የበለጠው ምንድነው? “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው” /ዮሐ.1፡52/። የናትናኤልን አሳብ ከፍ አደረገለት ፥ የሰማይ መከፈት ወይም የምሥጢር መገለጥ ይሆናል አለው። ምድራዊ ሠራዊት ያለኝ ምድራዊ ንጉሥ ሳይሆን ሰማያዊ ሠራዊት ያለኝ ሰማያዊ ንጉሥ መሆኔን ታያለህ አለው። ናትናኤል የእግዚአብሔር ልጅ ብሏልና ጌታ የሰው ልጅ መሆኑንም ተናገረ። ሰዎች የእግዚአብሔር ልጅ ሲሉት እርሱ ደግሞ የሰው ልጅ መሆኑንም ይናገራል። አምላክም ሰውም ነውና። በክርስቶስ ሰው መሆን መላእክት ተገልጠዋል። በጽንሰቱ ፥ በልደቱ ፥ በትንሣኤውና በዕርገቱ መላእክት የምሥራች ሰብከዋል። ጌታ ቢጣላ ሎሌ ይጣላል እንዲሉ ጌታ እግዚአብሔር ቢጣላን መላእክቱም ተጣልተውን ነበር ። ጌታ ቢታረቅ ሎሌ እንዲታረቅ ጌታ እግዚአብሔር ቢታረቀን መልእክቱም ታርቀውናል።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድን ፈጸምን። ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን።