የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቃና ዘገሊላው ተአምር

 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ስለ ቃል ዘላለማዊነት፥ መለኮታዊ ክብርና ልጅነት ይተርካል። የከበረው መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱ ክርስቶስን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ እንዲሁም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ወደ ጌታ እንደ መራ ይገልጣል። ከጌታችን ደቀ መዛሙርት ቢያንስ ስድስቱ ደቀ መዛሙርት እንዴት እንደ ተጠሩ ይገልጣል። ወንጌላዊው እነዚህ ላይ ብቻ አትኩሮት ያደረገው በምክንያት ነው። ስለ መጥምቁ ዮሐንስ እየተናገረ ስለነበር የመጥምቁ ዮሐንስ ተማሪዎች ስለነበሩት ስለ እነ እንድርያስና ጴጥሮስ ስለሌሎችም መናገር ስለነበረበት ነው። ዮሐንስ መጥምቅ ብዙ ደቀ መዛሙር ነበሩት። ሁሉንም ወደ ጌታ አልመራቸውም። አብዛኛዎቹ ከሳሾች ነበሩ። “እኛና ፈሪሳውያን የምንጦመው ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለምንድርነው?” የሚሉ ነበሩ /ማቴ. 9፥14/። ዮሐንስ ከሳሾቹን ትቶ መሢሑን የናፈቁትን ገራሞቹን ወደ ጌታ መራቸው። ከሳሽ ደቀ መዝሙር መሆን አይችልምና። ምክንያቱም ክርስቶስ የመጣው ሊከስስ ሳይሆን ስለሌሎች ጥፋት ሊከሰስ ነው።
ምዕራፍ አንድን የሚደመድመው የገሊላ ቃና ነዋሪ የነበረው ናትናኤል እንዴት እንደ ተጠራ በመግለጥ ነው። ምዕራፍ ሁለትም በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ በማለት ይጀምራል። ባለ አገሩን በመያዝ ወደ ገሊላ ቃና ሰርግ ጉዞ አደረገ። የትም ቦታ ስንሄድ ሁኔታዎች ምቹ እንዲሆኑ የአገሬውን ሰው መያዝ መልካም ነው። ለአገሩ ባይተዋር አንሆንም። የሚያዩንም እንደ ባዕድ ቆጥረው አያገልሉንም። ከተጠቀምነው በላይ የሆነ ክፍያ ውስጥ አንገባም። ወንበዴዎችም አይተናኮሉንም። ስለዚህ ጌታችን ለእኛ አብነት ለመሆን የገሊላ ቃና ነዋሪ የሆነውን ናትናኤልን ይዞ ወደ ሰርጉ ሄደ።
 ጌታችን ለናትናኤል የበለጠ ታያለህ ብሎት ነበር። የበለጠ ከሚያይበት ክስተት አንዱ የቃና ዘገሊላው ተአምር ነው። ናትናኤል የሮማን መንግሥት ከሚቃወሙ አደጋ ጣዮች አንዱ ነበር። በሕዝቡም ዘንድ እንደ ስውር አርበኛ ይታሰባል። ይህን ሰው ወደ መኖሪያው ጌታችን ይዞት የሄደበት ምክንያት አለው። ከአርበኝነት ይልቅ የሚበልጠው ደቀ መዝሙርትነት መሆኑን ለአገሬው ለማሳየትና የናትናኤልን ልብ ለመማረክ ነው። በቃና ዘገሊላ በተደረገው ተአምር ብዙዎች ተማርከዋል። ናትናኤልን የሚያዩትም የሚበልጠውን ጌታ እንደ ተከተለ አይተዋል። ናትናኤል ከአርበኝነት ወደ ደቀ መዝሙርነት ተብሎ ዘበት ውስጥ እንዳይገባ ጌታችን የሁሉን ኅሊና ጠበቀ።ናትናኤል አሳቡ ቢሞላና የሮማ መንግሥት ወድቆ የእስራኤል መንግሥት ቢመሠረት ፥ ጓዳ ገብቶ ችግርን የሚፈታ ፥ ከሐፍረት የሚያድን መንግሥት  ሊኖር አይችልም። ኢየሱስ ግን በደስታችን ደስ የሚለው ፥ ጓዳ ገብቶ ከሐፍረት የሚያድን ነው። ስለዚህ ናትናኤል ስለ ሕዝቡ ቀንቶ ከተመኘው አገዛዝ ይልቅ የክርስቶስ መንግሥትነት ይበልጣል።
 ጌታችን ናትናኤልን ይዞ ወደ መኖሪያ አገሩ የወሰደው ልቡን በፍጹም ለማሳረፍ ነው። ይህን የሚመስል ክስተት በጴጥሮስም እናያለን። ጌታችን ወደ ጴጥሮስ ቤት ሄደ። ጴጥሮስ ቤተሰቡን ትቶ የተከተለ ነው። ምናልባት ልቡ በናፍቆት እንዳይጎዳ ጌታችን የስብከቱን አቅጣጫ ወደ ጴጥሮስ ቤት አደረገና ወደ ቤቱ ገባ። በዚያም የጴጥሮስ የሚስቱ እናት በንዳድ ታማ ተኝታ አገኛትና ፈወሳት። ጌታ ባይደርስላት ሟች ነበረች። ጴጥሮስ ስለሌለ ይህች ሴት ልጇን ለማገዝ መጥታ ይሆናል። በየመሐሉም እንዴት ቤቱንና ትዳሩን ትቶ ይሄዳል ማለቷ አይቀርም። ስለዚህ ጌታችን ቤተሰባዊ ፍቅርን መጠበቅ ነበረበት። አማቱን በፈወሰ ጊዜ ተነሥታ አገለገለቻቸው /ማር. 1፥31/። በእውነትም ጴጥሮስ የተከተለው ሊከተሉት የሚገባውን ጌታ ነው እስክትል ተአምር አየች። በዚህም የጴጥሮስን ልብ ደግሞም ቤተሰቡን ጠበቀ። ወደ ዮሐንስና ወደ ያዕቆብ ቤት አልሄደም። እነዚህ ወጣቶች ናቸው። አባታቸውንም ጥለው ሲከተሉ ከብዙ ሠራተኞች ጋር ነው /ማር. 1፥20/። ስለዚህ አባታቸው አይጎዳም። ጌታችን የእኛንም የሌሎችንም ስሜት ያዳምጣል። ማኅበራዊ ሰላምንም ያስከብራል።
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ጋር ተመሳሳይነት አለው። ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ስለ ጋብቻ ጅማሬ ይናገራል፤ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለትም የመጀመሪያው ተአምር በቃና ዘገሊላ እንደ ተደረገ ይናገራል። ጋብቻን የመሠረተው የመጀመሪያውን ተአምር በሰርግ ቤት አደረገ። ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ከአዳም ጎን የተፈጠረችው መልሳ ሚስቱ እንደሆነች እናያለን። ይህ ያልተደገመ ክስተት ነው። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለትም ድንግል ፈጣሪዋን እንደ ወለደችው እናያለን። ይህም ያልተደገመና የማይደገም ክስተት ነው። በዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ላይ ሴት የሚለው ስም እንደወጣ እናነባለን /ዘፍ. 2፥23/። በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ላይም ጌታችን አንቺ ሴት በማለት እናቱን ሲጠራ እናያለን። እርሱ የሴት ዘር ነውና ሴት እያለ መጥቀሱ ግድ ነው። ይህ ትልቅ ምሥጢርን እንጂ ንቀትን የሚያሳይ አይደለም። በዘፍጥረት ሁለት ላይ አዳምና ሔዋን አይተፋፈሩም ነበር። በቃና ዘገሊላ ያሉ ሰርገኞች ግን ወይን ጠጁ አልቆባቸው አፍረዋል። አዳምና ሔዋንን ያለ ልብስ ጸጋን አልብሶ ያሳረፈ። የቃና ዘገሊላ ሰርገኞችንም ተአምር አድርጎ ከማፈር ያድናቸዋል። በየትኛውም ሰርግ የተጠራው እንግዳ ይስተናገዳል ፥ ይጋበዛል። ተጠርቶ የጋበዘው ግን ጌታችን ብቻ ነው። በሰርግ ቤት ሁሉ ሁካታውን ያያል ፥ ጉድለትን ያየች ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የዚያ ቀን ችግር በገንዘብ የሚወጡት አልነበረም ፥ ስለዚህ ልጇን ተአምር እንዲያደርግ ለመነችው። ከዐርባ ሦስት ቀን በፊት አባቱ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለት ለዓለም ገልጦታል። ከዐርባ ሦስት ቀን በኋላ  እናቱ ለዓለም ትገልጠዋለች። ከዐርባ ሦስት ቀን በፊት አባቱ እርሱን ስሙት ብሎ ነበር ፥ ከዐርባ ሦስት ቀን በኋላ እናቱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ ትላለች።
 የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ፥ ሁለት ታላላቅ ክፍሎች አሉት። ከቊጥር 1-12 በእመቤታችን ምልጃ ውኃው ወደ ወይን ጠጅ እንደ ተለወጠ ይናገራል። ከቊጥር 13-25 ስለ ሆሳዕናና የመጨረሻው ክስተት ይናገራል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ