“ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ” /ዮሐ. 2፥11/ ።
ብሉይ ኪዳንና አዲስ ኪዳን እንደ ሰምና ወርቅ ፥ እንደ ዋዜማና በዓል ፥ እንደ ጥላና አካል ፥ እንደ ምሳሌና እውነት ፥ እንደ ተስፋና ፍጻሜ ፥ እንደ ማጫና ሙሽርነት ፥ እንደ መርፌና ክር የተያያዙና የተሳሰሩ ኪዳናት ናቸው ። ወርቁ ከሌለ ሰሙ ቀላጭ ፥ በዓሉ ከሌለ ዋዜማው ሁካታ ፥ አካሉ ከሌለ ጥላው ምትሐት ፥ እውነቱ ከሌለ ምሳሌው ጉንጭ አልፋ ፥ ፍጻሜው ከሌለ ተስፋው ሐሰተኛ ፥ ሙሽራው ካልመጣ ማጫው መሳደቢያ ፥ ክሩ ከሌለ መርፌው መውጊያ እንደሆነ አዲስ ባይመጣ ብሉይ ኪዳን እንዲህ በሆነ ነበር ። በብሉይ ኪዳን ክርስቶስን የሚመስል ሙሴ ነው ። ወንጌላዊውም ሙሴን በአንጻራዊነት በማቆም ክርስቶስ የበለጠውን ኪዳን እንዳቆመ ተናግሯል ። “ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” ብሏል /ዮሐ. 1፥17/። ራሱ ሙሴም “አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን፦ እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ” ብሏል /ዘዳ. 18፥15/ ። የእስራኤል ልጆች በኮሬብ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ክብር መቋቋም ስላቃታቸው እግዚአብሔር በሥጋ እንደሚገለጥ ሙሴ እየነገራቸው ነው ። የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ባርነት ነጻ መውጣት የመዳን ፍጻሜ እንደሆነ እንዳያስቡ ከነፍስ ባርነት ነጻ የሚያወጣው ጌታ እንደሚመጣ ገለጠላቸው ። የእሳት ነበልባሉን ፥ የኮሬቡን ግርማ አስበው እንዳይደነግጡ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል አላቸው ። ስለዚህ የሙሴን ሕይወትና ኑሮ ሲያስቡ ክርስቶስን ለማወቅ አይቸገሩም ። ጥቂት ማነጻጸሪያዎችን ብናይ ፡-
ሙሴ
|
ክርስቶስ
|
|
1
|
ፈርዖን ሕጻናትን በሚገድልበት ዘመን ተወለደ
|
ጌታችንም ሄሮድስ ሕጻናትን በሚፈጅበት ዘመን ተወለደ
|
2
|
ስለ ሙሴ ሲነገር ስለ እናቱ ብቻ ተነግሯል
|
ጌታችንም ከሴት ዘር ተወልዷል
|
3
|
ካህን ፥ መስፍን ፥ ነቢይ ነበረ
|
ጌታችንም እነዚህን ስሞች ወርሷል
|
4
|
በፋሲካው በግ ሕዝቡን ነጻ አውጥቷል
|
ታርዶልን አድኖናል
|
5
|
ባሕረ ኤርትራን አሻግሯል
|
ባሕረ ሞትን አሳልፎናል
|
6
|
ብሉይ ኪዳንን መካከለኛ ሆኖ ተቀብሏል
|
አዲስ ኪዳንን መሥርቷል
|
7
|
በትሩ በዘመኑ ሁሉ አልተለየውም
|
መስቀሉን ለአንድ ቀን አልዘነጋም
|
8
|
አንድ ጊዜ ባሕረ ኤርትራን አሻገረ
|
አንድ ጊዜ ድኅነተ ዓለምን ፈጸመ
|
9
|
ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጦሞ ሕገ ኦሪትን ተቀብሏል ።
|
ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጦሞ ሕገ ሐዲስን መሥርቷል ።
|
10
|
መቃብሩ አልተገኘም
|
መቃብሩ ባዶ ነው
|
11
|
ከሞት ተነሥቶ በደብረ ታቦር ታይቷል ።
|
ከሞት ተነሥቶ በደብረ ዘይት በኩል ሽቅብ አርጓል ።
|
ሙሴና ጌታችን ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን ተነጻጻሪም ጎን ነበራቸው ። ሙሴ ከድሃ ቤት ተወልዶ ከፍ ካለ ቤተ መንግሥት አድጓል ። ጌታችን ግን ከዙፋን ወርዶ በበረት ተወልዷል ። የሙሴ እናት እየተከፈላት ጡት አጥብታለች ፥ እመቤታችንም የፍጥረቱን መጋቢ አጥብታለች ። በዓለም ላይ ስላጠባች የተከፈላት እናት የሙሴ እናት ናት ፥ ልጇን በማጥባቷ የምትደነቅም እመቤታችን ድንግል ማርያም ናት ። ሙሴ ያለ ችግር በቤተ መንግሥት ቢኖርም የወገኖቹ ሥቃይ ግን አሳዘነው ፤ ስለዚህ ስደት መረጠ ። በትጉሃን መላእክት ተከቦ ይመስገን የነበረው የእግዚአብሔር ልጅም የእኛ ጉስቁልና ከዙፋን ሳበው ። ሙሴ ስለ ክርስቶስ ክብርን ናቀ ። ክርስቶስም ስለ ሰው ልጆች ክብርን ናቀ ። የሙሴ እናት የዓላማና የእምነት እናት እንደ ነበረች ፥ እመቤታችንም የዓላማና የእምነት እናት ናት ። ሙሴ እስራኤላዊ ቢሆንም በፈርዖን ልጅ ግብጻዊም ነበረ ። ጌታችንም ሰማያዊ ሳለ ምድራዊ ሆኗል ።
ሙሴ እግዚአብሔር ከተገለጠለት በኋላ በፈርዖን ፊት ቆመ ፥ ጌታችንም በዮርዳኖስ ምሥክርነትን ከተቀበለ በኋላ በጠላት በግልጥ ተፈተነ ። ሙሴ በዓለም ገናና በነበረው በፈርዖን ፊት በትር ይዞ ቆሟል ። ጌታችንም ዓለሙን በኃጢአት በያዘው በጠላት ፊት መስቀል ተሸክሞ ድል ነሥቷል ። ሙሴ ፈርዖን ሕዝቡን እንዲለቅ የመጀመሪያውን ተአምር ውኃውን ወደ ደም ለውጧል ። ጌታችን ግን ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምር ሠርቷል ። ሙሴ የሚጠጣውን ውኃ የማይጠጣ በማድረግ ተአምር ሠራ ፥ ጌታችንም ግን በሠርግ ላይ የማይጠጣውን ውኃ ወደ ወይን ጠጅ በመለወጥ ተአምር ሠራ ። የሙሴ ሕግ ሁሉን ኰንኖ የማይጠጡ አደረገ ፥ የጌታችን ጸጋ ግን ሁሉን አክብሮ ባለ ዋጋ አደረገ ። ጌታችንና ሙሴ የመጀመሪያውን ተአምር ያደረጉት በውኃ ላይ በመሆኑ ሲያመሳስላቸው በውጤቱ ግን የጌታችን እንደሚበልጥ እንረዳለን ። የሙሴ ተአምር የመጀመሪያ መቅሰፍትም ነው ፥ የጌታችን ተአምር ግን ታላቅ በረከት ነው ። በሙሴ ተአምር ፈርዖን ደነገጠ ፥ ግብጻውያን ታወኩ ፥ እስራኤል ግን ተመኩ ። በጌታችን ተአምርም ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ አመኑ ፥ ጠላትም ድል ተነሣ ።
ቃና ዘገሊላ ወደኋላ ወደፊት እየሄደ ምሥጢርን የሚያገናኝ ትልቅ ተአምር ነው ። ቃና ዘገሊላ ገነትን ደግሞም ቀራንዮን የሚያስታውስ ነው ። ምልጃ ተአምርን ፥ ተአምርም ክርስቶስን ማመን እንደሚያስገኝ ቃና ዘገሊላ ያስረዳናል ። ወንጌላዊው በምዕራፍ አንድ ሙሴን ከሕግ መሰጠት ጋር አነሣው ። በምዕራፍ ሁለት በምሥጢር ከመጀመሪያው ተአምር ጋር ያገናኘዋል ።