የትምህርቱ ርዕስ | የኢየሱስ እናት

“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ” /ዮሐ. 2፥1/።
ሦስተኛ ቀን በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ነገሮችን ያሳስባል ። ሦስተኛ ቀን አዝርእትና አትክልት እንደ ወገኑ ያብቅሉ ተብሎ ትእዛዘው የተሰጠበት ቀን ነው /ዘፍ .1፥11/ ። አብርሃም ይስሐቅን በኅሊናው ከሠዋው ከሦስት ቀን በኋላ በትንሣኤ አገኘው /ዘፍ. 22፥4/ ። የእስራኤል ልጆች የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ ተጉዘው ለእግዚአብሔር እንዲሠዉ ታዘዙ /ዘጸ. 3፥18/። ያ የሦስት ቀን መንገድ የሚጀምረው የኤርትራን ባሕር ከተሻገሩ በኋላ ነው ። የኤርትራ ባሕር የሞት ምሳሌ ነው ። ስለዚህ የክርስቶስን መሥዋዕትነት ያመለክታል ፤ ሦስት ቀን ደግሞ ትንሣኤውን ያሳያል ። የእስራኤል ልጆች ከሦስት ቀን  በኋላ ለእግዚአብሔር የሠዉት በዕረፍት ነው ። በ12 ምንጮችና በሰባ የዘንባባ ዛፎች ሥር ዐረፉ ። በዚያ ውስጥ ትልቅ አምልኮ ነበረ ። ትልቁ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ሳይሆን የሰጠንን ማሰብና ማክበር ነው /ዘጸ. 15፥27/። የሦስቱ ቀን መንገድ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ያመለክታል ። በ12 ምንጮችና በሰባ ዛፎች ሥር መቀመጥ በ12 ሐዋርያትና በሰባ አርድእት አገልግሎትና መጻሕፍት ማረፍን የሚያመለክት ነው ። ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጦሞ ከተመለሰ በኋላ በሦስተኛው ቀን በቃና ዘገሊላ ተአምራት አደረገ ።
ይህ ሦስተኛ ቀን ከእሑድ የተቆጠረ ነው ። ስለዚህ ማክሰኞ ሰርጉ ላይ ተገኘ ። ከገዳመ ቆሮንቶስ እንደ ተመለሰ አንድ ቀን እንኳ ሳያርፍ ወደ ዮሐንስ ሄደ ። ወደ ሱባዔ ከመግባቱ በፊትና ከሱባዔ ከወጣ በኋላ ወደ ዮሐንስ መምጣቱ ውሳኔዎችን ስንወስን ከመንፈሳውያን አገልጋዮች ጋር መማከር እንዳለብን ሊያስተምረን ነው ። ሱባዔ ምክር የማያስፈልገው ይመስለን ይሆናል ? ጌታችን ግን ምክር ሳያሻው ይህን ያደረገው ለእኛ አብነት ለመሆን ነው ። አንዳንዴ ለመንፈሳውያን አማካሪዎች ችግሩን ወይም ጉዳዩን እንነግራለን ። ውጤቱን ወይም ፍጻሜውን ለመንገር ግን እንረሳለን ። እንደሚያስቡ እንዘነጋለን ። ጭንቀትን ተናግሮ የምሥራቹን መደበቅ ተገቢ አይደለም ። ደቀ መዛሙርቱን ከመረጠ በኋላ በቀጥታ የሄደው ወደ ሰርግ ነው ። እርሱ አገልግሎትንና ማኅበራዊ ቀረቤታን በታላቅ ጥንቃቄ ያደርግ ነበር ። ወደ ቃና ዘገሊላ ሰርግ የሄደውም ጥሪውን ለማክበር ብቻ ሳይሆን ጉድለትንም ለመሙላት ነው ። መፍትሔ ይዞ መጓዝ ከአንድ አገልጋይ የሚጠበቅ መሆኑን ያሳያል ። አገልጋይ ተቀባይ ሳይሆን ሰጪ ነው ። ምድራዊውን ነገር ከምእመናን ቢቀበል እንኳ የተቀበለው የእግዚአብሔርን ድርሻ ነው ። ዳግመኛም የዘላለሙን ነገር የሚሰጥ ስለሆነ ጊዜያዊውን ገንዘብ ከምእመናን ቢቀበል ከቊጥር የሚገባ አይደለም ።
“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች”  ይላል ። ቃና በሚል መጠሪያ የሚታወቁ ሁለት ከተሞች አሉና የገሊላ ቃና በማለት ይለያታል ። አንደኛዋ ቃና በኤፍሬም ነገድ ውስጥ ያለች ስትሆን ይህችዋ ቃና ግን በአሴር ነገድ ሥር ያለች ናት ። ይህች የገሊላ ቃና ሰሜናዊ የእስራኤል ግዛት ናት ። ከናዝሬት ሰባት ኪ.ሜ ርቃ የምትገኝ አነስተኛ መንደር ናት ። በዚህች በቃና ሁለት ተአምራት በጌታችን ተደርገዋል ። የመጀመሪያው ውኃው ወደ ወይን መለወጡ ሲሆን ሁለተኛው የቅፍርናሆም ሹም ልጅ መፈወስ ነው /ዮሐ. 4፥46-54/ ። ጌታ እነዚህን ተአምራት ካደረገ በኋላ ፈጥኖ ከከተማዋ ይወጣ ነበር ። “ተአምራቱ እንዴት ነበር ?” ብሎ ቃለ መጠይቅ አያደርግም ነበረ ። ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ከለወጠ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ሄደ ። ብላቴናውን ከፈወሰ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ ። ድንቆች በተደረጉበት ከተማ ከመቆየት ፈጥኖ መውጣት እንደሚገባ ሲያስተምር ነው ። ዛሬ ተፈወሱ የሚባሉ ሰዎች በቃለ መጠይቅ ልባቸው ሲደርቅ እናያለን ። ተአምር አድራጊውን ማክበርና ትልቁን ተልእኮ ወንጌልን ስለመስበክ ማሰብ አስፈላጊ ነው ። ሰው ምልክቱ ላይ ከቀረ ዋናውን ሳያገኝ ይቀራል ።
“የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች”  ይላል ። የጌታችን እናት በዚያ መኖሯ የሚያመለክተው ሰርጉ የቤተሰብ መሆኑን ነው ። እመቤታችን ብዙ ቤተሰቦች ነበሯት ። ጌታም በዚህ ቤተሰብ መካከል አድጓል ። ቃና ዘገሊላና ቀራንዮ ተዛማጅነት አላቸው ብለናል ። በቀራንዮ የተገኙትን ወንጌላዊው ይጠቅሳል ። “ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር” ይላል /ዮሐ. 19 ፥ 25/ ። ዮሐንስ የጌታን ልብስ ዕጣ ሲጣጣሉበት አዝኖ ከተረከ በኋላ በመስቀሉ ሥር ስለነበሩት ታማኞች ደግሞ መዘርዘር ጀመረ ። ሁሉም ክፉ አይደለም ። ስለጠሉን ሳይሆን ስለሚወዱን ፥ ስለ ወጉን ሳይሆን ቊስላችንን ስላጠቡልን ማሰብ መልካም ነው ። በቀራንዮ ከተገኙት ወዳጆች ውስጥ የእመቤታችን እህት የቀለዮጳ ሚስት የሆነችው ማርያም ተገኝታለች ። ማቴዎስና ማርቆስ የያዕቆብና የዮሳ እናት እያሉ ይጠሩአታል /ማቴ. 27፥56፤ማር. 15፥41/። ዮሐንስ ግን የእመቤታችን እህትና የቀለዮጳ ሚስት እያለ ይጠራታል /ዮሐ. 19፥25/ ። ስለዚህ የቃና ዘገሊላው ሰርግ የእመቤታችን እህት የቀለዮጳ ሚስት ቤት ነበረ ። ታዲያ እንዴት ማርያም ልትባል ቻለች ? በአንድ ቤት ለሁለት ሴት ልጆች ማርያም ተብሎ ይሰየማል ወይ ? ቢሉ እመቤታችን ማርያም የብጽአት ልጅ ሁና ለእግዚአብሔር የተሰጠች በመሆኗ ሁለተኛዋን ልጅ የመጀመሪያዋን ለማስታወስ ማርያም ብለው ሰይመዋል ። ይህ የተለመደ የአይሁዳውያን ባህል ነው ። በቃና ዘገሊላ በጉድለታቸው የተገኘላቸው ጌታ በተሰቀለ ጊዜ እነርሱም ኀዘናቸውን ለመግለጥ ተገኝተዋል ። ኀዘናቸውን ለመግለጥ መገኘት ብቻ ሳይሆን ከቅዱሳን ሴቶች መካከል ሆነው ጌታን ተከትለውታል ።
እመቤታችን ከጌታ ሌላ ልጆች አሉአት የሚሉ ወገኖች የሚጠቅሱት የአይሁድን ሐሜት ነው ። አይሁድ የጌታን ጥበብ ባዩ ጊዜ ፡- “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?” ብለዋል /ማቴ . 13፥55/ ። እርሱ ግን የጸራቢ ልጅ አይደለም ። በሰማይና በምድር አባቱ አንድ ነው ። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ። ወንድሞቹ የተባሉት ያዕቆብና ዮሳ የእመቤታችን የእህት ልጆች ናቸው /ማቴ. 27፥56፤ማር. 15፥40፤47፤ 16፥1/ ። አዎ ወንድሞች ለመባል መብቱም አላቸው ። የአክስት ልጆች ናቸውና ። ታዲያ ታናሹ ያዕቆብና ይሁዳ የጌታ ደቀ መዛሙርት ናቸው ። ሁለቱም መልእክታት ጽፈዋል ። በመግቢያቸው ላይም ያቀረቡትን እንመልከት። ያዕቆብ፡-  “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን” በማለት ሰላምታ ይጀምራል /ያዕ. 1፥1/ ። አብሮ ያደገ ፥ የሥጋ ዘመድ ቢሆንም ጌታን ግን በአምላክነቱ ክብር አይቶ ባሪያው ነኝ አለ እንጂ ወንድሙ ነኝ አላለም ። ይሁዳም ሲጀምር ፡- “የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ”  ይላል /ይሁዳ. ቊ. 1/ ። ይሁዳ በያዕቆብ ወንድምነት ሲኮራ በቀጥታ የድንግል ማርያም ልጅ ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ ወንድም በማለት ይኮራ ነበር ። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ በማለት በልዩነት ይናገራል ። አባቶች ስለ እመቤታችን ዘላለማዊ ድንግልና የሚናገሩት ፡- “በአምላክ ዙፋን ፍጡር አይቀመጥም” በማለት ነው ። የድንግል ማኅፀን አምላክ ያረፈበት ዙፋን ነው ። በዚህ ዙፋን ፍጡር አይቀመጥም ። ይህ መርሕ ለብዙ ነገር ይጠቅማል ።
የቃና ዘገሊላው ሰርግ ብዙ ነገሮችን ይገልጣል ። እመቤታችን ማርያም በዚያ ሰርግ ቀድማ ተገኝታለች ። ቀድማ መገኘቷ የዘመድ ሰርግ ስለነበረ ነው ። ጉድለቱንም ማወቋ ቤተኛ ስለነበረች ነው ። በቃና ሰርግ የነበሩት ሰርገኞች በቀራንዮም ተገኙ ። እውነተኛውን ወይን ደሙን ለዓለም ሲሰጥ ተመለከቱ ። ያን ጊዜ አላመኑበትም ነበር ። አሁን አመኑበት ። ቀራንዮ ቢገኝ የሚያምረው ጴጥሮስ ነበረ ፥ ግን መግደላዊት ማርያም ተገኘች ። ቀራንዮ የተሰቀለውን ጌታ ሊረዱት አይችሉም ። እናቱን ግን ደግፈው ነበረ ። እስከ መቃብሩ ተከትለው የተቀበረበትን ቦታ ያዩት እነዚያ የቃና ሰርገኞች ናቸው /ማር. 15፥47/።
“በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ፥ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች”  ይላል ። በሠርግ ላይ ስለ ሙሽራ እንጂ ስለ እድምተኞች አይወራም ። ዮሐንስ ግን ስለ ችግሩ ሳይሆን ስለ መፍትሔው በመናገር ጀመረ ። ከችግሩ ስንነሣ መፍትሔውን ማመን ይከብደናል ። ከመፍትሔው መነሣት ግን ችግሩን ያቀላል ። የቃና ዘገሊላ ሰርግ የገጠመው ችግር ባለጠጋ የሚሸፍነው አይደለም ። ገንዘብ አሁን ሁሉን ነገር አያስገኝም ። አሁን በዚህች ሰዓት አንድ ሺህ ሰዎችን ሊያስተናግድ የሚችል ወይን ጠጅ ማግኘት አይቻልም ። የእግዚአብሔር ተአምራት ብቻ ሊመልሰው የሚችል ጥያቄ ነበር ። ጉዳያችን ከጠቢባንና ከባለጠጎች ችሎታ በላይ ከሆነ እግዚአብሔር ይመስገን ። ሰው የማይችላቸው ችግሮች ባይኖሩ አማንያን በምድር ላይ ያንሱ ነበር ። ተስፋው ከምድር የተቆረጠ ጉዳይ ወደ ሰማይ ለመመልከት ጉልበት ይሆናል ። ወንጌላዊው ዓላማው ወይን ጠጅ ስለማለቁ ለመናገር አይደለም ። በተአምራት መሙላቱን ለመንገር ነው ። አለቀ የወረኞች ርእስ ነው ። ሙላት ግን የወንጌላውያን ርእስ ነው ። ወደቀ የአጋንንት ርእስ ነው ። ተነሣ ግን የቅዱሳን ዜና ነው ። የማለቅ ዜና በአጋንንት ዘንድ የደስታ ርእስ ነው ። የሙላት ርእስ ግን የመላእክት ዝማሬን የሚያቀጣጥል ነው ። በአንድ ኃጢአተኛ መመለስ በሰማይ መልእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ ይሆናልና ። የምስጋና ቃል ከአፋችን ሲወጣ መላእክት ይቀበሉናል ። ዝማሬ ሲቀጣጠል በረከት ይለቀቃል ። የእኛ ድርሻ ማመስገን ነው ፥ የእግዚአብሔር ድርሻ መሙላት ነው ።
እግዚአብሔርን እያልነው ያለነው አድርግልን ሳይሆን እንዴት ማድረግ እንዳለበት እናማክረዋለን ። እርሱ ግን ሁሉ መንገዱ ፥ የተዘጋ ደጃፍ የማይመልሰው ነው ። ቢሻ በየብስ ፥ ቢሻ በባሕር ተራምዶ ይመጣል ። በዚህ ነው የሚመጣው ተብሎ የተሰመረ መስመር ፥ መታወቂያ እግር ፈለግ የለውም ።
ሰርግ ገነትን ያስታውሳል ። አዳምና ሔዋንን በገነት የዳረ እግዚአብሔር ነው ። በሰርጉ ላይ ቢጋብዙት ትክክል ነው ። የተባረከው የአዳምና የሔዋን ትዳር የቆየው ከእግዚአብሔር ጋር ፍቅር እስከነበሩ ድረስ ነው ። የጋራ ፍቅር ያልቃል ፥ አንድ የሚያደርገን የክርስቶስ ፍቅር ነው ። በገነት ጋብቻን የመሠረተ ጌታ አሁን ደግሞ ለመባረክ መጣ ። ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ብሎ የመጀመሪያውን በረከት የሰጠው አምላክ አሁን ደግሞ የመጀመሪያውን ተአምር በሰርግ ቤት አደረገ ። ሰርግ ቀራንዮን ያስታውሳል ። ቀራንዮ ለክርስቶስ ሞት ለእኛ ግን ሰርግ ነበረ ። ለእርሱ ታላቅ መከራ ለእኛ ግን ታላቅ ደስታ ነበረ ። እርሱ የተተወበት እኛ ግን የተገኘንበት ነው ። ሰርግ ምጽአትን የሰማዩን ግብዣ ያስታውሰናል ። የመጨረሻ ወዳጆች የሚጠሩት ትልልቅ ግብዣዎች እራት ላይ ይደረጋሉ ። የመጨረሻው እራትም በሰማይ ይጠብቀናል ። በዚያ ቀን ሁላችንም ሙሽሮች ነን ። ከሙሽራው ተነሣ አንድ እንሆናለን ። በጉ ብዙ ሙሽሪቶች የሉአትምና አንድ ሆነን ልንጠብቀው ግድ ነው ።
የቃናው ሰርግ ደጋሾቹ ምስኪኖች መሆናቸውን ያሳያል ። የምስኪኖች ድግስ ደግሞ ሰው መመጠን አያውቅም ። ድሃ ይሉኝታ አለውና በብዛት ይጠራል ። ባለጠጎች ግን ከሚወልዱት ጀምሮ የተመጠነ ነው ። ይሉኝታ ቢስ ለመሆን ባለጠጋነት ይረዳል ። ባለጠግነት ቢያጠፉም ብዙ ወቀሳ የሌለበት ነው ። ባለጠጋ በቃል ሲደናቀፍ ሁሉ ይጠግንለታል ፥ በመንገድ ሲወድቅ ሁሉ እኔን ያስቀድመኝ ይልለታል ። ሐሰተኛ ፍቅርን እንደ ካባ ስለለበሰ ባለጠጋ ይሉኝታ የለውም ። አንዳንዴ ባለጠጎች ድሆችን የፈጠሩ ያህል ይሰማቸዋል ። ይህ የባለጠግነት አደገኛው ገጽታ ነው ። ባለጠጎች ልጆቻቸው የተመጠኑ ድግሳቸውና የሚጠሩትም እድምተኛ የተመጠነ ነው ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊቆጠር ነው” ሲባል አንድ ልዕልት “የጨዋዎቹ ልጆች 500 እንሞላ ይሁን?” አሉ ይባላል ። ባለጠጎች እንዲህ ሊያስቡ ይችላሉ ። ድሆች ከድግሱ ይልቅ ማኅበራዊ ኑሮአቸው ያሳስባቸዋል ። ጌታችን የመጣው በእነዚህ በድሆች መልክ ነው ። የኖረውም የባለጠጎችንና የመኳንንትን ድግስ ሲባርክ ሳይሆን የድሆችን ችግር ሲካፈል ነው ። በዓለማችን ላይ ያሉት ባለጠጎች ከ17 ፐርሰንት በላይ አይደሉም ። ጌታ ግን አብዛኛዎቹን ድሆች አድራሻ አድርጎ መጣ ።
ጌታችን በሚጠሩት ስፍራ አክብሮ ይገኛል ። የማርያም ልጅ ብለው ጠሩት ሲመለስ ግን የእግዚአብሔር ልጅም እንደሆነ አወቁ ። በዝምድና ጠሩት ሲመለስ ግን አምላክ መሆኑን አወቁ ። በጥቂት እውቀታቸው ጠሩት ፥ ሲመለስ ግን ከመረዳት በላይ የሆነውን እግዚአብሔርነቱን አወቁ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም