የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአርምሞ ትሩፋቶች

– ቃሉን ማሰላሰል
ከአርምሞ ትሩፋቶች አንዱ ቃሉን ማሰላሰል ነው ። የእግዚአብሔር ቃል ለዓለም መገኘት ምክንያት የሆነ ፥ ዘመናትን የተሻገረ ፥ የማለፍን ሥርዓት ተቋቊሞ ለዘላለም የሚኖር ነው ። ምእመናንን እስከ ሰማይ ለመምራት ብቁ የሆነ ፥ ዘላለማዊ ርስትን የሚያደላድል መሪና የሚያበለጽግ ቃል ነው ። እግዚአብሔር በቃሉ መናገሩ የምሕረቱ መገለጫ ነው ። እግዚአብሔር ዝም ያለበት ዘመን ለሕዝቡ አስጨናቂና የቅጣት ዘመን ነበር። ይህ ዘመን በነቢዩ በሳሙኤል ዘመን ተከሥቶ ነበር /1ሳሙ. 3፥1/ ። ከሚልክያስ በኋላም ለአራት መቶ ዓመታት ነቢያት አልተነሡም ነበርና ዘመኑ በምድረ በዳ የተመሰለ ነበር ። ዮሐንስ መጥምቅ ይህን ምድረ በዳ በድምፅ ስለሞላ የምድረ በዳው ድምፅ ተብሏል /ዮሐ. 1፥23/ ። እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚያመጣው ትልቅ ቅጣትም ቃሉን ማጣት ነው /አሞጽ. 8፥11/። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል ትልቅ በረከታችን ነው ።
ይህ ቃል ይነበባል ፥ ይጠናል ፥ ይሰላሰላል፥ ከሕይወት ጋር ይዛመዳል ። ማሰላሰል የሚባለው ቃሉን የምንመገብበት ሦስተኛ የአመጋገብ ደረጃ ነው ። እርሱም የሚገኘው በጽሞና ወይም በአርምሞ ነው ። ማሰላሰል ቃሉን በሕይወታችን ሕያው ማድረግ ነው ። በማሰላሰል ውስጥ ያለንበትን ሁኔታ በቃሉ እናያለን ፥ ለንስሐ እንነቃቃለን ፥ ልናደርገው ሲገባን ያላደረግነውን መልካም ነገር ለማድረግ ውሳኔ እናስተላልፋለን ። በማሰላሰል ውስጥ የበግ ባሕርያችንን እናሳያለን ። በግ የበላውን መልሶ ያመነዥጋል ። የሚያመነዥገው በጸጥታው ሌሊት ነው ። በማመንዠግ ውስጥ የሚወገደውን ያስወግዳል ፥ የሚያስፈልገውን አልሞ ያስገባል ። ማሰላሰል የጸጥታ ጊዜ ይፈልጋል ። በማሰላሰል ውስጥ የሚወገደውን ማስወገድ ፥ የሚያስፈልገውን ማላም ይገባል ። የጽሞና ሕይወት ከስህተት ትምህርቶች ያድናል ። ግልብልብ ካለ የትምህርት ንፋስ ይጠብቃል ። ምእመናን የአርምሞ ሕይወትን መለማመድ ካልቻሉ መሬት የቆነጠጠ ክርስትና ሊኖራቸው አይችልም ። በብሉይ ኪዳን የሚበሉ እንስሳት ሁለት መስፈርት ነበራቸው ። የመጀመሪያው ሸሆናቸው ክፍት መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማመንዠጋቸው ነው ። ሸሆናቸው ክፍት መሆኑ መሬት መቆንጠጥ ያስችላቸዋል፥ ማመንዠጋቸው ደግሞ መርዛም ነገርን ከደማቸው ጋር ከማዋሐድ ያድናቸዋል ። በሦስተኛ ደረጃ ሣር በል በመሆናቸው ገድለው የሚበሉ አይደሉም ። ገዳይ መብል መሆን አይችልም ። የአርምሞ ሕይወት ያላቸው ምእመናን ለሌላው ጥጋብ ይሆናሉ ። የመሥዋዕትነት ሕይወት ለመኖርም ቊርጠኛ ናቸው ። በብሉይ ኪዳን መሠዊያ ላይ የሚሠዉት እነዚህ እንስሶች ናቸውና ። ስለዚህ አርምሞ የቆነጠጠ ክርስትና ፥ መርዛም ትምህርትን ያራቀ አማኝነት ፥ ሌላውን የማይገድል ማንነት ያስገኛል ።
 ደጋግመን የምናስበውን እርሱን እናደርገዋለን ። ቃሉንም ደጋግመን ስናሰላስል ቃሉን መኖር እንችላለን ። ከሙሴ ቀጥሎ እስራኤልን ለመምራት አደራ የተሰጠው ኢያሱ ለመሪነት ብቃት የሚሰጠው ቃሉን ማሰላሰል እንደሆነ እግዚአብሔር አምላክ ነግሮታል ፡- “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም” /ኢያ. 1፥8/ ። ኢያሱ መሪነቱን ሲረከብ የሙሴ መጻሕፍት ተጽፈው በእጁ ነበሩ ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚናገረው በተጻፈው ቃሉ በኩል ነው ። “እግዚአብሔር ለሕዝቡ፥ በውስጥዋም ለተወለዱት አለቆችዋ በመጽሐፍ ይነግራቸዋል” ይላል /መዝ. 86፥6/ ። ኢያሱ መሪ በመሆኑ መሪ ተስፋው ቶሎ ሊጎዳ ይችላል ፥ የእግዚአብሔር ቃል የተስፋ ቃል ነውና ተስፋ ይሰጠዋል ። መሪ ብቸኝነት ይሰማዋል ፥ የእግዚአብሔር ቃል የእግዚአብሔርን አብሮነት ያበሥራል ። ኢያሱ ይህን የተጻፈውን ቃል እንዲያስብ ተነግሮታል ። ቃሉን በማሰብ ውስጥ ምስክርነት ፥ መታዘዝ ፥ የመንገዶች መከፈት ፥ መከናወንም ይሆናል ።
ነቢዩ ዳዊትም ፡- “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል ። ቃሉን የማሰላሰል እንቅፋቶችን መጀመሪያ ይጠቅሳል ። በወዳጅ ላይ ክፉ ምክር የሚመክሩ እንደ አኪጦፌል ያሉ ሰዎች የመጀመሪያዎቹ እንቅፋት ናቸው /2ሳሙ. 15፥34/ ። ለስህተት ቅርብ በሆኑ ሁኔታዎች እንደ አምኖን መጋለጥም ሁለተኛው እንቅፋት ነው /2ሳሙ. 13/። ሦስተኛው ሳቅ ፥ ስላቅ ከሚወዱ ጋር ጊዜን ማባከን የቃሉ እንቅፋት ነው ። መሄድ ፥ መቆምና መቀመጥ የሚሉ ድርጊቶች ተጠቅሰዋል ። መሄድ አፈጻጸም ነው ። መቆም ለአደጋ ተጋላጭነት ነው ። መቀመጥ ጊዜ መስጠት ነው ። ከእነዚህ ነገሮች የምንድነው ቃሉን በማሰላሰል ነው ። ቃሉን በቀንና በሌሊት የሚያሰላስል ከአድማ ሕይወት ይድናል ። አይቶ ይረግጣል እንጂ ረግጦ አያይም ። ጊዜውንም ለሚያንጹት ነገሮች ይሰጣል ። የጽሞና ሕይወት ማጣት ለክፎች ምክር ፥ ለስህተት ውሳኔ ፥ ዋዘኞችን ለመወዳጀት ምክንያት ይሆናል ። ብዙ ጊዜ ቃሉን የማንሰማው የማናሰላስለው ሥራ ፥ ሥራ እያልን ነው ። ነገር ግን የምንሠራው ሁሉ የሚከናወንልን ቃሉን በማሰላሰል ውስጥ እንደሆነ ተጽፎልናል ። አንድ ወጣት በአንድ ወቅት ደህና ነህ ወይ ? ብዬ ብጠይቀው ፡- “ቃሉን ስማር ደህና ነኝ” በማለት መልሶልኛል ። ችግሩንም መፍትሔውንም ስላወቀ ብዙም መልስ አልሰጠሁትም ።
 በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ ለመጽናት ቃሉ ያስፈልጋል ፡- “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው” /ዘዳ. 6፥6-9/
 የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ጸሎት ስንመለከት በእግዚአብሔር ቃል እውቀት የበረታች እናት መሆኗን እንረዳለን ። እያንዳንዱ የጸሎት ዘለላ ከብሉይ ኪዳን ጋር የተሳሰረ መልእክት አለው /ሉቃ. 1፥46-55/ ። ማርያም የሚለው ስም መሰየም የጀመረው ከሙሴ ታላቅ እህት ነው ። እህተ ሙሴ ማርያም ወንድ ልጅ በሚገደልበት ዘመን ሙሴን እንደ ሸሸገች ፥ እንዲሁም እመቤታችን ወንድ ሁሉ በሚገደልበት ዘመን ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ ተሰዳለች ። እህተ ሙሴ ማርያም የኤርትራን ባሕር እንደ ተሻገሩ ንሴብሖ የሚለውን ዝማሬ ፊታውራሪ ሁና እንደ ዘመረች የመዳን ጉዞ መጀመሩን ያየች ድንግል ማርያምም ታዐብዮ ነፍስየ በማለት ዝማሬን አቅርባለች ። በዚህም ፊታውራሪ ሁናለች /ዘጸ. 15፥1-18፤ ሉቃ. 1፥46-55/ ።
አዎ ከአርምሞ ትሩፋቶች አንዱ ቃሉን ማሰላሰል ነው ። ስለ አዳኝነቱ እግዚአብሔርን ማመስገን ነው ። ይህንንም ከድንግል ማርያም ሕይወት የምንማረው ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ