የቃና ዘገሊላው ሰርግ የመጀመሪያውንና የመጨሻውን ዘመን ያስታውሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ በሰርግ ጀምሮ በሰርግ ይፈጽማል ። በአዳምና በሔዋን ሰርግ የሚጀምረው ትረካ በበጉና በሙሽራይቱ ሰርግ ይፈጽማል /ራእ. 22፥17/ ። የዘላለም ዘመን የመክፈቻ ቀን ሰርግ ተብሏል ። ዘላለም ሰርግ እንደሆነ የሚቀር ነው ። በሰው ዓለም ሰርግ ይቀድማል ፥ ኑሮ ይከተላል ። በክርስቶስ መንግሥት ግን ኑሮ ይቀድማል ፥ ሰርግ ይከተላል ። የመጨረሻው ቀን ለኃጢአትና ለጭከና የመጨረሻ ቀን ነው ። ለእነዚህ ነገሮች መጨረሻን ይከፍላቸዋል ። በመጀመሪያው ምጽአቱ ሞትን የገደበ በሁለተኛው ምጽአቱ መከራን ይገድባል ። ያ ቀን የበጉና የቤተ ክርስቲያን የሠርግ ቀን ነው ። በጉ አንዲት ሙሽሪት አለችውና የክርስቲያን ወገን አንድ ካልሆነ ከዚህ ሰርግ ይደናቀፋል ። ቃና ዘገሊላ ዘላቂውንና እውነተኛውን ኅብረት ያመለክታል ። ጋብቻን የመሠረተው ጌታ በጋብቻ ላይ ተገኘ ። ብዙ ሰዎች ሠርጋቸው እንዲያምር ጌታን ይጋብዛሉ ፥ ትዳራቸው እንዲያምር ግን አይጋብዙትም ። ባልጋበዙት ስፍራ የማይገኝ አምላክ ነውና በእልልታ ይገባሉ ፥ በኡኡታ ይኖራሉ ። ክርስቶስን በኑሮአችን ልንጋብዘው ይገባል ። ቤት መሥራት የእርሱ ሙያ ነውና /መዝ. 126፥1/ ።
የባልና የሚስት ቀዳሚው አንድነት የነፍስ አንድነት ነው ። እርሱም በአሳብ መግባባት ነው። በነፍስ አንድ ሳይሆኑ በሥጋ አንድ መሆን ከባድ ነው። ድንቅ ነው ፥ በትንሿ መንደር በቃና ትልቅ ተአምር ተደረገ ። አቅማችን ትንሽ መሆኑ አያስነቅፈንም ፥ እምነታችን ስስ መሆኑ ግን ያስነቅፈናል ። የምናመልከው አምላክ ታናሽነታችን የማይመልሰው ፥ ትልቅነታችን የማያግዘው ነው ። በራሱ ጥበብ ይሠራል ። ከፈቀድንለት ጉድለታችንን ለሙላቱ ፥ ታናሽነታችንን ለብርታቱ መገለጫ ያደርገዋል ። ጌታ ምን አላችሁ ? ሳይሆን ምን ትፈልጋላችሁ ? ይለናል ። ምንም እንደሌለን እርሱ ያውቃል ። ምን ትችላላችሁ ሳይሆን ምን ያህል እንደምችል ታምናላችሁ ? ይለናል ። ምንም እንደማንችል እርሱ ያውቀዋል። ሰዎች የሚቀርቡን ያለንን እሴት ደምረው ሊሆን ይችላል ። እርሱ ግን የጎደለንን አይቶ ይጠጋጋናል ። በእውነት ከምናስፈልገው በላይ ክርስቶስ ያስፈልገናል ።
እመቤታችን ድንግል ማርያም አርባ ቀናት የተለያትንና በጾም በጸሎት ውጫዊ ሰውነቱ የተጎዳውን ልጇን ብታየውም ከናፍቆቷ ይልቅ የክብሩን መገለጥ ፈለገች ። ናፍቆቷ የአርባ ቀን ነው ፥ የክብሩ መገለጥ ግን ሠላሳ ዓመት የፈጀ መሻት ነው ። አማኒ ክፉን ከደግ አወዳድሮ የሚታዘዝ ሳይሆን ከመልካምና መልካም አወዳድሮ የበለጠውን መልካም የሚናፍቅ ነው ።የእመቤታችን ረሀቧ የልጇ ክብር መገለጥ ነው ። ለሠላሳ ዘመን በናዝሬት ጎጆዋ ክብሩን ሠወረ ፥ ከዚህ በኋላ ሰማያዊ አባቱን የሚያገልግልበት ጊዜና ክብሩን ለዓለም የሚገልጥበት ሰዓት ነው ። ምናልባት ልጅሽ ከሰማይ የተመሰከረለት ሳለ ለምን እንዲህ ያለ ኑሮ ትኖሪያለሽ ? ተብላ ይሆናል ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንዳለ ማረጋገጫው የልባችን ሰላም እንጂ የኑሮአችን ምቾት አይደለም ። ምቾት የላይ ዘርፍ ነው ። የውስጥ ልብሱ ግን ሰላም ነው ። ምቾት አለኝ ለማለት እንጂ በራሱ ድሀነት ነው ። የተመቻቸው ከሚበሉት እንዳይበሉት የተከለከለው ይበዛል ። ደረቅ ነገር ላይ ተኙ ይባላሉ። በእግራችሁ ሂዱ ተብለው ይመከራሉ ። የባለጠግነት መጨረሻው ድህነት ነው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም መንፈሳዊነት የሚያስከፍለውን ዋጋ በሙሉ ከፍላለች ።
ጌታን ይበልጥ ስንቀርብ ይበልጥ መውጊያ ይበዛል ። ለምን ቢባል ወራሽ ነንና ። ወራሾች ትርፉን ብቻ ሳይሆን ዕዳውንም ይካፈላሉ ። ሞትና ትንሣኤ መከራና ክብር ሁለቱም የክርስቶስ መልክ ነው ። ወደ ጎልጎታ ለመግባት በሩ ቀራንዮ ነው /ሮሜ. 8፥17/ ። ይህን ሁሉ ከእመቤታችን ሕይወት እንማራለን። ዛሬ እኛ በትምህርት የማናገኘውን ፥ ሐዋርያነትና ነቢይነት የማይደርስበትን ምሥጢር እርሷ ታውቃለች ። እመቤታችን ለቃና ሠርገኞች የለመነችውን አንድ ቀን ለራሷ ለምና አታውቅም ። ተአምር አድራጊው ልጇ ነውና የሚበልጠውን ይዛ አርፋለች ። እመቤታችን ሠላሳ ዓመት የቤት ልጅ ሁኖ እርሷን ያገለገለውን የልጅነት ድርሻውን ተወጣውን ልጇን ከዚህ በኋላ ዓለሙን እንዲያገለግል በሙሉ ፈቃድ ለቀቀችው ። ከዚህ የምንማረው መንፈሳዊ ጥሪ ያላቸውን በአጠገባችን ያሉት ወዳጆቻችንን ለጌታ እንዲኖሩ መልቀቅ እንዳለብን ነው ።
ጌታችን እናቱን ለዚህ ቀን ያዘጋጃት የነበረው ቀድሞ ነው ። የአሥራ ሁለት ዓመት ብላቴና ሳለ ለሦስት ቀን በቤተ መቅደስ ከሊቃውንት ጋር ሲጠያየቅ እናቱ አጥታው ተጨንቃ ነበር ። ባገኘችው ጊዜ ለምን እንዲህ አደረግህብን ? ስትለው “እርሱም፦ ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው” /ሉቃ. 2፥49/። አሁን ደግሞ ጠቅልሎ አባቱን የሚያገለግልበት ጊዜ ደረሰ ። የቤት ልጅ የነበረው ለዓለሙ ተገለጠ ፥ መለኮታዊ እቅዱን የሚተገብርበት ጊዜ መጣ ።
መንፈሳዊ ጥሪ በውሥጣችን ካለ አብረውን ያሉትን ማዘጋጀት አለብን። የዚያን ቀን ተቃዋሚ እንዳይሆኑ ደጋፊ ሁነው ክብሩን እንዲካፈሉ ማዘጋጀት መልካም ነው ። በቃና ዘገሊላ ልጇ ቢሆንም ታስፈቅደው ነበር ። ግንኙነቱ እናትነት ብቻ ሳይሆን እምነትም ነውና ።
የቃና ዘገሊላው የሠርግ ግብዣ ሳይጀመር አለቀ ። ሳይነጋ መሸ ። ሰርግ በአይሁዳውያን ባሕል ከሦስት ቀን እስከ ሰባት ቀን የሚቀጥል ነው ። ምን ዓይነት አደጋ ተከስቶ ይሆን ? በጅምሩ ፍቅር ፥ ኅብረት ፥ አገልግሎት፥ ያለቀባቸው ብዙዎች ናቸው ። ይህንን ሰብአዊ ኃይል አይቀጥለውም ። የእግዚአብሔር ጣት ግን ይቀጥለዋል ። እግዚአብሔር ዛሬም ባለቀ ነገር ላይ በሚቀጥለው ተአምራቱ መገለጥ አለበት ። ብዙ ያለቁ ነገሮች አሉና ። የጨበጥናቸውን መስለውን ለማሳየት ስንል እንደ ወፍ የሚበሩ ብዙ ነገሮች አሉ ። የዚህም መልስ ክርስቶስ ጋ አለ ። እርሱ ካለቀው መቀጠል አይደለም ፥ ከሞተውም መጀመር ይችላል ። በቃና ዘገሊላ ካለቀው ቀጠለ ፥ በቢታንያ የሞተውን ሕያው አደረገ ። ሁለቱንም የዘገበልን ወንጌላዊው ዮሐንስ ብቻ ነው ። ወዳጆች ሆይ አልችልም በሉ ። አይችልም ግን አትበሉ ። እኔ አልችልም እርሱ ግን ይችላል በሉ። ሁለቱም እምነት ነው። የእኔ አለመቻል እርሱን አያግደውም ፥ የእኔ መቻልም እርሱን አያግዘውም ።
አዎ ዓለም ልደትን ሳይጠግቡ ወዲያው በሽታ ፥ ሠርግን ሳይጠግቡ ወዲያው ጥላቻ ፥ ኅብረትን ሳይጠግቡ ወዲያው መካሰስ ነው ። ጉዳዩን በጉዳይነቱ መተረክ መፍትሔ የለውም ፤ እንደ እመቤታችን ለጌታ ስናቀርበው ግን መፍትሔ አለው ። እርሱ የሚመጣበት የተሰመረ መንገድ የለውም ፥ ማንኳኳትና እስኪከፈት መጠበቅ ለሰው ነው ። እርሱን የተዘጋ ልብ እንጂ የተዘጋ በር አይመልሰውም ። የቃና ሰርገኞች ደስታው በድንገት ወደ ኀዘን ተለወጠባቸው ። ለሳምንት ያሰቡት ለሰዓታት የማይቆይ ሆነባቸው። የሰው ነገር ፥ የሰው ጥንስስ ፥ የሰው እቅድ ፥ የሰው ምርጫ በጅምር የሚያልቅ ነው ። የማያልቀው የእግዚአብሔር ብቻ ነው ። ልንጸልይ የሚገባው ፡-
“ጌታ ሆይ እኔ ያሰብኩት ዳር ደርሶ አያውቅም ፤ አንተ በአሳቤ አስብበት ። እኔ የተናገርኩት ፈውሶ አያውቅም ፤ በንግግሬ አንተ ተናገርበት ። እኔ የጀመርኩት ተውቦ አያውቅም ፤ በጅምሬ አንተው ፈጽምበት” ልንል ይገባናል ።
ሲያልቅ ብንጋብዘውም እርሱ ይመጣል ። ሲጠነሰስ ብንጋብዘው ግን ይበልጣል ። ሳይታዘብ የጎደለውን ይሞላል ። ባሕርዩ መርዳት እንጂ መታዘብ የለበትምና ። ያ ሁሉ እድምተኛ እንደ ጎደለ ቢሄድ ኑሮ መተረቻ በሆኑ ነበር ። ብዙ ወዳጆች የማይሸፍኑትን አንዱ ወዳጅ ሸፈነላቸው ። ሰርግ ዕዳ መክፈያ ፥ አቅም ማሳያ ፥ ምን ይሉኛል ? ለሚለው ጭንቀት ማቃለያ ነው። እነዚህ ሰዎች ግን ከሁሉም የሉም ። የቃናው ሰርግ ማለቁም አልተሰማም ፥ መለወጡም አልተሰማም ። ባለቤቱ አውቋል ። ደቀ መዛሙርቱ አምነዋል ። ጌታ መለከት እያስነፋ አንዳች አያደርግም ። ተአምራት ካደረገበት ስፍራም አያድርም ። እርሱ ጓዳ ማንጎዳጎድ ይችላል ። ወደ ጓዳ ባልም አይጠራም ። እርሱ ግን የልብ አውቃ ጌታ ነውና ግባ ይባላል ።
የቃናው ሰርግ ገጠመኙ አሳዛኝ ነው ። ለደስታ ያሉት ቀን ለኀዘን ሲሆን አሳዛኝ ነው ። በየዕለቱ እንዲህ ያለ ነገር ይከሰታል ። ሰዎች ለደስታቸው ያቅዳሉ ፥ መከራ ግን በእነርሱ ላይ ያቅድባቸዋል ። የመጣው ክፉ ነገር ሁሉ ባይመለስ ወይም ወደ በጎ ባይለወጥ በጠፋን ደግሞም የምስጋና ርእስ ባጣን ነበር ። ጠላት ለታላቅ ኀዘን ያመጣውን እግዚአብሔር ለታላቅ ምስጋና ይለውጣል ። ጠላትም ይሠራል ። እግዚአብሔርም ይሠራል። የእግዚአብሔር ሥራ በመጨረሻ ነጥሮ ይወጣል ። ሕይወትን ስናስብ የሚያስደስተን በሕይወት ውስጥ እኛ ያልነው ሰዎች ያሉብን አይሆንም ። እግዚአብሔር ብቻ ያለው ይሆናል ። የምናልፍበት መንገድ እንቅፋት የበዛበት ፥ የእንባ ግብር የምንከፍልበት ሊሆን ይችላል ። እግዚአብሔር ግን ዋስትና ይሰጠናል ።
መንግሥታቸው በሚያውቀው ነገር የሚንቀሳቀሱ ምንም ቢከሰት ጦር ይላክላቸዋል ። ይደራደርላቸዋል ፥ ተናጥቆ ያወጣቸዋል ። እግዚአብሔር ያውቃል ። እርሱ የሚያውቀው እኛ እንደምናውቀው አይደለም። እርሱ አወቀ ማለት አዳነ ማለት ነው ። ወገኖቼ ብረቱ አለ ፥ እሳቱም አለ ። ሦስተኛው ግን የተቆጣጣሪው እጅ አለ ። የባለሙያው እጅ ካልተቆጣጠረ እሳቱ በዝቶ ብረቱ ይበተናል ፥ አንሶ የማይቀጠቀጥ ይሆናል ። መከራው ይኖራል ፥ እኛም እንኖራለን ። የሚቆጣጠረው የቆሰለልን የኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነው ። እኛ ጋ ለመቆየት ጊዜውን የሚወስነው ራሱ መከራው አይደለም ። የችግሩን ዕድሜ የሚያሳጥረው ባለሙያው ጌታ ነው ። በታላቅ ደስታ ላይ ታላቅ ሐፍረት ቢመጣ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ ። በሚደርስብን ነገር እግዚአብሔር በአማኑኤል ስሙ በቃል ኪዳኑ ከእኛ ጋር ነው ። እርሱ ከእኛ ጋር ለመሆኑ ስሜታዊ መለኪያዎች የሉም ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እያለ ህልውናውን ይሰውርብናል ። የእርሱን አብሮነት በስሜታችን ሳይሆን በእምነት እንድናረጋግጠው ይፈልጋል ። እየጸለይን ፥ እየዘመርን ሁሉም ነገር ጸጥ ይላል ። ደስታ ይደርቃል ። መደሰትም ማዘንም ስሜት ነው ። ከእኛ ጋር ለመሆኑ መያዣው ቃሉ ነው ። “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ይላልና /ዕብ. 13፥5 / ። ቃሉን የሰጠን አስገዳጅ መጥቶበት አይደለም ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ፡-
ምስጋና መጀመር ፥
ከጌታ አሳብ ጋር መስማማት ፥
የኋላውን እየረሱ ወደፊት መዘርጋት ያስፈልጋል ። በጓዳዬ ምንም የለም ። በዙሪያዬ የቆመ ማንም የለም ። ስወድቅ ተነሥ የሚለኝ ማንም የለም እያልን ከሆነ እርሱ ከሺህ ሠራዊት ይበልጣል ። ነገሥታት እኛን አጀንዳ አድርገው ከሚሰባሰቡ የእርሱ አብሮነት ቢሰማን ይሻላል ። በሕይወት ውስጥ ነገሥታት የማይፈቱት እንቆቅልሽ አለ ።