የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በቃና ዘገሊላ የድንግል ማርያም ጠባያት

በቃና ዘገሊላ ሠርጉ ሳይጀመር ወይኑ አለቀ ። ሠርግ ላይ የሚከሰት ችግር የሚረሳ አይደለም ። ኃይለኛ ዝናብ ከዘነበ እንኳ ዝናቡን እንቀየማለን። እመቤታችን ግን ጸሎት አቀረበች ፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው ።እመቤታችን ያቀረበችው ጸሎት አጠርና ቀለል ያለ ይመስላል ። ጸሎት የራሱ መንፈሳዊ ድንጋጌ አለው ። የሚለካው በመርዘምና በማጠሩ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ታላቅነት የሚያስብ መሆኑ ነው ። በምንሻው ላይ ሊሻበት ያስፈልጋል ። እንደ ፈለግን መጸለይ አንችልም ። ጸሎት መንፈሳዊ መርሖች አሉት ። እመቤታችን ልመናዋን አቀረበች ። በዚህ ጸሎት ውስጥ ከድንግል ማርያም ሕይወት አራት ባሕርያትን እናያለን ፡-

1- መረዳት
ሰዎች ሳይናገሩ ችግራቸውን መረዳት ይህ አስተዋይነት ነው ። አንዳንዴ እንገነዘባቸውና መልሰን እናፋጥጣቸዋለን ። ለምን አስቀድሞ እንዲህ አልሆነም ? እንላቸዋለን ። በዚህ ዓለም በገንዘብ ከሚረዳን መጀመሪያ አሳባችንን የሚረዳልን ይሻላል ። ከሚፈርድብንም የሚጸልይልን አቅማችንን ያድሳል ። ድንግል ማርያም ተረዳች ፥ ወደ ጌታ አቀረበች ። አጠገቧ ላሉት አላወራችም ። ትዝብትንና ወቀሳን አናይባትም ። ድግሱን የሚመጥን ግብዣ ለምን አልተዘጋጀም አላለችም ። ከችግሩ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ጋርም መወያየትን አልፈለገችም ። ጉዳዩ አምላካዊ እጅ ብቻ እንደሚመልሰው በማመን ለልጇ አቀረበች ። ይህ ለተጎጂዎቹ መጽናናትን ፥ ለእድምተኛው አቅርቦትን ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እምነትን ያመጣ ነው ። ሰዎችን በሰዎቹ ቦታ ሁኖ መረዳት ወሳኝ ነው ። በእኛ አቅምና በእኛ አስተሳሰብ ሁነን የሰዎችን ችግር ልንፈታ አንችልም። ሐዋርያው ፡- “ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ” ይላል /ዕብ. 13፥3/ ። የሌሎች ችግር እየተሰማን መጸለይ ጸሎትን ብርቱ መሣሪያ ያደርገዋል ። የጌታችን የሊቀ ካህንነቱ ታላቅነት የተነገረው የሌሎችን ችግር በርኅራኄ በማየቱ ነው ። “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” ይላል /ዕብ. 4፥15/ ። እመቤታችን ችግራቸውን ተረዳች ። ምናልባት አልነገሩአትም ። ጓዳውን ግን ታውቀዋለች ። ልጇ ይህንን መለወጥ እንደሚችል አውቀው አልጠየቋትም ። ተረዳቻቸው ። ስለዚህም ወደ ልጇ አቀረበች ። ሰዎች እስኪጠይቁን መጠበቅ የለብንም ። መከፋታቸውን እስኪነግሩን ከመጠበቅ በድምፃቸው መጠን ፥ በአካሄዳቸው ዝለት ፥ በደስተኝነታቸው መጠን ልናውቅላቸው ያስፈልጋል ። ይልቁንም የብቻ ሩጫ በበዛበትና ማንም የማንንም ችግር ላለመስማት በሚሮጥበት በዚህ ዘመን ከድንግል ማርያም ልንማር ይገባናል ። ሰው ሁሉ በራሱ ዙሪያ ያለ ይመስላል። ከራሱ አጥር ወጥቶ ማንንም ለማሰብ ፈቃደኛ አይመስልም ። የተራቡት ሰዎች የቀይ መስቀል ጉዳይ ፥ የተጨነቁት ሰዎች የሥነ ልቡና አማካሪዎች ዕዳ ፥ የታመሙት ሰዎች የሐኪም ደንበኞች አይደሉም ። የእኛ የቤት ሥራዎች ናቸው ። ቀይ መስቀል ፍቅርን ሊያቀርብ ፥ የሥነ ልቡና አማካሪ በሕይወት ውስጥ አብሮ ሊጓዝ ፥ ሐኪም አለሁ ሊል አይችሉም ። እውነተኛ ፍቅር ቢገኝ ዛሬ ከሞት የሚመለሱ ፥ ከኀዘን የሚፈወሱ አያሌ ናቸው ። የብዙዎች ሕመም ይልቁንም ሐኪም ያልደረሰበት ጥዝጣዜ ፍቅር ማጣት ነው ። ይህንን ሁሉ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልጋል ። የሰው ልጆች በኢኮኖሚ ፥ በሥነ ልቡና ፥ በማኅበራዊ ዋስትና ፥ በትዳር ግርግር ፥ በልጆች ሥነ ምግባር ክፉኛ እየተጨነቁ ነው ። ስግብግብነት እየበዛ ብዙ ድሆች እየተጎዱ ነው ። ሕግጋት ለተጨቆኑት ፍትሕን ከማምጣት የባለጠጎች ሎሌ እየሆኑ ነው ። አንድን ሰው ለማስደሰት መቶ ሰዎች እየሞቱ ነው ። ገሸሽ ብለን በማለፍ የዓለምን ቊስል እናበረክተዋለን ። ድንግል ማርያምን የሚወድ የሌሎችን ጉዳት መረዳትን ሊያዳብር ይገባዋል ። አስደናቂው ጸሎቷ ብቻ ሳይሆን አስደናቂው ሕይወቷም ትምህርት ቤት ነው ።
2- ሸፋኝነት
ድንግል ማርያም ያየችውን ጉድለት ለማሳየት ፥ የሰማችውን ችግር ለማሰማት አልከጀለችም ። ወደ ልጇ አቀረበች ። እርሱ ከምንም መሥራት የሚችል ነው ። በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን ሲሠራ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል እናነባለን /ዮሐ.9/። በደረቅ ጋኖችም ላይ ወይን ጠጅን ሲያበዛ ይኸው እያየን ነው። መንፈሳዊ ሰው ያየውን ለማሳየት የሰማውን ለማሰማት አይቸኩልም ። ሸፋኝነት ከእግዚአብሔር የሚወርሰው ጠባይ ነው ። “የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው” /ምሳ. 25፥2/ ። ሰሎሞን ጠቢብ የተባለው የተሰወረውን ወንጀል ቆፍሮ በማውጣቱ ነው /1ነገሥ. 3፥16-28/ ። ነገርን መመርመር የነገሥታት መደነቂያ ነው ። እግዚአብሔር ግን ንጉሥ ቢሆንም ከምድራውያን ነገሥታት የሚለየው ነገርን በመሰወር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ገበና ሸፋኞች አሉ ። ልብስ ፥ ቤት ፥ ትዳር ፥ ንስሐ አባት ፥ የሥነ ልቡና አማካሪ ፥ ወላጆች  ገበናን ሸፋኝ ናቸው ። እነዚህ ቢገልጡ ይነቀፋሉ ። ራቁታቸውን ከሚሄዱ በሽተኞች በቅጡ ያልሸፈነ ልብስ ይነቀፋል ። ቤትም ያየውን የማያሳይ ገበና ነው ። ሰው ምሥጢር ያለው ፍጡር ነው ። ቤት ካልሸፈነ ቤት ሳይሆን አደባባይ ነው ። “ቤቴ ቤቴ ገበና ከታቼ ፥ የቤት ገበና መክተት ምንድነው ምሥጢሩ? ? ወደ ጓዳ ገብተው ዱቄትስ ቢቅሙ” ይባላል ። ትዳርም ገበናን ካወጣ የውርደት ምዕራፍ ላይ ነው ። ሁለት ሰዎች የሆኑትን ለሦስተኛ መንገር አይገባም ። ካስፈለገም በቦታው ለአማካሪዎች ብቻ ማስረዳት ያስፈልጋል ። የሥነ ልቡና አማካሪም የሰማውን ማሰማት አይገባውም ። ንስሐ አባትም ምሥጢር ሲያወጣ መቃብር አፍ አወጣ ይባላል ። ልጆቻቸውን የሚያሙ ወላጆችም ክብር የላቸውም ። እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ባሕርይ መላበስ አለባቸው ። የእርሱ ባሕርይ ነገርን መሰወር ነው ። የወዳጆቻችንን ጉድለት እኛ ያየነውን ሌሎች እንዳያዩ መሸፈን ፥ መተያየትና መጸለይ ይገባል ። አብዛኛው ሰው በቤተሰቡ ውስጥ የማይደሰትበት ነገር አለው ። ያንን ግን ሸፍኖ የሚኖር ነው ። “አባቴ ክፉ ነው ፥ ሃይማኖቴ ጠማማ ነው የሚል የለም” ይባላል ። እንደ ቤተሰብ አለመተያየት የሚወልደው ፍርድን ነው ። የሰይጣንን ባሕርይ የተላበሱ ሲወራረዱ የሚኖሩ ናቸው ። መንፈሳውያን ግን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም የምንማረው ሸፋኝነትን ነው ።
3- እምነት
 እመቤታችን እምነቷ የተመሰከረለት ነው ። ዘመዷ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተመልታ “ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት” ብላ መስክራለች /ሉቃ. 1፥45 / ። ያለ ወንድ ዘር መፅነስ በእግዚአብሔር ኃይል እንደሚቻል ያመነች እርሷ ብቻ ናት ። በቃና ዘገሊላም ጉዳዩን በቀጥታ ወደ ጌታ ያቀረበችው በእምነቷ ነው ። ለመጸለይ እምነት ያስፈልጋል ። እመቤታችን እምነቷ ጥያቄን እንድታቀርብ አደረጋት። መጨነቅ አለማመን ነው ። መጨነቅ ችግሩን በአጉሊ መነጽር እያዩ ምን ይመጣ ይሆን ? እያሉ ውጤቱን መስጋት ነው ። መጸለይ ግን እግዚአብሔርን እያዩ ከችግሩ በላይ በሆነው መለኮታዊ ችሎታ መጽናናት ነው ። መጨነቅ ችግርን መተንተን ነው ። መጸለይ ግን የእግዚአብሔርን ተስፋ ማሰብ ነው ። መጨነቅ ሌሎች ተጨናቂዎችን መጋበዝ ነው ፥ መጸለይ ግን አርፎ ማሳረፍ ነው ። ይህችን ዓለም ወደ ህልውና ያመጣው የበላይ ምክንያት አለ ። ዕጣዋንም የሚወስን አንድ የበላይ ጌታ አለ ። የትኛውም ደብዳቤ ቢጻፍ ባለሥልጣኑ ካልፈረመበት ደብዳቤው አቅም የለውም ። በመጨረሻ የሚፈርመው ባለሥልጣኑ ነው ። እግዚአብሔርም ይሁን ያላለው አይሆንምና መረጋጋት ይገባል ።
 በኳስ ሜዳ ውስጥ አንድ ዳኛ ፥ ሁለት አራጋቢ ፥ መቶ ሺህ ደጋፊዎች ይኖራሉ ። ታዲያ አራጋቢዎቹ በተጫዋቹ ላይ ቢያራግቡ ፥ ይውጣ ቢሉ የሚወስነው የዳኛው ፊሽካ ነው ። ዳኛው ፊሽካውን እስካልነፋ ማንም አያስወጣውም ። በሕይወት ውስጥ ብዙ አራጋቢዎች ከራእይ፥ ከእሴታችን እንድንወጣ ሊጥሩ ይችላሉ ። ዳኛው እግዚአብሔር ካልወሰነ ግን ማንም አያወጣንም ይህ እምነት ነው ። በምንም ነገር ሳንደናገር እግዚአብሔርን ብቻ የሚያስደስተውን እየመረጥን ወደፊት መሄድ ይገባናል ።
4- መምህርትነት
 “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት አገልጋዮቹን አዘዘች ። ወይን ሂደት የሚፈልግ ነገር ነው ። መተከል ፥ ማፍራት ፥ መረገጥ ፥ መጥለል ፥ መሰንበት ያስፈልገዋል ። ይህን ሂደት ሳይጠብቅ ልጇ ተአምር ማድረግ ይችላል ። ጌታን ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ ድንጋጌዎች አይዙትም ።  በዓለም ላይ ያሉ የመጨረሻውን ዳኝነት ቢሰጡ እርሱ የበላይ ነው ። ተአምራት ከተፈጥሮ ሕግ በላይ መሥራት ነው ። ይህም የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ነው ። በሕይወታችን ተአምራት ይናፍቀናል ። ተአምራት ስንሰማም የእኔ ተራ መቼ ይሆን ? እንላለን ። ዛሬ መድረሳችን ግን በራሱ ተአምር መሆኑን አንገነዘብም ። ጉልበት ያለው ደክሞት ትላንት ላይ ቀርቷል። ዛሬን ማየታችን ትልቅ ተአምር ነው ። ያለ ተአምርም የዋለ ቀን የለም ። የማየትና ያለማየት ጉዳይ ነው ።
 እመቤታችን ያየውን ወደማያሳየው ፥ የሰማውን ወደማያሰማው ጌታ አቀረበች ። በስውር የለመኑትን በግልጥ የሚከፍል ጌታና መለሰላት ። ልመናው የማይነበብ ቢሆን እንኳ መልሱ ግን የሚነበብ ነው ። በእውነት በመለኮት ከመሰማት የበለጠ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ? እመቤታችን አንድም ቀን ስለራሷ ተአምር ለምና አታውቅም ። የግብፅ ስደቷ ፥ የኑሮ ጉስቁልናዋ ምስክር ነው ። ልጇም ከመስቀል ላይ እንዲወርድ እንደ ሰነፎቹ አልጠየቀችም ። ይህ ዓለም ለሰማይ ዜጎች እንደማይደላ ታውቃዋለች ። ሁሉን አድራጊው በእቅፏ ነው ። ጌታ የእኛ ሲሆን ጥያቄአችን ያንስብናል ። የመንፈሳውያን ደስታ የሌሎች ችግር ሲወገድ ማየት ነው ።
 እመቤታችን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው”  እርሱ የሚላቸው አለ። እግዚአብሔር ለልጆቹ ቃል አለውና ። እርሱ የሚለው እንዲያደንቁለት ሳይሆን እንዲያደርጉት ነው ። የሚላችሁን ሁሉ ብላለች ። እየመረጡ እርሱን መታዘዝ የለም ። የሚለንን ሁሉ ማድረግ ይገባል ። አገልጋዮቹም የእመቤታችንን ድምፅ ሰምተው የሚላቸውን ሁሉ አደረጉ ። ውጤቱ ምንድነው ? ወይን አልቆ ውኃ ይሞላል ወይ ? አላሉም ። ውጤቱ ሳያሳስበው የሚታዘዝ እርሱ አማኝ ነው ። እመቤታችን ልጇን ለዓለም አስተዋወቀችው ። በደብረ ታቦርም እግዚአብሔር አብ ፡- “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” ብሏል /ማቴ. 17፥5/ ። እግዚአብሔር አብ በዮርዳኖስ ልጄ ነው ብሎ ለዓለም ገለጠው ፤ በደብረ ታቦርም እርሱን ስሙት አለ ። እመቤታችንም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለች ። ለዓለምም አስተዋወቀችው ። “ሙሴም ለአባቶች፡- ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ” /የሐዋ. 3፥22-23/ ። በቃና ዘገሊላ እመቤታችን መምህርት ነበረች ። የሚላቸውንም ሁሉ ስላደረጉ በረከታቸው ተትረፈረፈ ። እነዚህን አራት ባሕርያት ከእመቤታችን ድንግል ማርያም እናገኛለን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ