የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ የካቲት 4/2008 ዓ.ም.
4- ዳግም ልደትና የአዲስ ኪዳን አምልኮ
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ከምናገኛቸው ዋና ዋና ትምህርቶች በምዕራፍ 3 እና 4 ላይ የተገለጡት ዳግም ልደትና የአዲስ ኪዳን አምልኮ ተጠቃሽ ናቸው። ሁለተኛ መወለድ/ዳግም ልደት/ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበት ምሥጢር ነው። ባንወለድ ኖሮ ይህን ዓለም ማየት አንችልም ነበር። ዳግመኛም ካልተወለድን የሚመጣውን ዓለም ማየት አንችልም። መወለድ የኅብረት ውጤት ነው። አባትና እናት በመተባበራቸው ልደት ይገኛል። እንዲሁም ቃሉና መንፈሱ፣ ውኃው /ጥምቀት/ እና መንፈሱ ሲዋሐዱ ዳግም ልደትን እናገኛለን። አባቶች እንደሚገልጡት፡- ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ እንወለዳለን። አምልኮ ግብር ነው። ግብር ለመንግሥት የሚደረግ መገዛት ነው። ርስት የያዘ ሰው ይገብራል። እንዲሁም የልጅነትን ጸጋ፣ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት የያዘ ሰው ለእግዚአብሔር የአምልኮ ግብር ይከፍላል። ርስት አንድ ጊዜ ተሰጥቶ ግብሩ ቀጣይ እንደሚሆን አንድ ጊዜ ተወልደን በዘመናችን ሁሉ እናመልካለን። የምናመልከው ልጆች ለመሆን ሳይሆን ልጆች ስለሆንን ነው። የማይገብር ከርስቱ የመነቀል ችግር እንደሚገጥመው እግዚአብሔርን በአምልኮ የማያከብርም ጸጋው አደጋ ላይ ይወድቃል።
የአዲስ ኪዳን አምልኮ ያለጊዜ፣ ያለ ቦታና ያለ ሁኔታ ወሰን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አገልግሎት ነው። የምናመልከው አምላክ የፈለገው ለባሕርዩ የሚስማማ አምልኮ ነው። “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” ይላል /ዮሐ. 4፡24/። እግዚአብሔር በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ አይገደብም። አምልኮም ያለ ጊዜ ገደብ በሕይታችን ዘመን ሊቀርብ ይገባዋል። “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ይላልና። አምልኮ የቦታና የሁኔታ ተጽእኖ ሊኖረው አይገባም። “በሁሉ አመስግኑ” ይላልና /ተሰ. 5፡17/። መንፈሳዊ አምልኮ የሚባለው ለባሕርዩ የሚስማማ አምልኮ ነው። በእግዚአብሔር መገኘት አርፈን ማምለክ ማለት ነው።
ጌታችን ዳግም ልደትን ለኒቆዲሞስ፣ የአዲስ ኪዳንን አምልኮ ለሳምራዊቷ ሴት ተናገረ። ታላላቅ ምሥጢራትን በጉባዔ ለሕዝብ ሳይሆን ለግለሰቦች ነገረ። ጌታችን ለአንድ ሰው ዋጋ ይሰጣል። ኒቆዲሞስ አዋቂ ቢሆንም የዳግም ልደት ምሥጢር አልገባውም። ሴቲቱ ያልተማረች ብትሆንም መንፈሳዊ አምልኮ አልተሰወራትም። የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለማወቅ የግል እውቀታችንና አለማወቃችን አይረዳንም፣ አይወስነንም። ትሕትና ብቻ የምሥጢራት ቁልፎ ሆኖ ይኖራል።
ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው የተወሰደብንን ልጅነት ለማስመለስ ነው። እርሱ የሰው ልጅ ወደ መባል ዝቅታ ወረደና እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ወደ መባል ከፍታ ወሰደን። ልጅነታችን የጸጋ፣ የስጦታ፣ የማደጎ ነው። ልጅነታችን በውስጡ ሥልጣንም ያለው ነው። ከንጉሥ የሚወለድ ልዑል፣ ልዕልት እንደሚባል ከእግዚአብሔር በመወለዳችን አዝማደ መንግሥት ወይም የቤተ መንግሥት ሰዎች ሆነናል። በልጅነት የተመሠረተው ይህ ኅብረት በአምልኮ ይቀጥላል። ጌታችን የአዲስ ኪዳንን አምልኮ ለአንዲት የተናቀች ሴት ተናገረ። ለሴቶች ነገረ መለኮትን ማስተማር ከጌታ እንማራለን። ኒቆዲሞስ የእኩለ ሌሊት ተማሪ፣ ሴቲቱ የእኩለ ቀን ተማሪ ነበሩ። በእኩለ ሌሊትና በእኩለ ቀን የሚያስተምር ክርስቶስ ብቻ ነው። ማንም በማይገኝበት ሰዓት የሚገኝ የሌሊትና የቀትር ወዳጅ እርሱ ብቻ ነው። እኩለ ሌሊትና ቀትር የከበበ ሁሉ የሚበተንበት ሰዓት ነው። በዚህ ሰዓት የሚሰለጥነው ክፉ ሰይጣን ነው። “ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም” /መዝ. 90፡5-6/ ይላል። እነዚህ ሁሉ የማያስፈሩት እግዚአብሔር መጠጊያ ሲሆነን ነው። ኒቆዲሞስ ጌታን ፈለገ አዋቂ ነውና። ከአዋቂዎች መፈለግ ይጠበቃል። ይህችን ሴት ግን ጌታ ፈለጋት። ያልተማሩትን መፈለግ ይገባል። ጌታ ሲያገኛቸው ከዘላለሙ ርእስ ጀመረላቸው። ሌላው ርእስ ሁሉ ጊዜያዊ ነው። እግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘው ግን ዘላለማዊ ርእስ ነው።
ከዘላለማዊው ርእስ ያውለን።