የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ ጥር 24/2008 ዓ.ም
የዮሐንስ ወንጌል ፀሐፊ ማን ነው?
የዮሐንስ ወንጌል ፀሐፊ ቅዱስ ዮሐንስ ነው። በአዲስ ኪዳን በዚህ ስም የሚታወቁ ሦስት ሰዎች አሉ። አንደኛው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ሁለተኛው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው። ሦስተኛው ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ነው። የወንጌሉ ፀሐፊ በጻፈው ወንጌል ወንጌላዊ ዮሐንስ ተብሏል። ዮሐንስ ከዓሣ አጥማጅነት ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ሲጠራ ታንኳውንና አባቱ ዘብዴዎስን ትቶ የተከተለ ነው /ማቴ. 4፡21/። ከአባት ፍቅር ይልቅ የአባት ፍቅር የሚያሳድር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ በእውነት ልዩ ነው። ከአባቱ በላይ የሚሆን ጌታ፣ ከዓሣ ማጥመድ በላይ የሆነ የወንጌል ሥራ፣ ከጥብርያዶስ የሚልቅ የእግዚአብሔር መንግሥት ሲመጣለት ለጥሪው አልዘገየም። እግዚአብሔር ጠርቶትም ከሰው ለመማከር አልፈለገም። እግዚአብሔር ሲጠራ ከማን ጋር እንማከራለን? “ተከተለኝ” የምትል አምስት ቃል ይህን ሁሉ ውሳኔ አስወስናለች። ሰዎች ረጅም ሰዓት በማስተማር የሚማርኩ ይመስላቸዋለች። እግዚአብሔር በአንደበታችን አጭር ቃል ቢናገር ብዙዎች የሕይወት ዘመን ውሳኔ ይወስናሉ። ይህ ዮሐንስ ዕድሜው ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ ወጣት ነበረ። በጊዜ ገብቶ ረጅም ዘመን አገለገለ። የዕድሜውን እንጥፍጣፊ ሳይሆን አስኳሉን ሰጠ።
ዮሐንስ ወንጌላዊ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አምስት መጻሕፍት ጽፏል። አንድ ወንጌል፣ ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ ጽፏል። በአዲስ ኪዳን ብቸኛ የሆነውን የትንቢት መጽሐፍ ራእየ ዮሐንስን የጻፈው ይህ ዮሐንስ ነው። ዮሐንስ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ ዘግይቶ አገልግሎቱን የፈጸመ ነው። በ95 ዓ.ም በደሴተ ፍጥሞ ላይ ታስሮ የተሰጠውን ሩጫ አጠናቋል። 65 ዓመታት ያህልም ጌታን በታማኝነት አገልግሏል። ይህ ዮሐንስ የብዙ ስሞች ባለቤት ነው።
1- ወልደ ነጎድጓድ፡- የነጎድጓድ ልጅ ይባላል። ኃይለኛ ስለ ነበር ከወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ጌታችን ያወጣላቸው ስም ነው /ማር. 3፡17/።
2- ወንጌላዊ፡- ከአራቱ ወንጌላት አንዱን የዮሐንስ ወንጌልን በመጻፉ ወንጌላዊ ይባላል።
3- ፍቁረ እግዚእ፡- ጌታ የሚወደው ማለት ነው። ዮሐንስ በወንጌሉ ስለ ራሱ ሲጽፍ የተጠቀመበት ስያሜ ነው /ዮሐ. 13፡23፣19፡26፣20፡2፣21፡7፣21፡20/። ዮሐንስ እኔ የምወደው ከማለት ጌታ የሚወደኝ በማለት በጌታው ፍቅር ተመካ።
4- አቡቀለምሲስ፡- ባለ ራእይ የራእይ አባት ማለት ነው። ራእዩን በማየቱና በመጻፉ የተሰጠው ስያሜ ነው።
5- ታኦሎጎስ፡- በግሪክ ቋንቋ ነባቤ መለኮት ስለ መለኮት የሚናገር ማለት ነው። በወንጌሉ ስለ አካላዊ ቃል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳማዊነት ጽፏልና /ዮሐ. 1፡1/።
6- ነቢይ፡- እስከ ምጽአት ድረስ ያለውን ክንውኖች በዝርዝር ጽፏል። ራእዩም የትንቢት መጽሐፍ የሚል መደብ ተሰጥቶታል።
7- ድንግላዊ፡- ዮሐንስ በድንግልና ምርጫ እግዚአብሔርን በማገልገሉ የሚጠራበት ስም ነው።
ይቀጥላል
ማሳሰቢያ ይህን የዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ እግዚአብሔር እንደ ረዳን በየዕለቱ ስለምንማማር ተግታችሁ እንድትከታተሉ የእናንተን ፈቃድ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንለምናለን።