“ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም”
/ዮሐ. 1፡6-8/፡፡
ዮሐንስ መጥምቅ ከእግዚአብሔር የተላከ ነበር፡፡ እኛም ብንሆን የምንልከው የቀለለንን ነው፡፡ የምንልከውን ስንጠራው እውነተኛ ተላኪ መሆኑን ከድምፁ እናውቀዋለን፡፡ የሚታዘዝ ሰው ቶሎ አይገኝም፡፡ መልእክተኛ እንደ ራሴ ነው፡፡ ክርስቶስ በእርሱ ቦታ ቢሆን የሚናገረውን ብቻ ለሌላው የሚናገር ነው፡፡ የመልእክተኛ ሌላው ስያሜ ሐዋርያ የሚል ነው፡፡ ሐዋርያ ማለት ሖረ ሄደ ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ሂያጅ ገስጋሽ ወንጌልን ተሸክሞ ለማድረስ የሚፈጥን ማለት ነው፡፡ ምሥጢራዊ ትርጉሙ ግን በሥልጣን የተላከ ማለት ነው፡፡ መልእክተኛ አፈ ንጉሥ ነው፡፡ ሥልጣን ያለውን ቃል የተሸከመ ነው፡፡ መልእክቱ እርቅ ነው፡፡ በድሎ ያኮረፈውን ዓለም እግዚአብሔር በመልእክተኞቹ እንታረቅ ይለዋል፡፡ የባሪያ አኩራፊ መልሶ ራሱን ይጎዳል፡፡ እግዚአብሔርም እንታረቅ እያለ ይለምናል፡፡ የምንወደውን አባብለን ለምነን ነው የምሰጠው፡፡ ከሰሙ ይስሙ የራሳቸው ጉዳይ ነው በሚል ወንጌል አይሰበክም፡፡ እንዲህማ ለማለት ባለመብቱ ጌታችን ነበር፡፡ እርሱ ግን ለሁሉ ሞተ፡፡
ክርስቶስ ልዩነትን ያመጣል በሚል መጽናኛ በገዛ ጠባያችን ሰዎች ሲደነብሩ ከመለወጥ መጽናናት እንፈልጋለን፡፡ ክርስቶስ ልዩነትን የሚመጣ ቢሆን እንኳ እርግጠኛ ባሕርዩ የተለያዩትን አንድ የሚያደርግ ሰላም ነው /ኤፌ. 2፡14/፡፡ ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው፡፡ ለማንም ሰው “የምሥራች” ስንለው በአገራችን “ምስር ብላ” የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ መልእክታችን የሚያጓጓ መሆን አለበት፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በአንድ ቀን ሦስት ሺህ ሰዎችን እንደማረከ እናስብ፡፡ ወንጌል ሰሚዎችን የሚማርክ ነው፡፡ ደጉን ጌታ በእኛ ጭካኔ እንዳንጋርደው ማሰብ ያስፈልገናል፡፡
ዲያቆናት ክንፋቸውን እንዳራገፉና ለበረራ እንደ ተዘጋጁ አእዋፋት ናቸው፡፡ መልእክተኛ ማለት ክንፉን ያራገፈ ማለት ነው፡፡ ደርባባነት መንፈሳዊነት አይደለም፤ ስልታዊ የክብር ጥማት ነው፡፡ ክንፉ ያልቀለለው ሊላክ አይችልም፡፡ ደርባባ አቡን ይመስላል እንድንባል ሳይሆን ሌሎች እንዲድኑ ፍቅር ያለን ልንሆን ይገባናል፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ እውነተኛ መልእክተኛ ነበር፡፡ ክብርን የሸሸ፣ ዓለምን የናቀ ነበር፡፡ ክብር ስለራቀው የናቀ ሳይሆን ምትክ ሊቀ ካህናት ሳለ እምቢ ብሎ በረሃ የገባ፣ በፈቃዱ ድሃ የሆነ አገልጋይ ነው፡፡
መጥምቁ ዮሐንስና ነቢዩ ኤልያስ ተመሳሳይ የሕይወት ምርጫና አገልግሎት ነበራቸው፡፡ ሁለቱም ድንግላውያንና መናንያን ነበሩ፡፡ ሁለቱም ነገሥታትን ገስጸዋል፡፡ ኤልያስ ንጉሥ አክአብን፣ ዮሐንስ ሄሮድስ ገስጸዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ልዩ ተልእኮ ካልተሰጠ በቀር ነገሥታትን መገሰጽ አይቻልም፡፡ የዮሐንስ መጥምቅ አገልግሎት ከኤልያስ ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ስለ ዮሐንስ መጸነስ ለአባቱ ለዘካርያስ ብሥራት ሲነግረው፡- “እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል” ብሏል /ሉቃ. 1፡17/፡፡ በነቢዩ ሚልክያስ፡- “እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” ተብሏል /ሚልክ. 4፡5-6/፡፡ ሚልክያስ የመጨረሻው ነቢይ ሲሆን ይህን ተስፋ ሰጥቶ ትንቢቱን ይዘጋል፡፡ ያ ኤልያስ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የኤልያስን ስምና አገልግሎት ቢወርስም ራሱ ኤልያስ ግን አይደለም /ማቴ. 17፡10-13/፡፡ በርግጥ ኤልያስ በመጨረሻው ዘመን እንደሚመጣ ይታመናል፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ግን በኤልያስ መንፈስና ኃይል የሚሄድ ነው፡፡ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች ማለት ወደ ይቅርታ ወደ ተስፋ ማለት ነው፡፡ የልጆችን ልብ ወደ አባቶች ማለትም ወደ ብስለትና ራእይ ማለት ነው፡፡ ምድር ከእርግማን እንድትድን አባቶች ይቅርታና ፍቅርን፣ ልጆችም ክብርና ማስተዋልን ሊይዙ ይገባቸዋል፡፡ የዮሐንስ አገልግሎት ይህ ነበረ፡፡ በርግጥም በክርስቶስ ሽማግሌዎች ታደሱ፣ ወጣቶች ራእይ አገኙ /ሉቃ. 2፡25-35/፡፡
የዮሐንስ የስሙ ትርጉም ደስታ ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ጸጋ ነው ማለትም ነው፡፡ ዮሐንስ የወላጆች ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ደስታ ነው፡፡ ወላጆቹ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ዘመናቸውን በሙሉ አገልግለው መጨረሻ ላይ ወለዱ፣ ልጁን ሳያሳድጉ ሞቱ፡፡ ዮሐንስም ወላጆቹን ሳያገኝ ዘመኑን በሙሉ እግዚአብሔርን አገልግሎ አለፈ /ሉቃ. 2፡80/፡፡ ዘመን ያልባከነበት ያ ቤተሰብ ምንኛ የታደለ ነበረ! ዮሐንስ ስሙ ደስታን ያመለክታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ይገልጣል፡፡ ጸጋ የታደልነው በረከት፣ የምንቆምበት አቅም፣ ዋጋ የምናገኝበት ክብረት ነው፡፡ የታደልነው በረከት፣ የቆምንበት አቅም፣ የከበርንበት ዋጋ እግዚአብሔር ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር