የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ማክሰኞ መጋቢት 13/2008 ዓ.ም.
“ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር።በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” /ዮሐ. 1፡9-11/፡፡
ወንጌላዊው ኀዘኑን ይገልጣል፡፡ ብዙ ሐሰተኛ ብርሃንን የተቀበለ፣ ለብዙ ሐሰተኛ መገለጥ ልቡን የሰጠ ሕዝብ እውነተኛውን ብርሃን በመግፋቱ፣ ዮሐንስ መጥምቅን ባከበረበት መጠን ክርስቶስን ባለማክበሩ ያዝናል፡፡ ይህ ብርሃን ብዙ ዘመን የተመላለሰና ሰውን የፈለገ ብርሃን ነው፡፡ በእኛም ሕይወት በልጅነታችን፣ በወጣትነታችን፣ በጎልማሳነታችን፣ በሽምግልናችን የፈለገን ብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ካለበት እስክንሄድ አይጠብቅም፣ ብርሃን ካለንበት ይመጣል፡፡ ክርስቶም ካለንበት ድረስ መጥቶ ፈለገን፡፡ ኃጢአተኛ ያለበትን አድራሻ አያውቅም፣ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ብርሃን ክርስቶስ ካለበት ድረስ መጥቶ ይፈልገዋል፡፡ ይህ ብርሃን ዓለምን አድራሻ አድርጎ የመጣ ብርሃን ነው፡፡ እጁን ከሰው ልጆች አንሥቶ የማያውቅ ቢሆንም ሰው ግን ሊያውቀው አልቻለም፡፡ የታላላቅ አገር መሪዎች ይታወቃሉ፡፡ ፈጥሮ የሚገዛው፣ ስለ ፍቅር እንደሚታረድ በግ የተነዳው ክርስቶስ ግን አይታወቅም፡፡ መኖራችን የመኖሩ ምስክር ነው፡፡ ባናውቀውም እስክናውቀው ታገሠን እንጂ አልተቀየመንም፡፡

ዓለሙ የሆነው በእርሱ ነው፣ ዓለሙ ግን አላወቀውም፡፡ የማመን መሠረቱ ማወቅ ነው፡፡ ለማወቅ ያልፈቀደ ዓለም ለማመን እንዴት ይፈቅዳል? ስለዚህ ዓለም የገፋችው ሠሪዋን ነው፡፡ በዓለም ታሪክ ሠሪውን የታዘዘ እንጂ የገፋ የለም፡፡ ግዑዛን እንኳ ለሠራቸው ይታዘዛሉ፡፡ መኪናውና አውሮፕላኑ ለሠራው ይታዘዛል፡፡ ሕያዋን ግን ለሠራቸው ባለመታዘዛቸው ወንጌላዊው ያዝናል፡፡ ግዑዛን ለሠሪያቸው የሚታዘዙት ለሚያም ሥርዓትም ነው፡፡ ወንበርን ብንወስድ ለሚያም ሥርዓቶች ታዝዞ ወንበር ሆኗል፡፡ ዛፍ ነበረ ተቆረጠ፣ በመሰንጠቂያ ተሰነጠቀ፣ በመቦርቦሪያ ተቦረቦረ፣ በሸካራ ለሰለሰ፣ በምስማር ተመታ…. ፡፡ በመጨረሻ ተቀብቶ አበራ፡፡ ሥራ ሠሪውን እስከዚህ ይታዘዛል፡፡ ዮሐንስ ዓለሙ አላወቀውም ሲል መደነቅ ሞልቶበት ነው፡፡ በመርሳት በሽታ የተያዙ ሰዎች ወዳጆቻቸውን በመርሳታቸው አዝነናል፡፡ የሞተልንን አምላክ የረሳን ከዚያ በላይ እናሳዝናለን እያለ ነው፡፡
ፀሐይና ጨረቃ በሚያበሩበት ዓለም ላይ ብርሃን ነኝ እያለ መጥቷል፡፡ጨለማ እንደ ጥያቄ ቆይቷል ማለት ነው፡፡ ይህ ጨለማ እኔ ብቻ ይድላኝ የሚል ስግብግብነት፣ ከእኔ ባይ ማንም የለም የሚል ኩራት፣ የማን አለብኝነት ቅሌት፣ ከእኔ ውጭ ያለው ይደምሰስ የሚል ጠባብነት… ምድሪቱን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ሥጋ በጥፋት፣ ነፍስ በድንቁርና፣ መንፈስ በክህደት የተያዙበት ዘመን ነበር፡፡ ገላጋይ አጥቶ ሁሉም በስምምነት ያበደበት ዘመን ነበር፡፡ ድሆችና ምስኪኖች ለባለጠጎች የተፈጠሩ እስኪመስል፣ ሞተው እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ዘመን ነበር፡፡ መጠን የለሽ ጥጋብና መጠን የለሽ ረሀብ እንደ ምሥራቅና ምዕራብ ላይገናኙ የተራራቁበት ዘመን ይመስል ነበር፡፡ ሥራ አጥነትና የጎዳና ተዳዳሪነት የበዛበት ዘመን ነበር፡፡ ኢየሱስ በዚህ ጨለማ ውስጥ ሊያበራ መጣ፡፡ ትውልድ ሞራል በሌለው ማንነት ተዘፍቆ፣ አገር ሻጭ ቀራጭ፣ ራሱን ሻጭ ዘማዊ የሆነበት ዘመን ነበር፡፡ የሃይማኖቱ መዲናም ሕይወት የሌለው ሥርዓት፣ ፍቅር የሌለው ወግ አጥባቂነት የሚታይበት ነበር፡፡ ከወግ አጥባቂዎቹ ትይዩ የሚታዩ ሰዱቃውያን ደግሞ ለባለጠግነትና ለዘመናዊነት ሥፍራ የሚሰጡ ተራማጅ ሃይማኖተኞች ነን ብለው ይኮሩ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ተራ ሥነ ጽሑፍና ለማኅበራዊ ሰላም ብቻ የሚጠቅም እንደሆነ የሚያስቡ የተበራከቱበት ዘመን ነበር፡፡ ጌታ በዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ውስጥ የብርሃን መልስ ሆኖ መጣ፡፡ ሰው ጭልም ብሎኛል ሲል ለመነሣትም ለመሄድም ግብ አልታይ ብሎታል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ትእዛዝ ሳይሆን የመሆን ኃይል ሆኖ መጣ፡፡ ያ ብርሃን የሕይወት ካርታ፣ የመንገድ መሪ ነው፡፡ በልብ ላይ የሚያበራ የእውነት ፓውዛ ነው፡፡
ብርሃን ክርስቶስ እርቃኑን ተሰቀለ፣ ብርሃን ከተጋረደ አያበራምና፡፡ፀሐይ አስቀድማ ብርሃኗ ቀጥሎ ሙቀቷ ይመጣል፡፡ ከክርስቶስ ቀጥሎ ከብቸኝነት ብርድ የሚገላግለው ሙቀት መንፈስ ቅዱስ መጣ፡፡ ያ ብርሃን ለሰው ሁሉ መጥቷል፡፡ ይህ ብርሃን የማያስፈልገው የለም፡፡ ብርሃን ካልከፈቱለት አይገባም፡፡ ከከፈቱለትም አይሰስትም፡፡ በሽቁር መጠን በር ካገኘ በዚያ መጠን ያበራል፡፡ ብርሃን በከፈቱለት መጠን ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ያመነውን ያህል አገኘነው እንጂ የሆነውን ያህል አላገኘነውም፡፡ ብርሃን እንደ ጎርፍ አንዴ የሚያጥለቀልቅ ነው፡፡ ክርስቶስም ከዘላለም ስጦታ የሚጀምር ወዳጅ ነው፡፡ ፀሐይ ሁልጊዜ እንደምትወጣ ጌታችንም እንዲሁ በደጃችን ቆሟል፡፡ እውነተኛው ብርሃንም ተፈልገን ወደ ማናልቅ ሁልጊዜ ይመጣል፡፡ ዓይነ ሥውሩ ፀሐይን ስላላየ የለችም ቢል መኖሯ አይቀርም፡፡ ስላላመነውም እርሱ ህልውናውን እና ክብሩን አያጣም፡፡
ይህ ጌታ ህልውናውን ከዓለም አላራቀም፡፡ ምክንያም ተፈጥሮን እርሱ ካልመራው ነገሥታት መምራት አይችሉትም፡፡ ክረምትና በጋ ከፓርላማ ውሳኔ ውጭ ነው፡፡ ሌሊትና ቀን ከካቢኔ ሥልጣን ባሻገር ናቸው፡፡ ዓለም ግን አላወቀውም፡፡ እየካደውም እንዲኖር ፈቅዶለታል፡፡ ነገሥታት ያልፈጠሩት ሲከዳቸው በሞት ይቀጣሉ፡፡ እርሱ ግን ፈጥሮ ሲከዳው ዓለሙን አላጠፋውም፡፡
ያልጠፋነው ከቸርነትህ የተነሣ ነው፡፡ ተመስገን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ