የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደህና ነው /2/

የሱነም ከተማ በተራራ ላይ ከተቆረቆሩ ከተሞች አንዷ ናት ። በቀርሜሎስ የመሸገው ነቢይ ኤልሳዕ በእግር ከዳር እስከ ዳር ያቋርጣታል ። የታመመን በነጻ ይፈውሳል ፣ ያዘነን ያለ ዋጋ ያጽናናል ፣ የበደለን ያለ ምንዳ ስርየትን ይነግረዋል ። ድነሃል ፣ በችግርህ ላይ እግዚአብሔር ትልቅ ነው ፣ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል የሚል ድምፅ በእውነት ውድ ነው ። የእግዚአብሔር ጸጋ የማይከፈልበት ዋጋ ሊገዛው ስለማይችል ነው ። ሕዝቡ ግን ከሚፈውሱት የሚያቆስሉትን ፣ ከሚያጽናኑት በችግሩ የሚያላግጡትን ፣ የኃጢአቱን ስርየት ከሚነግሩት በንስሐው እያስፈራሩ የሚኖሩትን ነቢያተ ሐሰት መርጧል ። የሚያበሉትን ሳይሆን የሚበሉትን ፣ ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ሰርግ የሚያሰናዱትን ቢጽ ሐሳውያን ያፈቅራል ። ኤልሳዕ በእግዚአብሔር ያረፈ ፣ ለቁራሽ የማይሰግድ በመሆኑ ስውር ዓላማ እንዳለው ሰው ይታይ ነበር ። የሰው ልጅ ጸጋን ትቶ ክፍያን ፣ ቸርነትን ጠልቶ ምንዳን ያከብራል ። ያቺ የሱነም መንደር የሚያልፈውን ነቢይ ጎራ በል ልትለው ያልደፈረች ፣ ሺህዎች ለአንዱ ነቢይ ያላሰቡባት ከተማ ነበረች ። የማያልፈውን ለሚሰጠው የሚያልፈውን ቁራሽ ልስጥህ ያለው ማንም አልነበረም ። ኤልሳዕን ላለማየት በተከናነበችው በሱነም ከተማ አንድ አስገራሚ ክስተት ተፈጸመ ።

ለማኝም ይሰጠዋል ፣ ይለምናልና ወይም ያሳዝናልና ። የእግዚአብሔር እንደራሴ የሆነው ነቢይ ግን አይለምንም ፣ ሕዝቡ እጅ ላይ የእግዚአብሔር ድርሻ አለና የመብቱን ይቀበላል ። ለእግዚአብሔር አገልጋዮች የቱንም ያህል ብናደርግ ምስጋና እንኳ መጠበቅ የለብንም ። ምክንያቱም ስጦታችን ግዴታችን እንጂ ቸርነታችን አይደለምና ። እግዚአብሔር ዋጋ የሚከፍለን በቸርነታችን ሳይሆን የአምላክን ቸርነት ለሰዎች በመግለጣችንና አደራችንን በመወጣታችን ነው ። የአገራችን ሰው ይቅር በለኝ ብለው እግሩ ላይ ሲወድቁ የሚያቀናቸው እንዲህ እያለ ነው፡- “ይቅር የሚል እግዚአብሔር ነው ፣ ሁላችንን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን” ይላል ። እንዲሁም ሰዎች ስለሰጠናቸው ስጦታ ጎንበስ ብለው ሲያመሰግኑን፡- “የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ፣ እኔ አቀባባይ ነኝ ፤ እኔም ከእርሱ ተቀብዬ ነው የምሰጠው” ማለት ይገባናል ። ስጦታ አምልኮ የሚሆነው እግዚአብሔርን ስናከብርበት ነው ።

ሱነም ውሎ ቀርሜሎስ ጫካ ያድራል ። ያ የእግዚአብሔር ነቢይ ለሰማይ ወፎች መሳፈሪያ ፣ ለምድር ቀበሮዎች ጉድጓድ አላቸው ፣ እኔ ግን ራሴን የማስጠጋበት የለኝም እስኪል የእግዚአብሔር ድሀ ሁኖ ነበር ። የሰው አነጋጋሪ ቢያጣ ከዱር አራዊት ጋር ያወራል ፣ ጉባዔ ቢታጠፍበት ከሰማይ ወፎች ጋር ያወጋል ፣ ሰዎች ርቀውት ዛፎች እንደ ሠራዊት ከበውታል ። መንፈስ ቅዱስ ብቸኝነትን ፣ ተፈጥሮ ፀጥታን ይዋጉለታል ። መንፈስ ቅዱስ በምድረ በዳው ዓለም ላይ ከለማ ከተማ በላይ ድፍረት ይሰጣል ። ብቸኝነት ያለ ሰው መሆን ሳይሆን ያለ መንፈስ ቅዱስ መሆን ነው ። ከእኛ ርቀው የሚኖሩ አባቶች ከእግዚአብሔር አልራቁም ። ተፈጥሮ ምላሽ ሳይጠብቅ ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት ይናገራል ።

የእግዚአብሔር ሰዎች ተፈጥሮን የሚንከባከቡት እንደ ዘመዳቸው አድርገው ስለሚመለከቱት ነው ። ተፈጥሮ አድልኦ የሌለው ቸርነት አለው ። አበባ ለእገሌ ውበቷን ሰጥታ ለእገሌ አትደብቅም ። በሰው እኩልነት የሚያምን ተፈጥሮ ነው ። የእግዚአብሔር ልግስና በሰው ሲታነቅ ተፈጥሮ ግን ያለ መቆጠብ ይሰጣል ። ተፈጥሮን ማድነቅ የማይችል እግዚአብሔርን በቅጡ አላወቀውም ። የሠርክን ውበት ማየት የማይችል የተዘጋ ልብ ያለው ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎች ከተፈጥሮ ጋር ስለሚዛመዱ አነጋጋሪ አይቸገሩም ። የምንወደው ሰው የሠራውን ሥዕል ባይገባንም እናደንቃለን ፣ ሙዚቃውንም እናዳምጣለን ። እግዚአብሔር የወጠረው ሸራ ሰማይ ይባላል ። ይህን የሚያህል ሸራ የወጠረ ሠዓሊ የለም ። በዚህ ሰማይ ላይ የማይጠገብ ውበት አርፏል ። የወፎች ዝማሬም የጆሮ ምታችንን አያውክም ። እግዚአብሔርን ስንወድ የፈጠረውን እንንከባከባለን ።

በነቢዩ፡- “እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን ፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት ፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል” ይላል ። /ኢሳ. 61፡3 ።/ ተክል ፣ ዛፍ ፣ ዘይት ፣ ቅጠል እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ማስተማሪያዎች ናቸው ። ተክል ሲተከል ቦታ ይይዛል ፣ እስራኤልም በምድረ ከነዓን ተተክላለች ። የተተከለ ከሌላ ቦታ የመጣ ነው ፣ እስራኤልም ከግብጽ መጥታለች ፤ የተተከለ ፍሬ ይጠበቅበታል ፣ እስራኤልም መልካም ማድረግ አለባት ። ተፈጥሮን መጉዳት የእግዚአብሔርን የማስተማሪያ ዕቃዎች መጉዳት ነው ። እውቀታችንም እያነሰ ይመጣል ።

ነቢዩ ኤልሳዕ ሁሉ በደጅ እጅ ይነሣዋል ። በቤቱ ግን የሚቀበለው ማንም አልነበረም ። የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሚበላ ፣ ማረፊያ እንደሚያስፈልገው ያወቀች ያች ሴት ብቻ ነበረች ። አሥር ቢወለድ የሚጠቅም አንድ ነው ። ከሺህ ሕዝብ መካከልም አንድ አስተዋይ ይገኛል ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ለችግር ቀን የሚፈለግ ለግብዣ ቀን የሚረሳ ነው ። እንደ ቀብር አስፈጻሚ ፣ እንደ ዕድር ጡሩንባ ነፊ ፣ እንደ እሳት አደጋ ሠራተኛ ፣ እንደ አልቃሽ ሙሾ አውራጅ ፣ እንደ ሐኪም በችግር ቀን ውል የሚል ችግሩ ሲያልፍ ከልብ የሚረሳ ነው ። ሰው የችግር ቀን ወዳጁን በደግ ቀን ቢጠራ ችግር በዓለም ላይ አይደጋገምም ነበር ።

በሰራፕታ ብዙ መበለቶች ነበሩ ። ኤልያስን መጀመሪያ ልቧን ቀጥሎ ቤቷን ከፍታ የተቀበለች ግን አንዲት ባልቴት ናት ። በሱነምም ብዙ ሴቶች ነበሩ ። ኤልሳዕን የተቀበለች ግን አንዲት ሴት ናት ። /ሉቃ. 4 ፡ 25-26 ።/ ኤልሳዕ ሳይነግራት ችግሩን ያወቀችለት ፣ ሳያሳስባት ያሰበችለት ፣ የሚበላ አፍ ፣ የሚያርፍ አካል እንዳለው የተገነዘበች አንዲት ትልቅ ሴት ናት ። ይህች ሴት ለአንድ ቀን ለጉራ አልጋበዘችውም ። ሸክሜ ነው ብላ ኃላፊነት ወሰደች ። ፈሪሳዊው ስምዖን ጌታን በር ከፍቶ ልቡን ዘግቶ ተቀበለ ። ይህች ሴት ግን ልቧን ስለከፈተች በሯንም ከፈተች ። ልብ ዘግቶ በር መክፈት ይቻላል ። ልብ ሲከፈት ደግሞ የማይከፈት ደጃፍ የለም ። /ሉቃ. 7 ፡ 36-50 ።/

ይህች ሴት የሀብት ጥያቄዋ ቢመለስም የልጅ ጥያቄዋ ያልተመለሰላት ሴት ናት ። ደስታ ማለት የሁሉም ጥያቄዎች መልስ መገኘት አይደለም ፤  ከጥያቄ በላይ የሆነውን አሸናፊ ጌታ ማየት ነው ። ባልተገኘው ነገር የተገኘውን ነገር ደምስሳ የምታይ ሴት አልነበረችም ። ባላት መደሰትን የመረጠች ፣  ደስታ አጥታ ባሏን ደስታ የምትነሣ ፣ እንደ ሣራ ከእገሌ ውለድ ብላ ወደ ዝሙት የምትመራ አልነበረችም ። “የወለዱ እንጀራ የላቸውም ፣ እኔ እንጀራ ቢኖረኝም ልጅ የለኝም ፤ ሁሉም ቤት ጉድለት አለ ፣ ቢሆንም ደህና ነው” ብላ ታስብ ነበር ።

ያለንን ማየት አቅቶን በሚኖረን ነገር ላይ ደስታችንን ያስቀመጥን ፣ ለደስታ ቀጠሮ የሰጠን ሰዎች ባለን እንደሰት ። እኛ ያለንን ሌሎች የላቸውም ። እግዚአብሔር ያየውን አይቶ በከለከለን ነገር ደስ ይበለን ። ሁኔታዎች በመለወጣቸው ሳይሆን እኛ በመለወጣችን ደስ ይበለን ። ያልተፈጸመ ፣ ያልተሟላ ነገር ፣ ይህ ቢሆን የምንለው ጉዳይ ቢኖረንም ደህና ነው ። ደህና ነው ማለት እግዚአብሔር ትክክል ነው ማለት ነው ። እግዚአብሔር ከአሳቡ ለሚስማሙ በረከት አዝሎ የሚጠብቅ ብሩህ ደመና ነው ። ደህና ነው ።

ይቀጥላል

ደህና ነው /2
ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ