የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደህና ነው /6

የሌሎችን ጉድለት ስንሞላ እግዚአብሔር የእኛን ጉድለት ይሞላል ። እኛ ጋ ያለው ከእኛ ይልቅ እዚያ ጋ ጥቅም ይሰጣል ። ሌሎች ጋ ያለው በረከትም ለእኛ ጥያቄ መልስ ይሆናል ። እግዚአብሔር አንዱን ላንዱ መልስ እንጂ ጥያቄ አድርጎ አልፈጠረውም ። ያቺ የሱነም ሴት ካላት ነገር ላይ ለኤልሳዕ ቤትን ሠራች ፣ የኤልሳዕ አምላክ ደግሞ የሌላትን ልጅ ሰጣት ። እርስዋ ያደረገችው ገንዘብ የሚገዛውን ነው ። በኤልሳዕ ምክንያት ያገኘችው ደግሞ ገንዘብ የማይገዛውን የልጅ ስጦታ ነው ። ኤልሳዕ ወደ ቤቷ ሲገባ የዘመናት ጸሎቷ መልስ አገኘ ። አገልጋዮች ዕዳ አይደሉም ፣ በረከት ናቸው ። የሱነም ሴት እንጀራ ስትጋብዝ የማንም ውለታ የማያልፍበት እግዚአብሔር ልጅ ሰጣት ። የእግዚአብሔርን አገልጋዮች በመቀበል የምናገኘው በረከት አለ ። ለእግዚአብሐር ሠራዊት መንገድ በመዝጋት ደግሞ እንደ አማሌቅ ለዘላለም መረገም አለ ።

ነቢዩ አልሳዕ ለንጉሥ ነግሮ ርስትን ፣ ለሠራዊት ነግሮ ጥበቃን ሊያሰጣት ቢፈልግም ይህች ሴት ግን በኑሮዋ የረካች በድሀ ወገንዋ የተማመነች ነበረች ። ኤልሳዕም ተጨነቀ ። ወደ አገልጋዩ ወደ ግያዝ ዘወር አለና፡- “እንግዲህ ምን እናድርግላት ? አለ ። ግያዝም፡- ልጅ የላትም ባልዋም ሸምግሎአል ብሎ መለሰ ።” /2ነገሥ. 4፡14 ።/ ይህች ሴት ለኤልሳዕ በሠራቸው ቤት እንኳ ለመግባት ድፍረት አልነበራትም ። ፈርታ በደጅ ቆማ ታናግረዋለች ። ችሮታዋ ፣ ቤት ሠርታ መስጠቷ እንድትዳፈር አላደረጋትም ። ግያዝ በእርስዋና በነቢዩ መካከል ሁኖ ቃል ያስተላልፍ ነበር ። አገልጋዮች  ራእያቸውን የሚያካፍሉት ፣ ደግሞም የሚያግዛቸው አንድ ደቀ መዝሙር ያስፈልጋቸዋል ። እነርሱ ሲርቁ ደግሞ ወንበሩን የሚወርስ ፣ ቃሉን የሚያስተላልፍ ረድእ በግድ ያሻቸዋል ። ግያዝ አገልጋይነቱ ለኤልሳዕ እንደ አጥርም ነው ። ነቢዩን እንዳይጋፉና እንዳይዳፈሩ ይከለክላል ። ነቢዩ በሚፈልጋቸው ምድራዊ ነገርም ግያዝ ይሯሯጣል ። አሁንም ይህች ሴት ልጅ እንደሌላት ለኤልሳዕ ነገረው ። ግያዝ እህ ብሎ ነገር የሚመጠምጥ ሰው ነበር ። ማን ምን እንደሆነ ያውቃል ። ነቢዩ ብዙ ነገሮችን ቢያውቅም የሰውን ገመናና ጉድለት ግን ላያውቅ ይችላል ። በነቢይነቱም በማንነቱም የሰውን ምሥጢር ላያውቅ ይችላል ። ግያዝ ወሬውን አጣርቷል ። መፍትሔ ግን የለውም ። ቢሆን ወረኞች ሁልጊዜ መጥፎ አይደሉም ፣ ለጥንቃቄ ይረዳሉ፤  ከዕይታችንና ከጆሮአችን ለራቁ ነገሮች እንደ መነጽር ፣ እንደ ጆሮ ሁነው ያገለግላሉ ። ወረኞች ሁልጊዜ ምንጫችን መሆን ግን አይችሉም ። ነቢዩ የማያውቀውን የዚያን ቤት ምሥጢር ግያዝ ግን አውቆ ጨርሶ ነበር ። ነቢይነት የሰውን ጓዳ ማወቅ አይደለም ። ለመፍትሔ እግዚአብሔር ችግሩንና መልሱን የሚገልጥበት ጸጋ ነው ። ግያዝ በወሬ አነፍናፊነቱ ችግሩን ያውቃል ፣ ኤልሳዕ ግን መፍትሔውን ያውቃል ። ያች ሴት ቤትን ሠርታ በሰጠች ቀን ነቢዩ ደግሞ ያላሰበችውን ፣ ተስፋ የቆረጠችበትን ፣ እንደ ሙላት የቆጠረችውን ጉድለት ፣ የማኅበረሰቡን ነቀፌታ የተቋቋመችበት ቋጠሮ ፈታላት ። በዚያ ዘመን አስተሳሰብ ባልዋ ልጅ ፍለጋ ወደ ሌላ ሴት አልሄደም ። ልጅን የትዳር በረከት እንጂ መሠረት አላደረጉትም ነበር ። በጊዜው ሊሆን ከአምላክ አልተቆራረጡም ፣ በአቋራጭ መንገድ አልሄዱም ። በዚህም ሰላማቸውንና በረከታቸውን ከማባከን ጠብቀዋል ።

ነቢዩ ከግያዝ ባገኘው መረጃ፡- “በሚመጣው ዓመት በዚህ ወራት ወንድ ልጅ ትታቀፊአለሽ አለ እርስዋም፦ አይደለም ጌታዬ ፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ፥ ባሪያህን እንዳትዋሻት እለምንሃለሁ አለች ።” ነቢዩ የእግዚአብሔር አፍ ነውና ልጅ እንደምትወልድ ተናገረ ። እግዚአብሔር ለእርሱ ስላደረገችው መልካምነት በልጅ በረከት ይባርካታል ። ኤልሳዕ ምንም ዕዳ የለበትም ። ቤት ተቀበለ ፣ አምላኩ ደግሞ ልጅ ሰጠ ። ለእግዚአብሔር ሰዎች መስጠት ማትረፍ እንጂ መክሰር አይደለም ። የነቢዩ የኤልያስ መንፈስ በእጥፍ ያረፈበት ሰው ነበር ። ኤልያስ የሰራፕታዋን መበለት ልጅ ከሞት ቢያስነሣም ልጅ እንድታገኝ ግን አልጸለየላትም ። ኤልሳዕ ግን የሱነም ሴት ፣ ልጅ እንድታገኝ ደግሞም ልጇ ከሞት እንዲነሣ ምክንያት ሁኗል ። ይህች ሴት የሰማቸውን ዜና ማመን አቅቷት በደስታ ሰከረች ። ከአእምሮ በላይ ሆነባትና እንዳትዋሸኝ አለች ። ነቢዩን ውሸታም ማለቷ ሳይሆን ታላቅ መደነቋን የገለጠችበት ቃል ነው ።

የሱነም ሴት ልጅ ባይኖራትም ሁሉም ነገር የለኝም ብላ የምታስብ ፣ በአንድ ጉድለት ያላትን ነገር ማየት የምትቸገር ሴት አልነበረችም ። አለመውለዷንም እንደ በጎ አይታ በደስታ የምትኖር ሴት ናት ። የምሥራቹ ሲመጣም በልጅ ነገር እኔ አርፌአለሁ የእግዚአብሔር ሰው በዚህ ነገር አትጨነቅ ማለቷ ነው ። ኤልሳዕን የጠራችበት “የእግዚአብሔር ሰው” የሚል አጠራሯ የሚደንቅ ነው ። ቤት ሠርቼ ብሰጥህም አንተ የእኔ ሎሌ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሰው ነህ ። ነገሮችን ከዘመኑና ከባሕሉ አንጻር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል የተነሣ የምትተረጉም ነህ ማለቷ ነው ። በትንሽ ገመድ ትልቁን ነቢይ የማሰር ፍላጎት አልነበራትም ። ስጦታ ማስገደጃ ፣ የአሳብ ማስፈጸሚያ ፣ ይሉኝታ ማስያዣ ከሆነ የሚቆጠረው ከጉቦ ነው ። ጉቦ ደግሞ ፍቅር የለሽ ስጦታ በመሆኑ ሰጪውንም ተቀባዩንም የሚያስጠይቅ ነው ።

“ሴቲቱም ፀነሰች፥ በዚያም ወራት በአዲሱ ዓመት ኤልሳዕ እንዳላት ወንድ ልጅ ወለደች።” ። እግዚአብሔር በነቢዩ አፍ ተናግሯልና አይዋሽም ። ልጅ የሀብት ውጤት አይደለም ። ሲሰጠን የምንቀበለው ፣ ከከለከለን አመስግነን የምንቀመጥበት ነው ። የወለደ ሁሉ የተደሰተ ፣ ያልወለደ ሁሉ ያዘነ አይደለም ። ክረምትና ማኅፀን የማያበቅለው የለም እንደሚባለው ይሁዳም ልጅ ነው ። አባቱን የሚገድል ፣ እናቱን የሚዋርድ ፣ ጌታውን የሚሸጥ ልጅም አለና እግዚአብሔር ሲከለክልም ማመስገን ይገባል ።

እግዚአብሔር የረሱትን የጸሎት መልስ አስቦ ይሰጣል ። አንዳንድ ጸሎቶች እንዲፈጸሙ ልናደርጋቸው የሚገቡ ተግባራት አሉ ። ይህች ሴት እግዚአብሔር ጸሎቷን የመለሰው ነቢዩን በማስተናገዷ ነው ። ጸሎት ተግባር ከሌለው አያርግም ። በአዲስ ዓመት አዲስ ስጦታ አገኘች ። ፀንሰው እስኪወልዱ ብዙ የእግዚአብሔር ጥበቃና ከለላ አለ ። ይህች ሴት አለመውለድን ተሻግራ ፣ ፀንሳ እስክትወልድ የእግዚአብሔር ጥበቃ አልተለያትም ።

እግዚአብሔር የረሱትን የጸሎት ዘር ፍሬ አድርጎ ያበላል ። የተቀበሉትን ችግር የሙላቱ አደባባይ ያደርገዋል ። በጌትነቱ ለሚታመኑ የጌትነቱን ሥራ ይሠራል ። እግዚአብሔር አለኝ ለሚሉ አለሁ ብሎ ይገለጣል ። አዎ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም ሕይወት ይቀጥላል ። ስጦታ መጪና ሂያጅ ነው ። ሰጪው እግዚአብሔር ግን ከሞላ የማይጎድል ነው ። ባይኖረንም የመኖር መብት አለን ። ቢኖረንም እንኖራለን ማለት አይደለም ። መኖር በእግዚአብሔር ነውና ደህና ነው ።

ይቀጥላል

ደህና / 6
ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ