የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ግንቦት 7/2007 ዓ.ም.
ገንዘብ መውደድን ድል መንሣት
/ራእ. 2፡12-17/
ከሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን ናት። የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ የሆነ የጣኦት አምልኮ ባለበት ከተማ ላይ ያለች እንዲሁም ሰማዕትነትን የቀመሰች ቤተ ክርስቲያን ናት። ይህች ቤተ ክርስቲያን ውጫዊ ግፊቶችን ድል ነሥታለች። ነገር ውስጣዊ ትግሏን ማሸነፍ ባለመቻሏ ተነቅፋለች። በውስጧ ገንዘብን የሚወዱ የሐሰት መምህራን ተነሥተው ነበር። አነዚህ የሐሰት መምህራን ለእግዚአብሔር ሕዝብ መውደቂያ ጉድጓድ የሚቆፍሩ ነበሩ። የበለዓምን ሥራ እንደሚሠሩ ተገልጧል። ባላቅ የተባለ ንጉሥ እስራኤልን በጦርነት ማሸነፍ ባልቻለ ጊዜ በለዓም ለተባለ የአሕዛብ ነቢይ እርገምልኝ ብሎ በገንዘብ ቀጠረው። በለዓም ግን እግዚአብሔር የባረከውን መርገም አቅቶት እረግማለሁ ሲል አፉ እየሳተ ብዙ በረከትን ባረከ። ባለቅ ደስ እንዳልተሰኘ ባወቀ ጊዜ ገንዘብን ላለማጣት አንድ ማሰናከያን አስጠናው። በሰይፍ ፊት የማይመለሱት እስራኤል ቆነጃጅት ካዩ እንደሚወድቁ በዚህም ከአምላካቸው ሲጣሉ ማሸነፍ እንደሚችል በለዓም መከረው። ባላቅም ቆነጃጅትን አሰልፎ ጠበቃቸው። የእስራኤል ጎበዞችም ሳቱ። ለአሕዛብ ጣኦታትም ሰገዱ። በዚህም ምክንያት ትልቅ ቁጣና ሽንፈት መጣ። በለዓም የንጉሡን ልብ፣ የእስራኤልን አቅም፣ የእግዚአብሔርን ውሳኔ የሚያውቅ በጣም ማስላት የሚችል ክፉ መካሪ ነው። በለዓም ይህን ሁሉ ያደረገበት ምክንያት ገንዘብ ለማግኘት ነው። የገንዘብ ፍቅሩ ለብዙዎች በነፍስ በሥጋ መውደቅ እንዳያስብ አደረገው። ይህንን የበለዓምን ሥራ የሚሠሩ የሐሰት ነቢያት በጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን ተንሰራፍተው ነበር።
ቤተ ክርስቲያን እስከ 313 ዓ.ም. በሰማዕትነት ውስጥ ታልፍ ነበር። በ313 ዓ.ም. የዕረፍት ዘመን ስታገኝ የውስጥ ፈተና ተነሣ። ይህም የኑፋቄ ትምህርት ነው። ሰይፍ አንድ ያደረጋትን ቤተ ክርስቲያን ኑፋቄው ግን ለሁለት ከፈላት። የኑፋቄው መነሻ ምን ነበር? ስንል የገንዘብና የሥልጣን ፍቅር ነው። ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ትልቅ ፈተና ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሁለት ጌቶች እንዳሉ ተናግሯል /ማቴ. 6፡24/። እነዚህ ጌቶች እነማን ናቸው? ቢባል አብዛኛው ሰው የሚመልሰው እግዚአብሔርና ሰይጣን በማለት ነው። እነዚህ ጌቶች ግን እግዚአብሔርና ገንዘብ ናቸው። ገንዘብ በምድር ላይ ብዙ ተከታይና አማንያን አሉት። ገንዘብ ያዘዛቸውን የሚያደርጉ ለመስረቅ ብቻ አይደለም ለመግደልም የማይሳሱ ብዙዎች ናቸው። በሃይማኖት የተቀባቡ ጠቦች ውስጥ ሰርገን ስንፈልግ የምናገኘው የገንዘብን ጦስ ነው። በችግር ዘመን በሰላም የኖሩ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ ሲመጣ መለያየት ይጀምራሉ። የዛሬ ዘመን የወንድም ፍቅር የገንዘብን ፈተና የሚያልፍ አልሆነም። በየውጭ አገሩ በኪራይ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ይኖሩ የነበሩ አዲስ ሕንጻ ሲገነቡ ኅብረቱ ይፈርሳል። ሕንጻው ይታነጻል ፍቅር ግን ይፈርሳል። ገንዘብ ፍቅርን የመበከል አደጋ ያለው መርዝ ነው። መርዝ ባለበት የማይቆም እየመረዘ የሚሰፋ ነው። ገንዘብም የግለሰቡን ታማኝነት በመንጠቅ ይጀምራል። ቀጥሎ ሌባ ቀጥሎም ነፍሰ ገዳይ ያደርገዋል። ገንዘብ ማኅበራትን መቆጣጠር ሲጀምር በልስላሴ ይገባል። ከዚያ በኋላ እየሻከረ ያሻክራል። የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ተበላ የሚሉ ተቆርቋሪ መሳዮች አንድ ቀን ነፍስ ጠፋ ብለው አያውቁም። የሚያሳዝናቸው ከነፍስ ይልቅ ገንዘብ መጥፋቱ ነው። ይህ ብቻ አይደለም በግፍና በቅሚያ የሚመጣ ገንዘብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ የቀሳውስቱን ሰላም ያናጋል። ገንዘብ ርግማን ተሸክሞ ይሄዳል። በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉት። የወር ስሙ ደመወዝ የሚል ነው። ደምና ወዝ ማለት ነው። ሁለቱም ከባድ ናቸው። ከገንዘብ ጋር አብሮ የሚሄድ ብዙ ነገር አለ።
ገንዘብ ግያዝን ከደቀ መዝሙርነት ጥሪ ያደናቀፈ ነው /2ነገሥ. 5፡20-27/
ገንዘብ ይሁዳ ጌታውን እንዲሸጥ ያደረገው ነው /ማቴ. 27፡3/
ገንዘብ ሐናንያና ሰጲራ መንፈስ ቅዱስን እንዲያታልሉ ያደረገ ነው /የሐዋ. 5/።
ዛሬም ወንድም ወንድሙን እስከ ሞት የሚፈልገው በገንዘብ ነው። ገንዘብ ተቀብለው ስም የሚያጠፉ ተሳዳቢዎች ነፍስ የሚያጠፉ ገዳዮች ብዙ ናቸው። ገንዘብ ንጹሑን ወንጀለኛ ወንጀለኛውን ንጹሕ አድርጎ የሚያሳይ ሐሰተኛ መስተዋት ነው። ገንዘብ ሌቦችን ከነገሥታት እኩል እጅ እንዲነሡ የሚያደርግ የሐሰተኛ ክብር መገኛ ነው። ገንዘብ ፍርድን የሚያስት ነገሥታትን አዋርዶ የድሆችን ንብረት እንዲቀሙ የሚያደርግ ነው። የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን ድል እንድትነሣ የተጠየቀችው ይህን ነው። ዛሬም ብዙ ነቢያት ነን፣ ይታየናል የሚሉ እንዲሁም ፈዋሽ ነን የሚሉ ወገኖችን እያፈላ ያለው ይህ ገንዘብ ነው። ታገኛለህ፣ ይሳካልሃል የሚለው የአፍሪካ ወንጌል የድሆች መቀስቀሻ ትምህርትን የወለደው ይኸው ገንዘብ ነው። ስብከትን ሳይቀር እያሳተ ጥሪን ሳይቀር እያደናቀፈ ወንድም ወንድሙን ልበ ሙሉ ሆኖ እንዲበላ የሚያደርገው ይህ ገንዘብ ነው። በሞት የታመኑ ሰዎች በገንዘብ ተሸንፈዋል። በእሳት ውስጥ ተፈትነው ያለፉ ምቾት ግን ጣኦት ሆኖባቸዋል። ገንዘብ የዝሙት ምክንያትም ነው። ስለ ገንዘብ ራሳቸውን የሚሸጡ አያሌ ናቸው። በገንዘብ ሃይማኖታቸውን የካዱ ቁጥር የላቸውም።
ይህ ፈተና ድል ለነሡ የተገባላቸው ተስፋ አለ፡- “ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፣ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፣ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል” /ራእ. 2፡17/። የተሰወረ መና እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ ይበሉት የነበረው ምግብ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ የተሰወረ በረከት አለው። አለምክንያትም ያኖራል። ነጭ ድንጋይ በሮማ ፍርድ ቤቶች ነጻ የወጣ ተከሳሽ የሚሰጠው ነው። የገንዘብ ፈተናን ድል መንሣት ከኅሊና ወቀሳ ነጣ ያደርጋል። በውድድር ላሸነፉም ስማቸው የተጻፈበት ነጭ ድንጋይ ይሰጥ ነበር። የሚጠፋውን ገንዘብ የናቁ የማይጠፋውን ክብር ያገኛሉ። እኛስ ገንዘብን እያዘዝነው ይሆን ወይስ እያዘዘን ነው?
ይቀጥላል