መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » አዲስ ኪዳን » የማቴዎስ ወንጌል » ጽድቅን ሁሉ መፈጸም/ማቴ. 3÷15/

የትምህርቱ ርዕስ | ጽድቅን ሁሉ መፈጸም/ማቴ. 3÷15/

ሐሙስ፡ ጥር 17/ 2004 ዓ.ም.
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ሊጠመቅ በሄደ ጊዜ ዮሐንስ ከሩቅ ዓይቶ፡-‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› በማለት ገለጠው /ዮሐ. 1÷29/፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን ስለ ኃጢአት ብዙ ሺህ መሥዋዕቶች ቀርበዋል፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ በቤተ መቅደሱ ምርቃት ቀን ሃያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሃያ ሺህ በጎች ለመሥዋዕት አቅርቧል /1ነገሥ.8÷63/፡፡ በአንድ ቀን ይህን ያህል መሥዋዕቶች ከቀረቡ በሺህ ዓመታትማ የቀረበውን መሥዋዕት ለመገመት እንኳ አይቻልም፡፡ ስለ ኃጢአት የቀረቡት መሥዋዕቶች ብዙ ቢሆኑም ኃጢአትን ከማስወገድ ኃጢአትን ያዳፍኑ ነበር፡፡ ጊዜያዊ የቁጣ ማብረጃ እንጂ እውነተኛ ስርየትን ማምጣት አልቻሉም ነበር፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ለዓለሙ ሁሉና ለዘላለሙ የሚበቃውን መሥዋዕት በሩቅ ባየ ጊዜ በልዑል ድምፅ፡- ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› ብሎ ጮኸ፡፡
በብሉይ ኪዳን የቀረቡት ብዙ ሺህ መሥዋዕቶች ሊያስወግዱት ያልቻሉትን አንዱ መሥዋዕት ክርስቶስ ሊያስወግደው መጣ፡፡ ያለፈውን ኃጢአት የሚደመስስ ብቻ ሳይሆን የኃጢአትን የመግዛት አቅም፣ አሰናካይነቱንም የሚያስወግድ መሥዋዕት ሆኖ ተገለጠ፡፡ እነዚያ ብዙ መሥዋዕቶች በብዛታቸው ኃጢአትን ማስወገድ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የሰው በጎች ነበሩና፡፡ አንዱ የእግዚአብሔር በግ ክርስቶስ ግን አንድ ጊዜ ተሠውቶ ለዘላለም የሚበቃ መሥዋዕት ሆነልን /ዕብ. 9÷26-28/፡፡

 ጌታችን እስከ ሠላሳ ዘመኑ ተሠውሮ እንደ ኖረ እናውቃለን፡፡ ይኸውም የመጀመሪያው ለዝግጅት ነው፡፡ ለሦስት ዓመት ከሦስት ወር አገልግሎት ሠላሳ ዓመት ተዘጋጀ፡፡ ሁለተኛ በሥጋ የወለደችውን እናቱን ድንግል ማርያምንና የሥጋ ዘመዶቹን ሊያገለግል ሠላሳ ዓመት መደበ፡፡ አሁን ግን ሰማያዊ አባቱንና ሕዝቦቹን የሚያገለግልበት ጊዜ ቀረበ፡፡ ለሠላሣ ዓመታት ተሠውሮ የኖረው የዓለሙ መፍትሔ፣ የእንቆቅልሹ ፍቺ ተገለጠ፡፡ ዮሐንስ እውነተኛን በግ ለዓለም ሁሉ አስተዋወቀው፤ መጋረጃው ተገለጠ፡፡ መሥዋዕቱ ለዓለም ሁሉ ተዋወቀ፤ ጠላትነት በግልጽ ተጀመረ፡፡

አይሁድና ሊቃነ ካህናት በገሀድ የሚነቅፉት ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ምስክርነቱ የዮሐንስ ብቻ አልነበረም፣ የባሕርይ አባቱና የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስም መሥዋዕቱን ገለጡት፡፡ ይህ መሥዋዕት ሰማይና ምድር የመሰከሩለት፣ ኃጢአትን ሊያስወግድ ብቃት፣ እግዚአብሔር ሊያስደስት ውድነት ያለው ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔርም ኅሩይ /ምርጥ/ ነው፡፡
ጌታችን ከዚህ በኋላ ያለው አገልግሎት ሦስት ክፍል አለው፡- የመጀመሪያው፣ የጠፉትን በቃሉ ትምህርት መመለስ፣ ሁለተኛ፡- በሥጋ መከራና በአጋንንት ቁራኛ የተያዙትን በእጁ ተአምራት መፈወስ፣ ሦስተኛ፡- ቤዛ ኩሉ ዓለም ሆኖ በመስቀል በመሠዋት ድኅነትን መፈጸም ነው፡፡ የማይገባውን ሞት ካልተቀበለ የማይገባንን ሕይወት አናገኝምና በቀራንዮ እርቃኑን የሚሰቀለው ጌታ በዮርዳኖስ በገሀድ ወጣ፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሩቅ ሲመጣ ዮሐንስ መሰከረለት፡፡ ጌታ ዮሐንስን ሲቀርበው ደግሞ ዮሐንስ ድካሙን ገለጠለት፡፡ አገልጋይ ለሰዎች የጌታውን ክብር፣ ለጌታውን ደግሞ የሕይወቱን ድካም ሊናገር ይገባዋል፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ፡፡ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፡፡ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር›› /ማቴ. 13÷14/፡፡ ዮሐንስ ይህንን ያለው እኛ እንደምንለው ለትሕትና አይደለም፣ በእውነት ነው፡፡ ዮሐንስ የብዙዎቹን ውድቀት ሰምቷል፡፡ እርሱ ደግሞ የሚሰማውን ጌታ ይፈልግ ነበር፡፡ ለዘመናት ኢየሱስ በመጣና እኔም በእጁ በተጠመቅሁ እያለ ይመኝ ነበረ፡፡ ኢየሱስ ግን አጥምቀኝ አለው፡፡ አገልጋዩም መገልገል ፈልጎ ነበር፡፡ አገልግሎት ግን ጡረታ የለውም፡፡ የአገልግሎት ወደቡ ሰማይ ነው፡፡ ብዙ አገልጋዮች ይህን ተመኝተዋል፣ ጌታ ግን ገና አገልግሉኝ ይላቸዋል፡፡ ዕረፍት ያለው በመቀመጥ ውስጥ ሳይሆን እያዳመጡ በመሮጥ ውስጥ ነው፡፡ 
ዮሐንስ እስከ ዛሬ ሰዎች ስለ ኃጢት አጥምቋል፡፡ ኃጢአት የሌለበትን ጌታ ግን በምን ምክንያት ያጠምቀዋል? ዮሐንስ እስከ ዛሬ በእግዚአብሔር ስም አጥምቋል፤ እግዚአብሔርን ግን በማን ስም ያጠምቀዋል? የአገራችን ሊቃውንቶች ዮሐንስ ሲያጠምቀው ‹‹የቡሩክ ልጅ፣ የብርሃን ገላጭ ይቅር በለን አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ የዘላለም ካህን ነህ›› ብሎ አጠመቀው ይላሉ፡፡ ገለጻቸው የተዋበ ነው፡፡
በእውነት እንግዶችን በመቀበል ስንተጋ አንድ ቀን እንደ አብርሃም ራሱን እግዚአብሔርን እንቀበለዋለን፡፡ ኃጢአተኞችን ተግተን ለንስሐ  ስናበቃ ንጹሑን ጌታ እናገለግለዋለን፡፡ ትእዛዙ ሲፈጸምለት ባለ ትእዛዙ ጌታ ራሱ ይመጣል፡፡ ፈቃዱ ባለችበት እግዚአብሔር አለ፡፡ ዮሐንስ የሌሎችን የሕይወት ድካም፣ የኃጢአት ውድቀት፣ የኑሮ ጭንቀት ይሰማል፡፡ ኢየሱስን ባየ ጊዜ እርሱም ለማረፍ ስፍራውን ለመልቀቅ ፈለገ፡፡ ሌሎችን ባገለገልን ቁጥር በእጥፍ ጸጋ ይበዛልናል፡፡ ጸ መክሊት ነው፡፡ መክሊት የሚበዛው ሲነግዱበት /ሲሠሩበት/ ነው፡፡
‹‹ኢየሱስም መልሶ አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው›› /ማቴ. 3÷15/፡፡
እኛ ወደ ጽድቅ ድንበር መጠጋት አቅቶን ጽድቅን እንደ አስጠቂ ቆጥረናት ይሆናል፡፡ ጌታ ግን ጽድቅን ሁሉ ፈጽሟል፡፡ ከሰው መንገድ ርቆ ሄዷል፡፡ ከመልካሞች የመልካምነት ርቀትም አልፏል፡፡ ጽድቅን የሚፈጽሙ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ከዚህስ አላልፍም በቃኝ እያሉ ግን ይቆማሉ፡፡ ጌታችን ግን ጽድቅን ሁሉ ፈጽሟል፡፡ ጽድቅ የተራበን ከማብላት የጠለቀ ትርጉምና አኗኗር አለው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ስለ ጽድቅ ብዙ ይናገራል፡፡ ጠሊቅ ከሆነ የጽድቅ አኗኗሮች ሁለቱን እንመልከት፡-
የመተው ጽድቅ
‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበረ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች፡፡ እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ›› /ማቴ. 1÷18-19/፡፡ 
አንዲት ሴት ያለ ጋብቻ ጸንሳ ከተገኘች ሕጉ እንደሚያዘው ለሸንጎ ማሳወቅና ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባት፡፡ ይህ የኦሪቱ እውነት /ጽድቅ/ ነው፡፡ ጽድቅ ግን ከዚህም ይልቃል፡፡ የኦሪቱ ጽድቅ ማጋለጥ ሲሆን የአዲሱ /የጸጋው ዘመን/ ጽድቅ ግን መሸፈን ነው፡፡ ዮሴፍ እንደ ኦሪቱ ቢገልጣት ጻድቅ ነበር፡፡ እርሱ ግን የአዲሱን ጽድቅ ፈጸመ፡፡ ‹‹ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ›› /ማቴ. 1÷19/፡፡ በዚህም ምክንያት እውነቱን እግዚአብሔር ገለጠለት፡፡
‹‹እውነቱ መውጣት አለበት›› እንላለን፡፡ እውነት ግን አንዲት ወይንም ይህቺ ብቻ ናትን? እውነት የሰውዬው ስህተት ገሀድ መውጣቱ ብቻ ነውን? ኢየሱስ ክርስቶስም እውነት ነው፤ ሀቀኝነቱ ወይንም ጻድቅነቱ ማጋለጥ ብቻ ነውን? በስውር መምከር ካልተቻለ መተውም ጽድቅ ነው፡፡ የምንመራው በየትኛው ጽድቅ ነው? በማጋለጥ ኦሪታዊ ጽድቅ ወይስ በመሸፈን ሐዲሳዊ ጽድቅ?
ታናሽን የማክበር ጽድቅ
‹‹እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና›› /ማቴ. 3÷15/፡፡ ጌታችን ዮሐንስ በከለከለው ጊዜ ታናሽን የማክበር ጽድቅ መፈጸም እንዳለበት ተናገረ፡፡ ታላላቆችን ሹሞችን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ጽድቅ ግን ከዚህም ያልፋል፡፡ ከኃጢአተኞች ጋር በዮርዳኖስ ወንዝ መሰለፍ ይህ ታላቅ ጽድቅ ነው፡፡ ፀሐይ በቆሻሻ ቦታ ብትወጣም አትቆሽሽም፡፡ ኢየሱስም በኃጢአተኞች መካከል በመገኘቱ ቅድስናው አልጎደፈም፡፡ ከእርሱ የሚያንሰውን ዮሐንስ አጥምቀኝ ብሎ ዝቅ ማለቱ ይህም የላቀ ጽድቅ ነው፡፡ 
ታናሾቻችንን ማክበር፣ ለሕፃናት ሳይቀር ከበሬታ የመስጠት ጽድቅን መለማመድ ያስፈልገናል፡፡ ድሆችን የተረሱትን ማዳመጥ፣ ዓለም በናቀቻቸው ሰዎች ውስጥ ያለውን ጥልቅ ምሥጢር ማዳመጥ ይህ ጽድቅ /እውነተኛነት/ ነው፡፡ እኛስ የሌሎችን ነገርን የመሰወርን፣ የሚያንሱንን የመፈለግ ጽድቅ ተገኝቶብን ይሆን?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም