የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጾም

እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁ ጾም /ዐቢይ ጾም / በሰላም አደረሳችሁ !!
ጾም ለመንፈሳዊው ዓለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ።  በእግዚአብሔር ፊት ቊርጥ ልመናን ለማቅረብ ፣ እውነተኛ ንሰሐን ለመፈጸም ፣ የዕንባ መሥዋዕትን ለማቅረብ ፣ በትሕትና ጸጋን ለመቀበል ጾም አስፈላጊና ግዴታ ነው ።
ጾም አዋጅና በአዋጅ ሊደረግ የሚገባው ነው ።  በስውር የሚደረግ ጾም አለ ።  ግለሰቡ ጉዳዩን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብበት ፣ መጾሙንም የማያሳውቅበት ነው ።  የማኅበር ጾም ግን በአዋጅ የሚደረግ ፣ ስለ አገርና ስለ ወገን የእግዚአብሔር ማዳን የምንጠባበቅበት ነው ።  ጾምን ሰው ለራሱ ያውጃል ፣ ቤተ ክርስቲያንም ታውጃለች ።
ጾም ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት የምናዋርድበት ነው ።  በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ልመና ግዳጅን ይፈጽማል ።  ፈጽሞም መልስ ያገኛል ።  ጾም ለትሑት ጸሎት እጅግ ይረዳል ።  ሥጋን በማድከም ወደ ነፍስ ልዕልና የምናቀርብበት ምሥጢር ነው ።  ጾም የርኅራኄ መገኛ ፣ የዕንባ ምንጭ ፣ የትሕትና መፍለቂያ ናት ።  ራሳችንን በጾም ስናዋርድ እግዚአብሔር ከፍ ያደርገናል ፣ ምሪትን ይሰጠናል ። (ዕዝ. 8÷21) ።
ጾም አዋጅን የሚሽር አዋጅ ነው ።  በመጽሐፈ አስቴር ላይ እንደምናነበው በአይሁድ ላይ የታወጀው የሞት አዋጅ ወደ ሹመትና ክብር የተለወጠው በጾምና በጸሎት ነው ።  (አስቴ. 4÷3) ። የተዘጉ ደጆች እንዲከፈቱ ፣ በአገር በወገን ላይ የመጣ የክፉ አዋጅ ማለት ሞት ፣ መከራ ፣ በሽታ እንዲወገድ ጾም ጸሎት ትልቅ መሣሪያ ነው ።  የጾምና የጸሎት ትጥቅ አይታይም ፣ የሚታየውን ጠላት ግን ያሸንፋል ።
ጾም ይቅር ብለን ይቅርታ የምንለምንበት ነው ። እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን (ይቅርታን) ይወዳል ።  በጾም በጸሎት የእግዚአብሐር ይቅርታ ስንለምን ይቅር እያልን ፣ በረከቱን ስንለምን ለተራቡት እያበላን ሊሆን ይገባዋል ።  አማኝ ከጫጫታ ስፍራ ገለል ብሎ ፣ ከዘፈን ይልቅ ዝማሬን መርጦ ፣ ከወሬ ይልቅ በጸሎት ተጠምዶ እንዲባረክ ጾም ቀስቃሽ ደወል ነው ።
ዘፈንና ዝሙት እንዲሁም ስካር በአገር ሲበዛ ቀጥሎ ትልቅ ጥፋትና ልቅሶ ይኖራል ።  “የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም“ እንዲሉ ዘፈን ሲበዛ መጾምና ማልቀስ ይገባል ።  እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾሞ የበሬ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥጋም እንድንርቅ ነው፡፡  ያለ ቢላዋ በሐሜት የሰውን ሥጋ መብላት ጾምን እንደ መግደፍ ነው ።  ሠራተኞቻችንን እያስለቀስን ፣ ደመወዛቸውን እየበላን ፣ ቂምን በልባችን ሞልተን የምንጾመው ጾም የረሃብ አድማ እንጂ ጾም አይባልም (ኢሳ. 58 ÷ 5-6) ። የጾም መሰናዶው ነጠላን ማጽዳት ሳይሆን ልብን ማጽዳት ፣ በልኳንዳ ቤት ደጆች መሰለፍ ሳይሆን ንስሐ መግባት ፣ ዕቃን ማጣጠብ ሳይሆን ከቂም መጽዳት ነው ።  የጾምን መረቁን እንጂ ሥጋውን አልበላንምና ከንቱ ልፋተኞች ሆነናል ።  ምክንያቱም ለጾማችን የምናደርገው ዝግጅት ሜዳዊ እንጂ ውስጣዊ አይደለምና ። ትልቁ ጾም ከኃጢአት መከልከል ነው ።  ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ኃጢአት ነው ። በአገራችን በጾም መግቢያ መውጫ ስካርና ዝሙት ይደራል ።  ቅበላውና ፋሲካው በኃጢአት በመሆኑ ከጾም የሚገኘውን በረከት ማግኘት አልቻልንም ።
ጾም ለእግዚአብሔር እንጂ ለታይታ አይደለም ። (ዘካ. 7÷5) ።  ከማኅበረሰቡ ላለ መለየት ፣ ሆዳም ላለ መባል ፣ ዶሮ ለመባረክ መጾም ከንቱ ጾም ነው ። የምንጾመው ከእግዚአብሔር ዋጋ ለማግኘት እንጂ ጾመኛ ለመባል መሆን የለበትም ።  የጾምና የጸሎት ዋጋ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ።  በጾም አፌ ክፉ አታናግሩኝ ለማለት መጾም አይገባንም ። ባንጾምም ክፉ መናገር አይገባንም ። በጾማችን የሚታየን እግዚአብሔር ነው? ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል ።
ጾም እውነትና ሰላም ያለበት ነው ። በጾማችን ወራት ከድሆች ጋር ማሳለፍ ብድር መመለስ ለማይችሉ ቸርነት ማድረግ ይገባል ። እኩዮችን ሲጠሩ መኖር እውነተኛነት አይደለም ። ከእኛ ባነሰ ኑሮ ለሚኖሩት እጅን መዘርጋት ግን የጾም መገለጫው ነው ።  ጾም ሁለት እጆች አሏት ። አንደኛው የጾም እጅ ጸሎት ፣ ሁለተኛው የጾም እጅ ምጽዋት ነው ። ጾም ሁለት አንደበት አሏት፡፡  አንደኛው ቃላችን ሲሆን ሁለተኛው ዕንባችን ነው ። ጾም እውነትን ትፈልጋለችና ለተጨቆኑ ምስኪኖች ፣ ፍርድ ለተጓደለባቸው እስረኞች ፣ በግፍ ከገዛ አገራቸው ለሚሰደዱ አቤት የምንልበት ፣ ግፍ አድራጊዎችን በቃችሁ ብለን የምንገስጽበት የእውነት ሰይፍ ነው ። ጾም ሰላም ስለሆነ ግለሰብ ከግለሰብ ፣ ማኅበራትን ከማኅበራት ፣ አገር ከአገር ጋር የሚታረቁበት ፣ እንዲታረቁም ጥረት የምናደርግበት ሊሆን ይገባዋል ። እርቅን የጠሉና የገፉ ጾምን የማወጅ አቅም የላቸውም ።  ስለዚህ ታርቀው የሚያስታርቁበት እንዲሆን ሊያስቡ ይገባቸዋል ። የጾም የመጨረሻው ውጤት ወይም በዓሉ እግዚአብሔር በሚሰጠን መልስ ሆታና ደስታ ነው ። መልስ እንዲመጣ ግን እውነትና ሰላም መርጋት አለባቸው ። ግፈኞች ፣ የሌላውን ድርሻ እየነጠቁ የሚበሉ ፣ ለሀብታም እያደሉ ለድሃ የሚፈርዱ ሊገሰጹ ፣ ንስሐ ሊገቡ ይገባል ። ያ ሲሆን የጾም ዳርቻው ተድላና ደስታ ይሆናል ። (ዘካ. 8÷19) ።
የነነዌ ሰዎች ምሕረትን የተቀበሉት በሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ነው ። የመጣው መዓት የተመለሰው ፣ የራቀው ምሕረት የቀረበው በአንድ ልብ ሆነው አቤት በማለታቸው ነው ።  እኛ ግን ዓመት ሙሉ እየጾምን ለምን በረከት ራቀን ብለን ጠይቀን አናውቅም ።  ስለዚህ ይህን ዐቢይ ጾም ስንጾም፡-
1.  ርዕስ ልንይዝ
2.  ይቅር ልንባባል
3.  ንስሐ ልንገባ ይገባናል ።
ብዙ አንገብጋቢ ርዕሶች አሉን ። የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መክፈል ፣ እርቅን የማይወዱ ሰዎች መሙላታቸው ፣ በአገር ያለው የኑሮ ውድነት ፣ ድሆች በደንብ እየደኸዩ መሆናቸው ፣ ፍትሕና ፍቅር መጥፋቱ ፣ የገንዘብ ጣኦት በምድራችን መቆሙ ፣ የዝናብ መታጣት ፣ የበሽታ መበርከት ፣ የአንድነት መጥፋት ፣ የትዳር መናጋት ፣ የልጆች ዋልጌነት ፣ የሐሰት መምህራን መብዛት ፣ እግዚአብሔርን መርሳት…….  ይህ ሁሉ የጾምና የጸሎት ርዕሳችን ነው ። ክርስቲያን መንፈሳዊ ኃይልን አጥቷል ። በየደረሰበት ውጊያ አሸናፊ ሳይሆን ተሸናፊ ሆኗል ። ይኸውም፡-
·       ቃሉን ስለማያጠና
·       የጸሎት ሰዓቱ ስላልተከበረ
·       ጾምና ጸሎትን ስለተወ
·       ምጽዋትን ስላስቀረ
·       የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ስላልቻለ …. ነው ።
 በእውነት ጾመን በዓሉ ተድላ እንዲሆን ፣ በጾም ዘርተን በፈውስ እንድናጭድ እግዚአብሔር ይርዳን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ