መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ፈተና ነው

የትምህርቱ ርዕስ | ፈተና ነው

በአፍ ያመኑትን ሃይማኖት በሥራ መካድ ፣ የመሰከሩለትን እውነት መልሶ መጣል ፈተና ነው ። ውጤትን እያሰቡ ማገልገል ፣ ምድራዊ ዋጋን እየሻቱ በእግዚአብሔር ቤት መመላለስ ፈተና ነው ። እየበሉ መራብ ፣ እየጠጡ መጠማት ፣ ተቀብሎ እንዳልተቀበለ ማጉረምረም ፣ ያለውን ከጎደለው አለማወቅ ፈተና ነው ። ለእውነት አንቀላፍቶ ለስሜት ታማኝ መሆን ፈተና ነው ። መልካሙን ሰው አጠልሽቶ ማየት ፣ ንጹሑን ወገን መጠራጠር ፣ በጎ ንግግርን በክፉ መተርጎም ፈተና ነው ። ሰውን በጉልበት መልካም አደርጋለሁ ብሎ መነሣት ፣ ትላንት ባደረጉት መልካም ነገር መጸጸት ፈተና ነው ።

ስለማናውቃቸውና በመለኮት ፊት ስለማንከሰስባቸው ሰዎች አስተያየት ሲሰጡ መዋል ፣ ስለ ማንም በጎ መናገር አለመቻል ፈተና ነው ። በየደረሱበት መስገድ ፣ አምልኮን እየወደዱ የሚመለከውን አምላክ አለማወቅ ፈተና ነው ። እንዴት እኔ ይህን አደርጋለሁ ብሎ መመጻደቅ ፣ ለቁጭት እንጂ ለንስሐ አለመብቃት ፈተና ነው ።

እግዚአብሔር የከደነለትን የወንድምን ገመና ማውጣት ፣ በሌሎች ምሥጢር መሳለቅ ፣ በፍቅር ቀን ለጠብ ቀን ብሎ መረጃ መያዝ ፈተና ነው ። ባማረ ፊት የተቀበሉንን ፣ ክፉውን ቀን ያሻገሩንን ረዳቶች መርሳት ፣ መመሪያን ትቶ መሪን መከተል ፣ ማምለክን ፈልጎ እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመፈለግ ፈተና ነው ። ይሙትም ይዳንም ሲባል ማጨብጨብ ፣ ለሕሊና ትቶ ለሆድ ማደር ፈተና ነው ። ሰውዬው የኮራበትን ክፋት አለማመን ፣ ዝንጀሮን አቆነጃለሁ ብሎ ቀለም መጨረስ ፈተና ነው ።

ጊዜ ተሰጥቶት ጊዜ መጠበቅ ፣ የቀበሩትን ቂም ቆፍሮ ማውጣት ፣ ለአምላክ የሚሰጠውን ፍቅር ለሰው መስጠት ፈተና ነው ። ራሱን የሰጠንን አምላክ እያመለክን ፣ ገንዘባችንን ለአሥራትና ለመባ መሰሰት ፈተና ነው ። ባልጋበዙን በሰው ጉዳይ መግባት ፣ የታገሡን ላይ ሌላ ጭነት መጨመር ፣ የተኰነነውን ኃጢአት ጽድቅ ለማድረግ መታገል ፈተና ነው ። የራስን ችግር አጉልቶ የሌላውን ረሀብ አሳንሶ ማየት ፣ በመጣው ነገር መማርን ጥሎ ማማረር ፈተና ነው ።

ራስን መምራት ከሥልጣን በላይ መሆኑን ዘንግቶ ሥልጣን መሻት ፣ ክፉ ሳይመጣብን ወደ ክፉ መሄድ ፣ እግዚአብሔር ያድነኛል ብሎ በበሽታ መጫወት ፈተና ነው ። በገነት መሰቃየት ፣ በምቾት መጨነቅ ፣ ከመልካም ሰውና ከመልካሙ ነገር እንከን መፈለግ ፣ ባሌ የማይመታኝ ስለማይወደኝ ነው ፣ ሚስቴ የማትሰድበኝ ስለማትቀናብኝ ነው ብሎ ፣ ጦር አውርድ ጸሎት መያዝ ፈተና ነው ። ጭር ሲል አልወድም ብሎ ነገር ማለኳኮስ ፣ በሚዋደዱ መካከል ጠብ መዝራት ፈተና ነው ። ሲሄድ የሚኖረውን ሰው አትሂድብኝ ብሎ ማልቀስ ፣ የወደደንን አምላክ ትቶ በጠሉን መደነቅ ፈተና ነው ። ያለፉትን ሰዎች ላሉት ሰዎች ማማት ፣ በማይመጣው ትላንት ላይ ማቀድ ፈተና ነው ።

አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !  በምን እየተፈተንን እንደሆነ እንኳ አናውቅምና ከፈተና አድነን !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም