ናዝሬት
“በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ ።” ሉቃ. 1 ፡ 26-27 ።
መልአኩ ገብርኤል የተላከው ናዝሬት ወደምትባል የገሊላ ከተማ ነው ። ገሊላ ሰሜናዊ የእስራኤል ግዛት ነው ። እስራኤል ሦስት ታላላቅ ግዛቶች ነበሩአት ። ደቡቡ ይሁዳ ፣ ማዕከሉ ሰማርያ ፣ ሰሜኑ ገሊላ ይባላል ። በገሊላ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞች አንድዋ ናዝሬት ናት ። ናዝሬት በብሉይ ኪዳን ስምዋ አልተጠራም ። ታዋቂ የሆኑ ድርጊቶች ያልተከናወኑባት ፣ ስመ ጥር ሰዎች ያልወጡባት ፣ የጦርነትም የዕድገትም መዝገበ ቃላት ያላወቃት አነስተኛ መንደር ነበረች ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመወለዱን ብሥራት የላከው ወደዚህች ወደ ናዝሬት መንደር ነው ። የናዝሬት መንደር የተናቀች ነበረች ። ወደ ተናቀችው መንደር ታላቅ የምሥራች መጣ ። ጌታችን ለልደቱ ቤተ ልሔምን እንደ መረጠ ፣ ለፅንሰቱ ናዝሬትን መረጠ ። እርሱ ከሚጠራበት ስም ገናናው “የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚለው ነው ። የተናቁት ወዳጅ ፣ የምስኪኖች አለኝታ መሆኑን የሚያሳይ ስም ነው ። ናዝሬት በቅርብ ከተሞች እንኳ የተናቀች ለመኖሪያነት የማትመረጥ አነስተኛ መንደር ነበረች ። ማንም የማያውቃት ያቺ ናዝሬት መላው ዓለም ያውቃታል ። የተናቁትን ማክበር እግዚአብሔር ያውቃል ። ትላንት የተናቁ አገራትና ከተሞች ዛሬ እየተወደዱ መጥተዋል ። በተቃራኒው የተከበሩ አገሮችና መንደሮች ተንቀዋል ። በዓለም ላይ በጣም ደምቀው የደበዘዙ ከተሞች ብዙ ናቸው ። ሮም ፣ ባቢሎን ፣ እስክንድሪያ ፣ አንጾኪያ ፣ ቍስጥንጥንያ/ኢስታንቡል ፣ አኵሱም በጣም ስመ ጥር የነበሩ የዓለማችን ከተሞች ናቸው ። ዛሬ ግን ደብዝዘዋል ። ናዝሬት ግን በትንሽ ጀምራ በመላው ዓለም ትታወቃለች ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ በሚለው መጠሪያ ከአምላክ ጋር ስትነሣ ትኖራለች ።
እግዚአብሔር የተናቁ አገሮችን ያከብራል ። ዛሬ አገራችን ከዓለም መጨረሻ ሁና ብትታይ እንኳ እግዚአብሔር ቀኝ ኋላ ዙር ያለ ቀን አንደኛ ትሆናለች ። ይህ እንዲሆን የምሥራቹን መቀበል ያስፈልጋል ። ወንጌል በራሱ በእግዚአብሔር ፣ በአበው ፣ በነቢያት ፣ በካህናት ፣ በመልአክ ፣ በድንግል ማርያም ፣ በሐዋርያት የተሰበከ ትውልደ ሐረግ ያለው መልእክት ነው ። ይህን ወንጌል አምኖ መኖር ክብርን ያሰጣል ። እግዚአብሔር ናዝሬትን ብቻ ሳይሆን ታናሽ ብላቴና የምትሆነውንም ድንግል ማርያምንም አከበረ ። እርስዋ ራስዋ አክባሪነቱን ስትገልጥ፡- “እነሆም ፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤” አለች ።(ሉቃ. 1 ፡ 48) ። ከዛሬ ጀምሮ የሚለውን እናስተውል ። ከዚህ ቀን በፊት ማንም የተዘጋጀላትን ክብር አላወቀም ነበር ። እርስዋም አላወቀችም ነበር ። አሁን ግን የአምላክ እናት ሁናለችና ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት እንደሚሏት ተናገረች ። እግዚአብሔር የተናቁ መንደሮችን ፣ የተናቁ ሰዎችን ያከብራል ። እመቤታችን አሁንም በተደነቀው ጸሎትዋ፡- “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና” ብላለች ። እግዚአብሔር ያያል ። የተናቁትን ለክብር ቀን ያስባል ። ሔዋን ተዋርዳ ነበር ፣ አሁን አያት ። በልጅ ልጅዋ በድንግል ማርያም በኩል የሔዋን ውርደት ተካሰ ። ሔዋን ካመጣችው ውርደት ለድንግል ማርያም የሆነው ክብር በለጠ ። በዚህም የሴት ዓለም ከበረ ።
በኮልታፋ ምላሳችን ሰዎች ይንቁን ይሆን ? እስራኤልን እየመራ ያወጣው ሙሴ ኮልታፋ ነበር ። እግዚአብሔር ከአፌ ቅቤው ከአሮን ይልቅ ሙሴን መረጠ ። እንደ ሰው ቢሆን ቃላተኛው አሮን የሕዝብ መሪ ፣ ሙሴ ደግሞ ካህንና ጸሎት አሳራጊ በሆኑ ነበር ። እንደ ሰው ቢሆን ብሉያትን ያጠና ጳውሎስ መምህረ አይሁድ ፣ ጴጥሮስ መምህረ አሕዛብ ተደርገው በተደለደሉ ነበር ። ኃይላችን የማያግዘው ፣ ድካማችን የማይመልሰው እግዚአብሔር በእውነት ድንቅ ነው ። እኔም በልቡናዬ ጉልበት ተንበርክኬ አመሰግነዋለሁ ። ደካማ የሆነ የአካል ክፍል ስላለን ፣ ቁመናችን ስለማይማርክ ሰዎች እንደ ናቁን እናስብ ይሆን ? እነ ኤልያብን ትቶ አጭሩን ዳዊትን ፣ እነ ቀያፋን ጥሎ ቁመተ ትንሽ ዘኬዎስን የመረጠ አምላክ ዛሬም አሠራሩ አልተለወጠም ። ከተናቀች አገር በመምጣታችን እየተጨነቅን ይሆን ? እግዚአብሔር ከፍታን ሲያወርሰን ማንም አያግዘውም።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 8 ቀን 2018 ዓ.ም.