ባልንጀርነት ማለት ነው ። ባልንጀራ የሥጋ ዝምድና የሌለው ፣ ቤተሰብ ያልሆነ ግን በአሳብ የተጣመረ ነው ። ለዚህ ፍቅር የግሪኩ ስያሜ ፊልዮ የሚል ነው ። የቤተሰብ ግንኙነት በመወለድ ብቻ የምናገኘው ሲሆን ፈጽሞ የአሳብ አንድነት ላይኖረን ይችላል ። ፊልዮ ወይም ባልንጀርነት ግን የእኛ ምርጫ ያለበት ነው ። መስፈርቱም የአሳብ አንድነት ነው ። የሥጋ ትስስር ሳይሆን የነፍስ ጥምረት ነው ። ባልንጀራ ከንስሐ አባት በላይ የራሳችንን ምሥጢር የምንነግረው ሊሆን ይችላል ። ባልንጀራ አስፈላጊ ነው ። የቅርብ ቤተሰብ እንዲያክም ሙያው አይፈቅድም ፣ ምክንያቱም በመጨነቅ ትክክለኛውን መድኃኒት ላያዝ ይችላል ። ለትዳራችን ፣ ለቤተሰባችን የማንነግረውን ለባልንጀራ ልንነግር እንችላለን ። የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑ ከሌሎች ጋር መኖሩ የውድ ሳይሆን የግድ ነው ። ሔዋን ለአዳም የአሳብ ረዳት ሁናም ተፈጥራለች ። ከሚስትነት ባሻገር ጓደኛም ነበረች ። ሰውም ከትዳር ውጭ ባልንጀራ ይኖረዋል ። ይህ ባልንጀርነት በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት ። መልካም ባልንጀርነት እንዳለ ሁሉ ክፉ ባልንጀርነትም አለ ። ሞት ወደ ዓለም የገባው በማይገባ ባልንጀርነት ነው ። የሔዋንና የእባብ ባልንጀርነት የጥፋት መነሻ ሁኗል ።
ባልንጀርነት የመተዋወቅ ውጤት ነው ። አንዳንዴ ቀስ እያለ እንደሚፈስ ወንዝ እየተግባባን እንመጣለን ። ኃይለኛና ክፉ የሚመስሉን ሰዎች መጀመሪያ ላይ ይከብዱናል ፣ ቆይቶ ግን መልካም ሰዎች መሆናቸውን እንረዳለን ። በዕለቱ መልካም የመሰለን ሰው ቆይቶ እውነተኛ ማንነቱ ሊወጣ ይችላል ። የብዙ ሰው ሕይወት ጭምብል/ማስክ ያለበት ነው ። ጭምብሉን ሲያወልቅ እውነተኛ መልኩ ይወጣል ። ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር ያጣራል ። ስሜት ዛሬ ወይም አሁን ካልሆነ ይላል ። እውነት ግን ጊዜ ይፈልጋል ። የምንቀርበው ለመራቅ ስላልሆነ ጊዜ መስጠት መልካም ነው ። አንድን ሰው ስንቀርብም ስለዚያ ሰው ጥናት ለመሥራት ሳይሆን የራሳችንን ፍቅር ለማፍሰስ መሆን አለበት ። እናት ጡትዋን ስታጠባ ቅለት ይሰማታል ፣ ሁላችንም ፍቅርን እንድንሰጥ ሁነን ስለ ተፈጠርን የምንወደው ሰው ያስፈልገናል ። አሊያ ስሜታችን የተረበሸ ፣ እውቀታችን እርግጠኝነት ያጣ ፣ ውሳኔአችን የተዛባ ይሆናል ። ፍቅር መኖርን ምክንያታዊ ያደርገዋል ።
ባልንጀርነት የራሱ የሆነ መስፈርት አለው ። የምንወዳጀው ሰው ምሥጢር የሚጠብቅ ፣ ከሌላ ሰው ጋር የማያማን ፣ ሽንገላ የሌለበት ፣ ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሆን አለበት ። ባልንጀራ ከጸደቀ የሚያጸድቅ ፣ ከተኰነነ የሚያስኰንን ነው ። ባልንጀራችን ሃይማኖታችንን ፣ ሥነ ምግባራችንን የሚያስጠብቅ መሆን አለበት ። የባልንጀርነት ግዴታው መመካከር ፣ በደስታ በኀዘን ቀድሞ መገኘት ፣ ለአደራ መብቃት ፣ ወዳጅን አሳልፎ አለመስጠት ነው ። ባልንጀርነት የሚፈተንበት ጊዜ ብዙ ነው ። ጌታችን በክፉ ሰዓት እግሩን ያጠበው ጴጥሮስ ክዶታል ፣ የጎረሰው ይሁዳ ጠላት እየመራ አምጥቶበታል ። “ክፉ ቀን አይምጣ ወዳጅ እንዳላጣ” ይባላል ። ክፉ ቀኖች የምንጠብቃቸውን ሰው ጠላት ያደርጋሉ ፣ የማንጠብቃቸውን ሰዎች ደግሞ ያቀርባሉ ። ክፉ ቀን የማጣሪያ ቀን ነው ። ክፉ ቀንን መውደድ ያለብን ከውሸት ኑሮ ስለሚገላግሉን ነው ።
ባልንጀራን በይቅርታ ማለፍ ወሳኝ ነው ። ክርክርና ወደ ቤተሰብ የሚደርስ ቀልድ ወዳጅነትን ይጎዳልና መጠንቀቅ ይገባል ። በግል የተወራን ነገር አስቂኝ ቢሆን እንኳ ለሦስተኛ ሰው ስንናገር ጥንቃቄ ይፈልጋል ። እኛ ጋ የተራቆተው ሰው ሁሉም ሰው ጋ መራቆት አይፈልግም ። ባልንጀራችንን አብዝተን ወደ ቤተሰብና ወደ ትዳር ባናቀርብ መልካም ነው ። የእነርሱ ብቻ እንድንሆን የሚፈልጉ ቤተሰቦቻችን ሊለዩን ይችላሉ ። በተለይ የትዳር አጋሮች የበለጠ የተወደደ የመሰላቸውን ወዳጅ ሊመቱና ሊያርቁብን ይችላሉ ። የክፉ ቀን መድኃኒት ነውና ባልንጀራን ደብቀን ማስቀመጥ ይገባል ። ሁለታችን አብረን የፈጸምነውን ምሥጢር ለማንም መንገር አይገባም ። ሌላ ወዳጅ አግኝተን ብናወራ የእኔንም እንዲሁ ያወራል ብሎ ይታዘበናል ፣ ይርቀናል ።
ባልንጀራችንን ፊቱን በማየት ብቻ ችግሩን መገንዘብ አለብን ። ምናልባት እየተራበ ከእኛ ጋር ሊስቅ ይችላል ። ለጉቦና ለጉራ የምንሰጠውን ብናስብ ለወዳጃችን ምንም አላደረግንም ። አብሮን ያለ ወዳጅ ፣ የሚያማክረን ዋጋው ብዙ ነው ። በሰለጠነው አገር ወዳጅነት ስለ ተመታ ሁሉም ነገር የሚገኘው ከሱቅ ሁኗል ። ምክር እንደ ሸቀጥ ከሱቅ ይገዛል ። ባልንጀራ ግን ወዶ የሚመክረን እንጂ አስከፍሎ የሚመክረን አይደለምና ብልጫ አለው ። ክርስትና ዓላማው በክርስቶስ ወንድምና እኅቶችን ማብዛት ነው ። ፊልዮ ይህ መተሳሰብ ያለበት ፍቅር መግለጫ ነው ። ፊልዮ ከተቃራኒ ጾታ ፍቅር ፣ ከቤተሰብ ፍቅር የተለየ መልክና ዓላማ አለው ። የጋራ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ ነገ ላይ አስገዳጅ ነገር የሚያመጡ ግንኙነቶች ፊልዮ አይደሉም ፣ ብድር መመላለስ ያደክማል ። መልካም የሆነ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ያ ፍቅር ወደ ትዳር ያድጋል ብለው ያስባሉ ። ጥሩ ጓደኞች ጥሩ የትዳር አጋሮች ላይሆኑ ይችላሉ ። ምክንያቱም ባልንጀርነት መስማማት ሲሆን ትዳር ግን በመቃረን የሕይወትን ሚዛናዊነት መጠበቅ ነው!
የባልንጀርነት ፍቅር ትልቅ ጉዳት እየደረሰበት ነው ። ስለዚህ ብዙ ሰዎች ለትዳራቸውና ለቤተሰባቸው የማያካፍሉት ጭንቀት ውስጥ ብቻቸውን ያልፋሉ ። ባልንጀርነት የዓለምን ችግር ያቃልላል ። የማይዘልቁ ጓደኝነቶችም እየበዙ ነው ። ብዙ ቅርርብ ሳይጀመር ያልቃል ። ይህ የእኛን ዘመን አስፈሪ ያደረገው ሁነት ነው ። እባክችሁ ያረፈደ ፍቅራችሁ እንዲውል ፣ የዋለ ፍቅራችሁ እንዲያመሸ ፍቀዱለት ! የምንሄደው የፍቅር ዓለም ወደሆነው ወደ ሰማይ ነውና ፍቅርን እንለማመድ ።
ይቀጥላል
መስከረም 20 ቀን 2019 ዓ.ም.