በተቃራኒ ጾታ መካከል ያለ ፍቅር ፣ የባልና የሚስት መሳሳብ ኤሮስ ተብሎ ይጠራል ። ኤሮስ በጥንቱ የግሪክ ፍልስፍና የታወቀ ቃል ነው ። በውጫዊ ውበት በመሳብ ይጀምርና ወደ እውነተኛው ውበት የሚገሰግስ ፍቅር ነው ። ኤሮስ በግሪክ አፈ ታሪክ የፍቅር አምላክ ስም ነው ይባላል ። ኤሮስን እንደ ጣዖት ከወሰዱት በዚህም ዘመን እየተመለከ ይገኛል ። ይኸውም የወንድና የሴት ግንኙነት በፈቃደ ሥጋ ላይ ብቻ እንዲመሠረት እያደረገ ነው ። የፈቃደ ሥጋ ግንኙነት ያለ ፍቅር ሊደረግ የሚችል ፣ ለስሜት የሚከፈል ዋጋ ነው ። ሰዎች ያለ ፈቃደ ሥጋ ግንኙነት ሊፋቀሩ ይችላሉ ። ፈቃደ ሥጋ እየፈጸሙ ደግሞ ፍጹም ላይዋደዱ ይችላሉ ። የሰው ልጅ ለእንስሳዊ ጠባዩ የሚገዛበት ፣ መሬት የሆነው ጠባዩ ሲያይልበት የሚፈጽመው ነው ። ፈቃደ ሥጋ በጋብቻ ሕጋዊ ሊሆን ይገባዋል ። ምክንያቱም ቅድስናው ካልተጠበቀ በምድርም በሰማይም ታላቅ ቅጣት ስለሚያመጣ ነው ። ፈቃደ ሥጋ እንደ ሸቀጥ ገንዘብ ያለው እንዲገዛው ተደርጎ አልተሠራም ። ሰው ራሱን የሚሰጥበት በመሆኑ ከዚያ በፊት የሃይማኖትና የአሳብ አንድነት ያስፈልገዋል ። ውኃ እንኳ መስመሩን ካላገኘ የተለያዩ ገዳይ ነፍሳት ማፍሪያ ይሆናል ። ፈቃደ ሥጋም ሕጋዊ ካልሆነ ለብዙ ጥፋቶች መገኛ ይሆናል ።
ዘመናችን ፍቅር ብሎ የሚጠራው የፈቃደ ሥጋን ግንኙነትን ነው ። ፈቃደ ሥጋ ለባልና ለሚስት የተሰጠ ስጦታ እንጂ ለጨዋታ የተሰጠ ልቅ ሕይወት አይደለም ። ፈቃደ ሥጋ ለሁለት በእጮኝነት ጉዞ ላይ ላሉት እንኳ ያልተፈቀደ ነው ። ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው ከጋብቻ በፊት ያለ ማንኛውም ግንኙነት ዝሙት ነው ። ፈቃደ ሥጋ ለጋብቻ የተሰጠ ስጦታ ነው ። በጥንቱ የግሪክ አምልኮ ለአጋንንትን ከሚቀርቡ መሥዋዕቶች አንዱና ዋነኛው ዝሙት ነው ። ልጆቻቸውን በእሳት ውስጥ እያሳለፉ መሥዋዕት የሚያቀርቡ እንደ ነበሩ ሁሉ ራስን በእሳት ውስጥ እያሳለፉ ደጋግሞ መሥዋዕት መሆን በዝሙት ምክንያት የሚመጣ ነው ። ዝሙት በራስ መጨከን ነው ። ዘመናዊው ዓለም ዝሙትን ያቆነጀ ነው ። ከእያንዳንዱ ድርሰትና ድራማ ውስጥ ማሳረጊያው ወይም ማጣፈጫው ዝሙት ነው ። ሰው ለፈቃደ ሥጋው ብቻ ዋጋ ከሰጠ ፍቅር እየጠፋ ይመጣል ። ወንዱ ሴትዋን ሲያያት እንዲሁ ማድነቅ ይችላል ። ማድነቁን በማፍረስ መደምደም የለበትም ። ዘላቂ ግንኙነት እንጂ የዕለት ግንኙነትን መጀመር የሌላውን ሕይወት አደጋ ላይ መጣል ነው ። ብዙ ሴቶች እኅቶቻችን ደጋግመው በዕድሜአቸው ሁሉ እንዲሞቱ የሆኑት በዚህ የስሜት መንገድ ስለ ተጎዱ ነው ። ሴቶችን ስናስብ እንዲማሩና ፣ በዓለሙ ላይ ተገቢ ክብርና ቦታ እንዲይዙ ፣ ብቁ እንዲሆኑ ማሰብ ይገባል ። የሴቶች ሕይወት ሲቀደስ ለተባረከ ትውልድ መገኛ ይሆናል ።
ፈቃደ ሥጋ ሕጋዊ ካልሆነ ምድር ልትሸከመው የሚከብዳት መከራ ይመጣል ። ሰብአ ትካት ወይም በኖኅ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች በንፍር ውኃ የጋዩት በዝሙት ነው ። ሰብአ ሰዶም በእሳት የወደሙት በዝሙት ነው ። ፈቃደ ሥጋን ባለመቆጣጠር ሰዎች ለሱስ ፣ ለገንዘብ ብክነት ፣ ለጤና እክል ፣ ለባከነ አእምሮ ፣ ለክብር አልባነት ይዳረጋሉ ። ሰብሳቢና አሳዳጊ የሌላቸው ልጆች ይወለዳሉ ። የተዘባረቀ ዓለም የሚፈጠረው ፈቃደ ሥጋን መግራት ባለመቻል ነው ። የሚታየው ዓለም ሁሉ የማይታይ ውድቀቱ ዝሙት ውስጥ አለ ። የባልና የሚስት ግንኙነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ። ጋብቻ የሚባለውም የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ነው ። ኤሮስ የእነዚህን መሳሳብ የሚገልጥ የፍቅር ቃል ነው ። ቃሉ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም አሳቡ ግን ይኖራል ። አዳምና ሔዋን በገነት የኖሩት በድንግልና ነው ። ስለዚህ ፈቃደ ሥጋ በጋብቻ ውስጥ ዋናውና ወሳኙ ነገር አይደለም ማለት ነው ። ከዚያ በፊት የሃይማኖትና የአሳብ አንድነት ያስፈልጋቸዋል ። የሃይማኖት አንድነት በጋብቻው እግዚአብሔር እንዲከብር ነው ። የአሳብ አንድነቱ ደግሞ መረዳዳት እንዲኖር ነው ። በተለያየ ምክንያት በጋብቻ እየኖሩ ፈቃደ ሥጋን የማይፈጽሙ ሰዎች አሥራ አምስት ፐርሰንት እንደሚደርሱ ይነገራል ። ይህ አንድ ትዳር የሚቆመው በፈቃደ ሥጋ ነው ብሎ ማመን ትክክል አለመሆኑን ያሳየናል ።
የባልና የሚስት ፍቅር የአጋፔ ፍቅር ቢኖረው ይመረጣል ። ምክንያቱም ይቅርታ ለማድረግና ለኑሮ ዋጋ ለመክፈል በጣም ስለሚረዳ ነው ። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በአጋፔ ፍቅር እንደወደዳት ባልም ሚስቱን በአጋፔ ፍቅር ሊወዳት ይገባል ። ጉድለት እንኳ ቢኖራት አሟልቶ የሚያያት ይህን ፍቅር ሲይዝ ነው ። በባልና በሚስት መካከል የፊልዮ ፍቅር ሊኖር ይችላል ። ምክንያቱም በአሳብ መረዳዳት ስላላቸው ነው ። የቤተሰብ ፍቅርም ወደ ልጆቻቸው ስለሚሻገር ስቶርጅ የተባለው ፍቅርም ይኖራል ። ባልና ሚስት የሥጋ አንድነት ስላላቸው የእነርሱ ፍቅር ከሌሎች ፍቅር የተለየ ነው ። ከሌሎች ጋር የነፍስና የመንፈስ አንድነት ሊኖረን ይችላል ። የሥጋ አንድነት የፈቃደ ሥጋ ጥምረት ግን በባልና በሚስት መካከል ብቻ የሚፈጸም ነው ። የአጋፔ ፍቅር እንዲሁ የሆነ ነው ። ከመስፈርት ውጭ ሁሉን የሚያቅፍ ነው ። የፊልዮ ፍቅር የአሳብ መቀራረብ ነው ። የስቶርጅ ፍቅር ተፈጥሮአዊ ስለሆነ ሁሉም ቤተሰቡን ይወዳል ። የኤሮስ ፍቅር ግን መሳሳብ ያለበት ወደ ውስጣዊ ውበትና እውነት የሚገሰግስ ነው ።
የባልና የሚስት ፍቅር መቀራረብ ፣ መተማመንና አንዱ ላንዱ ጥበቃ በማድረግ ላይ ሊመሠረት ይገባዋል ። አሊያ ፍላጎቴን ልፈጽም እንጂ ስለሌላው አይመለከተኝም በሚል መንገድ ከተያዘ ከሥጋ ጨዋታ የማያልፍ ሌላውንም በመስበር የሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ብቻ ይሆናል ። ሴት ልጅ ለወንድ ልጅ የፈቃደ ሥጋ ማሽን ተደርጋ አልተፈጠረችም ። ወንዱም እንዲሁ ለዘር ብቻ የሚፈለግ አይደለም ። ወንዱ ሴትዋን እየደፈረ ትልቅ በደል ውስጥ መግባት አይገባውም ፣ ሴትዋም ከወለደች በኋላ ወንዱን አባራ ለመኖር ማቀድ አይገባትም ። በሴትና በወንድ መካከል ያለው ግንኙነት ቅድስናውንና ክብሩን ማግኘት አለበት ። ይህ እንዳይሆን ስሜታዊነት ፣ የገንዘብ ፍቅር ፣ የመብት እንቅስቃሴዎች ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶች ፣ የዘመናዊው ዓለም የትዳር ትንታኔ እያወከው ይገኛል ።
ትዳር የሁለት ፍጹማን ሰዎች ኅብረት ሳይሆን ሁለት ይቅር የሚባባሉ ሰዎች ጥምረት ነው ። የይቅርታን ልብ ያላዳበረ ሰው ለትዳር ብቁ አይደለም ። ራስንና ሰዎችን ይቅር ማለት መማር ያስፈልጋል ። ትልቁ ጀግንነት ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ያሸከሙንን የበደል ሸክም መጣል መቻል ነው ። የበደለንን ሰው በአካል እየራቅን በልባችን ውስጥ ግን ነጻ ክፍል እንሰጠዋለን ። ለሥጋችን እያሰብን ለነፍሳችን አላሰብንም ። በትዳር ውስጥ እኛን ለማስደሰት ሲሉ ያሳዘኑን ሰዎች እንዳሉ ማሰብ አለብን ። አንዳንዴም እንደ ሣራ ወደ ዝሙትና ወደ ስህተት የሚመሩ ሚስቶች ሊሆኑ ይችላሉ ። ያላሰበችውን በማሳሰብ ሚስታቸውን ወደ ጥፋት የሚመሩ ባሎች አሉ ። ምንድነው ጥፋቴ ማለት ትዳርን ውጤታማ ያደርገዋል ። በቃል የጀመረው ፍቅር በትዳር ያድጋል ፣ በመተማመን አክሊሉን ይወስዳል ። ባልና ሚስትን አንድ የሚያደርጋቸው የጾታ መጨፍለቅ ሳይሆን በችግር ፊት አንድ መሆናቸው ነው ። የልብን በር ካልከፈቱ እንደ ትዳር ያለ የስቃይ ስፍራ ሊኖር አይችልም !
ይቀጥላል
መስከረም 23 ቀን 2019 ዓ.ም.