መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕፃናት ልብ » እግዚአብሔር መልካም ነው !

የትምህርቱ ርዕስ | እግዚአብሔር መልካም ነው !

ጌታችን ትምህርት ከሚያንሱንም እንደሚገኝ ነግሮናል ። የሰማይ ወፎች ፣ የምድር አበቦች ለሰው ልጅ የእምነት መምህራን ናቸው (ማቴ. 6 ፡ 26-28) ። እንዲሁም ሕፃናት ቀላል የሆነውን የኑሮ ዘይቤ የምንማርባቸው አስተማሪዎቻችን ናቸው (ማቴ. 18 ፡ 3) ። ሁሉንም ማክበር ያለብን ትምህርቱ እንዳያመልጠን ነው ። ከማናከብረው መማር አንችልምና ። ሁሉም ሕፃን ላይሸመግል ይችላል ፣ ሁሉም ሽማግሌ ግን ሕፃን ነበረ ። የልጅነት ጊዜ የሚናፍቅ ደግሞም የማይገኝ ነው ፣ ክርስቲያን በመሆን ግን ይገኛል ። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደ ሕፃናት በመሆን እንገባለን ፣ ሕፃን በመሆን አንገባም ፣ እንደ ሕፃናት በመሆን ግን እንገባለን ። ሕፃን ልጅ ወላጆቹ ክፉ ያደርጉብኛል ብሎ አይሰጋም ። አንድ ሕፃን እንዲህ ካሰበም ጤንነቱ ተውኳል ማለት ነው ። በእውነትም የዘመኑ መጨረሻ ሁኖ ፍቅር ሲቀዘቅዝ የወላጆች ፍቅር ግን አልተፈተነም ፣ ዛሬም አልወደቀም ። ወላጆቻቸው ላይ ጉዳት ስላደረሱ ልጆች አልፎ አልፎ እንሰማለን ፣ ልጆቻቸው ላይ አደጋ ያደረሱ ወላጆችን ግን አንሰማም ። ወላጅ ለልጁ ሁልጊዜም መልካም ነው ። ሕፃንም ወላጆቹ መልካምን ብቻ ያደርጉልኛል ብሎ ያስባል ። እንዲህ በማሰቤ ተታልዬ ነበር ብሎ የተጸጸተ ጎረምሳም ጎልማሳም አናውቅም ። እግዚአብሔር መልካም አምላክ ነው ። ለእኛ ክፉ የሆነ ነገርን አይሰጠንም ። የምናልፍበት ሕይወት አስቸጋሪ ቢሆን እንኳ ፍጻሜው መልካም አሳብ ነው ።

ወላጅ ልጁን ገና በጨቅላነቱ ክትባት ሲያስከትበው ልጁ ያለቅሳል ። ልጁ ስለ አሁን ሕመሙ ሲያለቅሰ ወላጅ ግን የሚያስበው ስለ ዘለቄታው ሕመምና ሞት ነው ። ትልቁን ሕመም በትንሽ ሕመም እንዲያልፈው ወላጅ በልጁ ይጨክናል ። ገና በስምንተኛው ቀን ልጁን ያስገርዛል ። ግዝረቱ በስለት መቆረጥ ፣ የአካል መውደቅ ፣ የደም መፍሰስ ያለው ነው ። የልጁ ፈቃድ አልተጠየቀም ። ወላጅ ግን ስለሚወደው ልጁን ያስለቅሰዋል ። የግዝረቱ ዓላማ ለውበት ፣ ለጤንነት ነው ። ይህን ሥርዓት ለመፈጸም የሳሱ ወላጆች አሉ ፣ ልጆቹ አድገው ግን ይወቅሷቸዋል ። እግዚአብሔርም ለሚያም ሥርዓት አሳልፎ ይሰጠናል ። በዚህም ለእኛ ያለውን የወደፊት አሳቡን እንረዳለን ። ለዛሬ ጉዳይ ብሎ ልጁን በመርፌ ወይም በግዝረት ምላጭ የሚያስለቅስ ወላጅ የለም ። እግዚአብሔርም ፍጻሜ ላለው ነገር ልጆቹን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ ያደርጋል ። መንግሥት ወታደሩን የሚያሰለጥነው ለዛሬ ጦርነት ሳይሆን ለወደፊት ትግል ነው ። እግዚአብሔር ከጦርነቱ በፊት ልጆቹን ያሰለጥናል ።

“ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።” (ኤር. 29 ፡ 11) ። ይህ ቃል የተነገረው ሰባ ዓመት በምርኮ ለነበሩት አይሁዳውያን ነው ። ምንም እንኳ ለዚህ የበቁት በኃጢአታቸው ምክንያት ቢሆንም እግዚአብሔር ክፉውን ወደ በጎ ይለውጠዋል ። ወላጅ ለልጁ የሚያስበውን ትልቅ ነገር ያውቃል ። ልጁ ቤት ንብረት ተዘጋጅቶለት ሳለ ከረሜላ አልገዛም አሉኝ ብሎ በወላጅ ላይ የምሬት ልቅሶ ያለቅሳል ። እኛም ሕይወትን የሰጠንን ጌታ በእንጀራ ፣ መንግሥተ ሰማያትን ያዘጋጀልንን አምላክ በቁሳቁስ እንጠራጠረዋለን ። የአባታችን የሆነው ሁሉ የእኛ መሆኑን እንረሳለን ። የእግዚአብሔር አሳብ ፍጻሜ አለው ። ብዙ ነገሮች ፍጻሜአቸው እንደ ጅማሬአቸው ደማቅ አይደለም ። በእልልታ ተጀምረው በኡኡታ የሚያልቁ ነገሮች ብዙ ናቸው ። “መጨረሻው ይመር” የሚል አስተዋይ መራቂ ነው ። ጉዳዩ ብቻ ሳይሆን የሰውዬው የራሱም መጨረሻው ማማር አለበትና “መጨረሻህን ያሳምርልህ” ተብሎ ይመረቃል ። የእግዚአብሔር ዕቅድ መጨረሻው ያምራል ። ወተት በቧንቧ እናስገባላችኋለን ብለው በመልካም ቃል የመጡ ገዥዎች ደም በቧንቧ ሲልኩልን መጨረሻው አለማማሩ ያሳዝነናል ። ሰው በመረጠው እንዲቀጣ የተፈረደበት ፍጡር ነው ።

የእግዚአብሔር አሳብ ተስፋ አለው ። አይሁዳውያን ምንም በምርኮ አገር ቢሆኑ መዋለድ አለባቸው ። ምክንያቱም ሕይወት ይቀጥላልና ። የሚታያቸው የፈረሰው አገራቸውና መቅደሳቸው ቢሆንም አሁንም ተስፋ አለ ። ዛሬን ያጨለሙ ጠላቶቻቸው ቢሆኑም ነገን ብሩህ የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው ። ተስፋ አለ ፣ ተስፋ አያልቅም ፣ የተስፋ መሠረቱ እግዚአብሔር ነው ። ብዙ ሞክረን ጥቂት አላሳካንም ብለን ተስፋ እንቆርጣለን ። ከሠራነው የተሠራልን ፣ ከለወጥነው ጉዳይ የተለወጠው ልባችን ይበልጣል ። በእውነት ችግራችን እንደ ድሮው ሊሆን ይችላል ፣ እኛ ግን እንደ ድሮ አይደለንም ። ከተለወጠ ኑሮ የተለወጠ ሕይወት ይሻላል ። የእግዚአብሔር አሳብ የሰላም አሳብ ነው ። በምድር ላይ የምንኖረው በእምነት ነው ። ምግብ ቤት ገብተን የምንበላው እምነት ስላለን ነው ። ባናምን ኖሮ በረሀብ እንሞት ነበር ። ሐኪም ዘንድ የምንሄደው በእምነት ነው ። ሥራ የምንጀምረው በሚቀጥለው ወር ደመወዝ ይሰጡኛል ብለን አምነን ነው ። ለምድር ኑሮ እምነት ወሳኝ ነው ። የማይታመነውን ሰው ዛሬም ድረስ በአንዳንድ ነገሮች ፍጹም እናምነዋለን ። የሰማይ ኑሮ የበለጠ እምነት ያስፈልገዋል ። የሚታመነውን አምላክ ማመን ይገባናል ።

ደግሞ ምን ሊያመጡ ይሆን ? የሚል ስጋት የሚገጥመን ጊዜ አለ ። መንግሥታት ሲሰባሰቡ እንሰጋለን ፣ ሰዎች እፈልግሃለሁ ሲሉን እንታወካለን ። የእግዚአብሔር አሳብ ግን የሰላም አሳብ ነው ። እኛ ከእስራኤላውያን የተሻለ ቁመና ላይ ልንሆን እንችላለን ። ቢያንስ በምርኮ አገር አይደለንም ፣ አገራችን አልተቃጠለም ፣ መቅደሳችንም አልፈረሰም ይሆናል ። ኤር. 29፡11 እስራኤልን የሚያጽናና ከሆነ እኛን የበለጠ ሊያጽናናን ይገባል ። አሁን ያለንበት ሁኔታ የመጨረሻው መዳረሻችን አይደለም ።

አንድ ሰው የዛፍ ችግኝ ተከለ ። ከተከለው በኋላ ግን ችግኙ ይጠወልግ ፣ ወደ ሞትም ይሄድ ነበር ። ወዲያም የሚያብብ መስሎት ነበርና ሊቆርጠው ተነሣ ። በዚህ ጊዜ አንድ አትክልተኛ “አትቁረጠው አሁን የምታየው የዛፉ መጨረሻ አይደለም ፣ ሥሩ ከመሬት በታች እየተጓዘ ነው” አለው ። ጊዜ እያለፈ ሲመጣ ዛፉ እየጠነከረ ፣ ቅጠል እያወጣ ፣ ቅርንጫፉን እየዘረጋ መጣ ። ተስፋ የተቆረጠበት ዛፍ ትልቅ ዛፍ ሆነ ። እኛ የአሁኑን እናያለን ፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀልንን ማየት ግን አንችልም ። እንደ ሕፃናት እንሁን ! አባታችንም ፈጣሪያችንም የሆነውን አዳኝ እንመነው ።

ይቀጥላል
መስከረም 27 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ