አገርህ ከድታህ፣ ወገንህ ለግድያው ስም ሰጥቶ መሣሪያ የወደረብህ ፣ ጥፋትህ ጠፍቶህ ፣ ያልበደልከውን ካስ ስትባል ግራ የገባህ ፣ ጥፋትህንም ገዳይህንም ዛሬ ስታያቸው ሕልም ዓለም ውስጥ የገባህ ፣ እመጣለሁ ብለህ ደውለህ ሳትደርስ የቀረኸው አንተ ብላሽ ገለል በል ከፊቴ ። ግንድ ተማፅኖ በሚዳንበት አገር የአምላክህን ስም ጠርተህም የሚራራ ያጣኸው አንተ ጀምር ገለል በል ከፊቴ።
ምድር የጌታ ነው ብለህ ተቀምጠህ የሰው ሲሆንብህ ፣ መንገድ የእግዜር ነው ተብለህ አድገህ ሰው አምላክ ካልሆንሁ ሲልህ ጭልም ያለብህ አንተ እሸት ገለል በል ከፊቴ ። ከመቼው አድገህ ለሞት በቃህ፣ ለማታውቀው አያትህ ዕዳ ከፋይ ለመሆን በቃህ። አንተ ሠርክ በጅምር ገለል በል ከፊቴ ። እንዳላለቅስልህ ለማልቀስም ቀን ይፈልጋል ፣ የማልቀሻዋ ቤትም ቤተ ፈያት /የወንበዴ ዋሻ/ ሆናለች።
ወንድ በጠላው ዘመን ተወልደህ ፣ ወጣትነትህ እንደ ዕዳ በሚቆጠርበት ምድር ተገኝተህ ፣ በቅጡ መኖር በቅጡ መሞት አቅቶህ የተሰቃየኸው አንተ ጎበዝ ገለል በል ከፊቴ። ስለ ወንድ ልጅ አምላክ ብለህ ስትለምን የተጨከነብህ ፣ እናትህን ልጅህን እያሰብህ በሜዳ የቀረኸው ፣ ገዳይህ በደሉ እንዳይጠፋ ፎቶ አንሥቶ የሚገድልህ ፣ ቪድዮ ቀርፆ ላይበላህ የሚያርድህ አንተ ወጣት ገለል በል ከፊቴ ።
የወጣት ሞት ፣ የወንድ ልጅ አበሳ ሃምሳ ዓመት ሞላው ፣ በነጻ ኖረህ በዋጋ ትሞታለህ። ለመብል የረሳህ ለጥይት ያስታውስሃል ።
አንተ በሥጋ ሞትህ፣ እኛ ግን በሕሊና እንሞታለን ። አንተ አንድ ጊዜ ሞትህ ቋሚው ደጋግሞ ይሞታል። የሰው አንገት አንድ ነውና ሰው የሆነ ሁሉ ያዝናል። አንተ ስቃይህ ለአንድ ሰዓት ነው፣ ገዳዮችህ ግን ዘመናቸው ሁሉ የስቃይ ነው።
ደምህን ደመ ኢየሱስ ይዋቀሰዋል !
አልተሸካከፈም ያገሬ አዝመራው ፣
ዛላው ዛላው ወድቋል በየጎዳናው ።
የሚፈሰው ደም ይብቃ!!!