መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ቅድስት ማርያም » ቅድስት ማርያም -2

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ማርያም -2

የሰው ልጆች በያዙት ነገር የማይረኩት ሁልጊዜም የሚመጣውን የሚናፍቁት መንግሥተ ሰማያት ሲደርሱ እንዲያርፉ ሁነው ስለ ተሠሩ ነው ። ሰይጣን ሰዎችን በሽንገላ ከጣለበት ነገር አንዱ ገንዘብና ሥልጣን ቢኖራችሁ እርካታን ታገኛላችሁ ብሎ በማታለል ነው ። ሰዎች ገንዘብና ሥልጣንን ሲይዙ የሚገጥማቸው ባዶነትና እዚያ ለመድረስ የከፈሉትን ተጋድሎ ማስታረቅ አቅቷቸው ራሳቸውን በተስፋ ማጣት ይጎዱታል ። የሰው ልጆችን በእቅፉ ሊያስጠጋና ዘላለማዊ መልስ ሊሆናቸው አምላክ ወደ ምድር መምጣት ፈለገ ። የአምላክ ጉብኝት ዕለታዊና ያልተቋረጠ ቢሆንም ይህ መምጣት ግን በሥጋ መገለጥ ነው ። በክርስቶስ መምጣት ዓለም መልካም አልተደረገለትም ፣ መልካም ሆነለት ። የማያቋርጥ ደግነት ፈሰሰ ። ሁለት መልእክተኞች ከንጉሡ ፊት ፊት ይሄዳሉ ። አንደኛው ሰማያዊ ፣ አንደኛው ምድራዊ ነው ። ምድራዊ ጥሪት ሁለቱም አልነበራቸውም ። በሰማያዊ ጸጋ አሸብርቀዋል ። እነርሱም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና መጥምቁ ዮሐንስ ናቸው ።

ለአምላክ መወለድ ፣ ለሰው ዘር መዳን የምሥራች እንዲነግር የተላከ መልአኩ ገብርኤል ነው ። መልአክ በወደቀ ጊዜ አምላክ መልአክ ሁኖ ለምን አላዳነም  ሰው በወደቀ ጊዜ እንዴት ሰው ሆነ አላለም ። መልአኩ በሰው መዳን ደስተኛ ነበረ ። የአምላክ ሰው መሆን ሂደት በሰማይ በተሰማ ጊዜ ታላቅ ደስታ ነበረ ። ዓለም በተፈጠረበት ቀን ዓለም እንዲድን ፣ ብሥራት እንዲነገር መልአኩ ተጠራ ። ባለቤቱ ሰማይን ሳይሰናበት በምድር ይገኛል ። ምድርን እንግዳ ሳይሆንባት በሥጋ እንግድነት ይገለጥባታል ። የእግዚአብሔር ልጅነቱን ሳይለቅ የሰው ልጅ ይባላል ። ለአምላክ ልጅ የሰው ልጅ መባል እንግዳ ነው ። ካለንበት የመጣው ካለበት ሊያደርሰን ነው ።

ሕዝብና አሕዛብ ሁሉ በዘመናት የናፈቁት ክርስቶስ በሥጋ እየመጣ ነው ። እንግዳን ቤተ ዘመድ ይቀበለዋል ፣ እልልታ ይሰማል ። አንዲት ድንግል ግን በቤትዋ ሳይሆን በማኅፀንዋ ተቀበለችው ። ጉዳዩ እስከ ጊዜው ምሥጢር ነበርና የምሥጢር መዝገብ የሆነችው ማርያም ሰወረችው ። እርስዋ ከሴቶች የተለየች ናት ። ሔዋን ምሥጢር አውጥታ ሞትን ጋበዘች ፣ ምሥጢር ጠባቂዋ የሕይወትን ፍሬ አስገኘች ። የመምጣቱን ዜና የሚናገሩ የተቀደሱ ትንቢቶች በእኔ ይፈጸማል ብላ አንድም ቀን አስባ አታውቅም ። ከሥጋዋ ሥጋ ፣ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ፣ አገሯን አገሩ አድርጎ ሊወለድ መጣ ።

አስደናቂው ነገር ከአባቱ የተወለደው መለኮታዊው ልደት የዘመን መቀዳደም የለውም ። እናቱ በሥጋ ልደት እየቀደመችው ቢሆንም የፈጠራት ግን እርሱ ነው ። እናቱን የጦረ ልጅ እናውቃለን ፣ እናቱን የፈጠረ ልጅ ግን ታይቶ ተሰምቶ አያውቅም ። አባቱም በዘመን ያልቀደመው ፣ በክብር ያልበለጠው ይህ ሕፃን እንደምን ያለ ነው !! ዘመን የሌለው ሁኖ ሲኖር ሳለ በዘመን ቋጠሮ ውስጥ የገባው ፣ እርሱ ዘመን የለሽ እርሱ ዘመነኛ ነው ። ዘመናችንን ሊቀድስ ፣ ዓመተ ፍዳን ወደ ዓመተ ምሕረት ፣ ዓመተ ኵነኔን ወደ ዓመተ ጽድቅ ሊለውጥ መጣ ። የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ ። ለአባቱ የበኵር ልጅ የነበረው ለእናቱም የበኵር ልጅ ሆነ ። ሁለት አባት የለውምና ያለ ወንድ ዘር ተወለደ ። በቀዳማዊ ልደቱ እናት ፣ በደኃራዊ ልደቱ አባት የለውም ። በቀዳማዊ ልደቱ ከአምላክ የተገኘ አምላክ ነው ፣ በደኃራዊ ልደቱ ፍጹም ሰው ነው ። አምላክነቱ ሰውነቱን ሳያጠፋ ፣ ሰውነቱም አምላክነቱን ሳይሰበስብ አንዱ ክርስቶስ በተዋሕዶ ይኖራል ። እግዚአብሔር አንድነት መገለጫው ነው ። ሦስት አካል አንድ አምላክ ነው ፤ አሁንም ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካል ፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሁኖ በአንድነት ይኖራል ። አንድ ስንሆን እግዚአብሔርን እንመስላለን ።

የእግዚአብሔርን የፍቅሩን ውበት ፣ ድሀና ባለጠጋ ፣ ጥቁርና ነጭ ሳይለይ ሁሉም ይናፍቀው ነበር ። ይህን የውበት ፀሐይ ቀና ብሎ ለማየት ሰው በኃጢአት ጎበጠ ፤ ዝቅ ብሎ ያየው ዘንድ በበረት ተወለደ ። ሕፃናትን ለማስተማር በእነርሱ መጠን ዝቅ ብሎ በቁመታቸው ልክ ተንበርክኮ መናገር ውጤታማ ያደርጋል ። እውነተኛው የሕይወት መምህር በእኛ ሥጋ ተገለጠ ። ጣዖትን ከሚሻ ሕፃንነት አዳነን ። ስምዖን የቀሬናው በድንገት መስቀል ተሸከመ ። ድንግል ማርያም ግን በድንገት የአምላክ እናት አልሆነችም ። መሢሑን እጅግ የምትናፍቅ ፣ የብሉይ ኪዳም ትንቢቶችን የምታጠና ፣ በእግዚአብሔር ቤት እግዚአብሔርን የምትጠባበቅ ነበረች ። እግዚአብሔር ንጉሥ ነውና ከለመኑት በላይ ይሰጣል ሲባል ይሰማ ነበር ። ያለመኑትንም እንደሚሰጥ በድንግል ማርያም ታየ ። እርሱም ወላዲተ አምላክ መባል ነው ። ነቢይነትም ፣ ሐዋርያነትም ፣ ሰማዕትነትም ለብዙዎች ይሰጣል ። ለድንግል ማርያም የተሰጠው ግን የማይደገም ጸጋ ነው ።

በአምላክ ሰው መሆን ኃይሉ ፣ ዳኝነቱ ፣ ፍርዱ ፣ ችሎታው ሳይሆን ፍቅሩ ተገለጠ ። የሰው ልጅ እግዚአብሔር ነፍጎኛል ብሎ ከሰይጣን ጋር አምላኩን አምቶ ነበር ። ስለዚህ በፍቅሩ ተገለጠ ። እኛ የአባትነት ፍቅር የሚያድርብን ልጅ ስንወልድ ነው ፣ እግዚአብሔር ግን የዘላለም አባት ነው ። ፍቅርንም በእኛ አልተለማመደም ፣ የዘላለም ፍቅር ነው ። መለኮት እኔ ልሙት ብሎ የመጨረሻውን መሐላ ለወዳጆቹ ምሎ ነበር ። በባሕርዩ አይሞትምና መሐላው ተንጠለጠለ ። የሚሞትበትን ሥጋ ለብሶ በመስቀል ላይ ዋለ ። የመጨረሻውን መሐላና ፍቅር በተግባር ገለጠ ። እኔ ልሙት ያሉን ብዙዎች ናቸው ፣ ሞተው ግን አላሳዩንም ።

ሩቅ ሁኖ ማዘዝ ቀላል ነው እያሉ ሰዎች አጉረምርመው ነበርና በቅርብ ተገኝቶ ታዘዘ ፣ የሰጠውንም ሕግ ፈጸመ ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የሌለበት የዘላለም አባት ፣ የሚመጣው ንጉሥ ፣ የሚያሳርፈው የሰላም አለቃ ፣ የሚራራው ሊቀ ካህን ፣ ልቅደምልህ የሚል መሥዋዕት ፣ እጅግ ልበ ሰፊ ፣ ዝንጉዎችን የሚታገሥ ፣ የኃጢአተኞች ወዳጅ ፣ ሸፍኖ የሚሠራ ፣ አጋልጦ የማያዋርድ ፣ የሕመምተኞች ጤና ፣ የጥያቄዎች ሁሉ መልስ ፣ በለጋስነት ሁሉን የሚሰጥ ፣ የቆሰለ ልብን በደሙ የሚፈውስ ፣ ነፍስን የሚገዛ የሰማይ ልዑል ፣ አገር ለሌላቸው አገራቸው ፣ በግፍ ለሚገደሉት ተበቃያቸው ፣ የወደቁትን በተስፋ ቃል የሚያናግር ፣ አገሩ እዚህ ነው የማይባል ፣ ሁሉም መልኬ የሚለው ፣ የዘር ልዩነትን ያጠፋ ፣ የድሆችን ንቀት ያስወገደ ነው ።

የዚህ ታላቅ ጌታ እናት ነሽና ማርያም ሆይ ደስታ ይገባሻል ! ክርስቶስ ሆይ የታመመው አልድን ፣ የወጣው አልገባ ያለበትን ይህን ዘመን ስለ እናት ስለ ማርያም ብለህ ለውጠው !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 5 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ