“በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ፥ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ ።” ሉቃ. 1 ፡ 26-27 ።
ዓለም ሁሉ በታላቅ ኀዘን ፣ ለሞትም በተሸነፈ ልብ ይኖር ነበር ። መዳን በሰዎች ፣ ሰዎችም በሚያደርጉት ጥረት የማይገኝ መሆኑ ታወቀ ። የእንስሳት መሥዋዕትም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞትን ማስቀረት አልቻለም ። መሥዋዕተ እንስሳ ለጊዜው ቍጣን ቢያበርድም የገነትን በር ከፍቶ ጽኑ ይቅርታን ማምጣት አልቻለም ። የአበው ተስፋ ፣ የነቢያት ትንቢት ፣ የአዋቂዎች ሱባዔ ዘገየ እየተባለ ይታሰብ ነበር ። ፈሪሳውያን በታላቅ ቁጭት ሕዝቡን ለመሢሑ መምጣት ያነሣሡ ነበር ። ከእነርሱ የተከፈሉ ኤሤናውያንም በሙት ባሕር ዳርቻ በኩምራን ገዳም ተወስነው ፣ በጾምና በጸሎት ጸንተው ፣ መጻሕፍትን እየጻፉ መሢሑን ቶሎ ና እያሉ ይናፍቁት ነበር ። የእግዚአብሔር ጠባዩ ይህ ነው ። እያለ ና ይባላል ። በልብ ተቀምጦ ይናፍቃል ። የእግዚአብሔር የፍቅር ልብ በሰው ላይ አዝኖ ነበር ። ካሣ ሊከፈል ፣ መዳን ሊፈጸም ፣ ሰውም ወደ ቤቱ ሊመለስ ፣ የዳግም ልደት ምሥጢር ሊጀመር የግድ ያስፈልጋል ። ሰው እንደ ወጣ እንዲቀር የእግዚአብሔር ዘላለማዊ አሳብና ጽኑ ፍቅሩ አላስቻለውም ። እንደ ራሱ የጠፋው ሰው እንደ እግዚአብሔር መዳን አለበት ። ሰው እግዚአብሔርን መምሰል አለበት ተብሎ ስለ ቅድስና ሲነገረው ነበር ። ሰውም በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ እየተባለ ዘወትር ይዘመራል ። አሁን ግን እግዚአብሔር ሰውን ሊመስል ፣ የሰውንም ሥጋ ሊለብስ ዘመን ደረሰ ።
ይህ ሥጋ በፈላስፎች እንደ ርኵስ ተቆጥሮ ነበር ። ሥጋንም በማጎሳቆል አምላክን ደስ ማሰኘት የሚል የግሪካውያን ፍልስፍና ተስፋፍቶ ነበር ። ሥጋን በመልበሱ ሥጋን ሊያከብረው ፈለገ ።
በቀጠሮው ማርፈድ የማያውቅ በሰዓቱ ፣ በቦታው የሚገኝ እግዚአብሔር በስድስተኛው ወር በናዝሬት ገሊላ ተገኘ ። እግዚአብሔር የዘገየ የሚመስለን በእኛ ሰዓት ስለምንጠብቀው ነው ። የእግዚአብሔር ተስፋ በእኛ ጊዜ ቢፈጸም ይጎዳናል ፤ ተስፋው በራሱ ጊዜ ሲፈጸም ይጠቅመናል ። እስራኤልን በምድረ በዳ እየመገበና ዐርባ ዓመት እያስጠበቀ በከነዓን ደግሞ አሞራውያንን ለንስሐ ጊዜ እየሰጠ ነበር ። እኛን እዚህ ሲያቆየን እነዚያን ለንስሐ እየጠበቀ ነው ። እኛ በትዕግሥት ስንጠብቅ እግዚአብሔር ደግሞ የታገሣቸው ሰዎች አሉ ። የእኛ ተስፋ በእኛ ጊዜ ሲፈጸም የእነርሱ ንስሐ ይቀራል ። የእኛ በረከት የዘገየ የመሰለን የሌሎች ሕይወት እየዳነ ስለ ነበር ነው ። ሐኪሙ በቀዶ ጥገና ክፍል ቢዘገይ የእኛ ኪኒን ግን በደቂቃ የሚታዘዝ ፣ ዓመታዊ ምርመራችን ጊዜ የሚሰጥ ነው ። ዓመታዊ ምርመራችን ዘገየ ስንለው እዚያ ጋ ዛሬ ካልሠራላቸው የሚሞቱ ወገኖች ገጥመውት ነው ። እግዚአብሔር የዘገየ ሲመስለን እየፈጠነ ፣ የረሳን ሲመስለን ታላቅ ፍቅርን እየገለጠ ነው ።
በራሱ ጊዜ የሚሠራው አምላክ መልአኩ ገብርኤልን ሊልክ ወደ ታላቁ ዙፋን ጠራው ። ከብዙ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል የተመረጠው ለምን ይሆን ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ከ600 ዓመታት በፊት መሢሑ የሚወለድበትና የሚሰቀልበት የተሰፈረ የሱባዔ ቍጥር ለነቢዩ ዳንኤል የተገለጠው በቅዱስ ገብርኤል በኩል ነው (ዳን. 9 ፡ 24-27) ። አሁን የሱባዔው ፍጻሜ መሆኑን ለመግለጥ ወደ ድንግል ማርያም ተላከ ። በስድስተኛው ወር ሲል በስድስት መቶኛው ዓመት ማለትም ነው ። ለዳንኤል በተገለጠ በስድስት መቶኛው ዓመት መልአኩ ገብርኤል ለድንግል ማርያም ተገለጠ ።
በባቢሎን ግዞት የነበሩት በዚህ የሱባዔ ምሥጢር ደስ አላቸው ። መሢሑ መምጣቱን መስማት የልብ ድጋፍ ሆናቸው ። እግዚአብሔር ታዳጊ ነው ብለው ዘመሩ ። ቀጥሎ የሚታያቸው የፈረሰው መቅደስ መሠራት ፣ ማኅበረ እስራኤል እንደገና ለዝማሬ መቆም ነው ። እስራኤል በባርነት እንደ ተጋዙ ዓለም በሙሉ ወደ ሲኦል ተግዞ ነበር ። እስራኤልን ወክሎ የምሥራቹን ዳንኤል እንደ ሰማ የሰውን ዘር ወክላ ድኅነተ ዓለምን የሰማች ድንግል ማርያም ናት ። ድንግል ማርያም የሰማችው ለመላው የሰው ዘር የሚሆነውን የምሥራች ነው ። ነቢዩ ዳንኤል ግን የሰማው ለእስራኤል ብቻ የሆነውን የምሥራች ነው ። የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው ነቢያት ይባላሉ ፣ ድንግል ማርያምም የእግዚአብሔር ቃል መጥቶላታልና ነቢይት ትባላለች ። ለእስራኤል ብሔራዊ ጥያቄና ለሰው ዘር ዓለም አቀፋዊ እንቆቅልሽ መልሱ አንድ ነበረ ። እርሱም የመሢሑ መምጣት ነው ።
ነቢዩ ዳንኤል በታላቅ ሱባዔ ሳለ የመሢሑ መምጣት በተሰፈረ ዘመን ተገለጠለት ። ድንግል ማርያም በታላቅ ዝግጅት ላይ ሳለች ፣ በጸሎትና ቃሉን በማንበብ ስትተጋ የምሥራች መጣላት ። እንደ ንጉሥ ሳኦል በመንገድ የምሥራች የመጣላት ሳትሆን ለቃሉ ፍቅር ሕይወትዋን ሰጥታ ሳለች የምሥራቹ መጣ ። ቃሉን ስታፈቅር ቃለ አብ ኢየሱስ ከእርስዋ ሰው ሊሆን መጣ ። ቃልን ሰምታ ቃልን ፀነሰች ። የአምላክ አገልጋይ መሆን ስትሻ ወላዲተ አምላክ ለመሆን በቃች !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም.