መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » አትተወኝ ለራሴ

የትምህርቱ ርዕስ | አትተወኝ ለራሴ

ብዙ ቀርቶት የደረሰ ይመስለዋል ፣ ምንም አያውቅም አውቃለሁ ብሎ ይኮፈሳል ። ለሊቅና ለድሀ ጆሮ ይነፍጋል ፣ ለባለጠጋ በከንቱ ይስቃል ። ጥላ ይዞ በዝናብ ይመታል ፣ ዳስ ሳለው በውርጭ ይገረፋል ። በቀትር ይበርደዋል ፣ በውድቅት ሌሊት ይሞቀዋል ። ሲነጋም ሲመሽም ሁልጊዜ ያማርራል ። የሌለውን አለኝ ሲል ያለውን የለኝም ይላል ። ሲያገኝ ዝም ይላል ፣ ሲያጣ ያውጃል ። ለምሬት ተጣርቶ ለምስጋና ድረሱልኝ አይልም ። የደቦ አማራሪ ይፈልጋል ፣ የደቦ ምስጋናን ይረሳል ። ልቤ ልብ ፣ አእምሮዬ እውቀት ፣ ሕሊናዬ ይሉኝታ አጥቶ ይዋረዳል ፤ እንኳን መንፈሳዊ ፣ ሰው መሆን አቅቶታል ። ለካ ሰው ለመሆንም መንፈሳዊ መሆን ግድ ይላል ። ሲራብ ያለቅሳል ፣ ሲጠግብ ይዘላል ። ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ እባክህ ለራሴ አትተወኝ !

አትተወኝ ለራሴ

ፍቅርን ይጠራጠራል ፣ ጠብን ለዘመናት ያመነዥጋል ፣ ለማየት ብሎ ማያ ይዋሳል ፣ ባየ ቍጥር ጨለምተኛ ፣ በተማረ ቍጥር አላዋቂ ይሆናል ። ልቤ ልብ አጥቶ ይዋልላል ። ራሴን የራሱ ጉዳይ ብለህ አትተወው ፣ እምቢ ቢልህ በሽሽግ ቀጥተህ ገንዘብህ አድርገው ። መንገድ ዘግተህ ከጥፋት መልሰው ፣ እያለቀሰ የሚወደውን ከልክለው ። ልቡን ሳያውቅ የሰው ልብ አውቃለሁ ይላል ፣ ራሴ ራሱ ጠፍቶት ስለ ሰው ይተነትናል ። መሄድም መቅረትም ሁለቱም ያስጨንቀዋል ። ብዙ ተቀብሎ ጥቂት መስጠት ይከብደዋል ። ያሳደጉትን ለመጠየቅ እንኳ ይተናነቀዋል ። የክፉ ቀን ወዳጆቹን ይጠላል ። ጠላትን ላያለምደው እባብ ይጨብጣል ፣ የሸሸውን ላይዘው ነፋስ ያባርራል ። የወደዱትን ትቶ ከጠሉት ጋር እልህ ይጋባል ። ወላጁን እየረሳ ጠላቱን ያለ ልክ ያስታውሳል እባክህ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ለራሴ አትተወኝ !

አትተወኝ ለራሴ

ቍጣ አራስ ነብር ያደርገዋል ፣ በአጥፊው አመሉ ከመቆጣት የሚመክሩትን ይንገፈገፋል ። ምንም ሳይሠራ መልክን አሳምሮ ፣ ጡንቻን አደድሮ መጓዝ እንደ አንበሳ ይወዳል ። ዓለም ልፋተኛዋን አህያ ትታ የማይለፋውን አንበሳ ታወድሳለችና እንዲሁ ተቀባብቶ ጎዳና ለጎዳና ይለፋል ። ራሴ ራሱን ለሽያጭ አቅርቦ ፣ በቅንነቱ ሳይሆን በቀለሙ ፣ በእውቀቱ ሳይሆን በመልኩ ለመወደድ ይጥራል ። ለአገልግሎት እንደ ዔሊ ለኃጢአት እንደ ሚዳቋ ይጓዛል ። እንደ ቅንቅን ሰው አያስተኛም ፣ ሁልጊዜ ርእስ መሆን ይፈልጋል ። እንደ ፒኮክ እዩኝ እዩኝ ያበዛል ። አፈር መሆኑን ረስቶት አፈር ነካኝ እያለ ዐሥሬ ልብሱን ያራግፋል ። ኑ ብሎ ጠርቶ ዕዳ ውስጥ ይገባል ። ብሉ ብሎ ጋብዞ መልሶ ይታዘባል ። እባክህ ጌታዬ ኢየሱስ ሆይ ለራሴ አትተወኝ !

አትተወኝ ለራሴ

ሰጪ አንድ አምላክ መሆኑን ረስቶ በዕድል ያምናል ። ከላይ ተልኮ ሰው ያስቀረበት እየመሰለው ከሁሉ ይጣላል ። ሲሰጠው እንዳመሰገነ ሲቀበሉት ማመስገን ይሳነዋል ። ሁልጊዜ ፋሲካ መስሎት ይደላደላል ። ሥራን የምትባርክ አምላክ ሳለህ ምኞቴን ባርክ ይልሃል ። ራሱን አጽድቆ በእነ እገሌ ምክንያት ኋላ ቀረሁ ይላል ። መገፋቱን እልፍ ለማለት ቢጠቀምበት መንገዱ ይቀልለት ነበር ። በነጻ መማር እያቃተው በብዙ ዋጋ ይማራል ። ሌሎች የለፉበትን ቁጭ ብሎ ይመኛል ። ምናለ ቢያካፍሉኝ እያለ ተኝቶ ይቃዣል ። የራሱን መታመም ሳያውቅ ዓለም ሁሉ አብዶ እኔ ብቻ ቀረሁ ይላል ። ሸሽጎ መስጠት አያውቅም ፣ የሰጠውን እስኪያወራ ምጥ ይይዘዋል ። ልጁ የሚያባልግ መሆኑን ክዶ ልጄን አባለጉብኝ ይላል ። የዘመዱን ጉድ እየደበቀ የሌላውን ይለፍፋል ። ተከድኖለት እርሱ ግን የሌላውን ይገልጣል ። ልቤ ፍርድ አያውቅም ፣ ማንነቴ ያንተ ወኪል አይደለም ። አፍቃሪዎቹን እንደ ምስኪን ሲቆጥር የኮሩበትን ማንበርከክ ይፈልጋል ። ዘመድ እንደማይጠቅም በሰው እያየ ምነው ዘመድ በኖረኝ  ይላል ። ለሚሠራ እየጨከነ ላወዳሽ ይሸልማል ። እባክህ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ለራሴ አትተወኝ !

አትተወኝ ለራሴ

ለሥራ ከቤት ወጥቶ ሲያፌዝ ይውላል ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው ከማለት ማንም አጠገቤ የለም ይላል ። ከተማው ጭር ይልበታል ፣ ሰማይ ከቦት ብቻዬን ነኝ ይላል ። እግዚአብሔር አንሶበት በረሃ ቀረሁ ይላል ። ገና ሳይኖር ሞትን ፣ በሃይማኖት ሳይጋደል መጠቃለልን ይፈልጋል ። ለምስጋና ዘሎ ከመጽናት ለጥጋብ እየዘለለ ይሰበራል ። እንደ ዳዊት ከመዘመር እንደ ሜልኮል እያሽሟጠጠ መካን ሁኖ ይኖራል ። እባክህ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ለራሴ አትተወኝ !

አሜን !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 2 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ