መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ቅድስት ማርያም » ቅድስት ማርያም -5

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ማርያም -5

የማርያም ስሞች

2. ቅድስት

እግዚአብሔር የፈጠረን ለራሱ እንድንሆን ነው ። ለራሱ ስለ ፈጠረን ለማንም መሆን አንችልም ። ሰው ከእግዚአብሔር ከራቀ ተቅበዝባዥ ፣ እርካታና ዕረፍት የለሽ ይሆናል ። ለራሱም የማይሆን ለሰውም የማይበጅ የሚሆነው ሰው ከፈጠረው አምላክ ሲርቅ ነው ። የሕይወት መንከራተትን ያየው ፣ በብዙ ጸሎት ለእግዚአብሔር ደጅ የበቃው ቅዱስ አውግስጢኖስ ኪሣራና ትርፉን ከመዘነ በኋላ እንዲህ ብሎ አመሰገነ፡- “ጌታ ሆይ ለራስህ ስትል ስለ ፈጠርከን ልባችን ባንተ እስኪያርፍ ድረስ የትም ይባክናል ።” እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረበት መነሻው ፍቅር ነው ። ፍቅር በጠባዩ ምን እሰጣለሁ እንጂ ምን አገኛለሁ ባይ አይደለም ። እግዚአብሔር ለሰው መልኩን ፣ ክብሩን ፣ ጸጋውን ፣ ገዥነትን ፣ ልጅነትን ፣ ረዳትን ፣ ትእዛዝን ሰጥቶታል ። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ረድኤት በመላእክት ጥበቃ የሚኖር ፣ የተከበረና እንደ ልዑል የሚመላለስ ፣ ጸጋ የተትረፈረፈለት ሲሆን በአምልኮ መጽናት ፣ ትእዛዝን መጠበቅ ፣ በፍቅር ከጎረቤቱ ጋር መኖር ያስፈልገዋል ። ይህን መጠበቅ ባለ መቻሉ ከአዲስ ሰውነት አሮጌነት መገለጫው ሆነ ። ስለ ትላንት ትዝታ ያለው እንጂ ስለ ነገ ተስፋው የዘገየበት ሆነ ። በገነት በነበርን ጊዜ ፣ በቅድስና በተመላለስንበት ወራት እያለ ለልጆቹ የሚተርክ ሆነ ።

ከውድቀት በኋላም የቅድስና ሕይወት ምርጫ ነው ። ሰዎች ከገዛ ፍላጎታቸውና ከቤተሰባቸው ተለይተው ለእግዚአብሔር ሕይወታቸውን ይሰጣሉ ። የሚሰጡት ሕይወታቸውን ነውና የሚቀራቸው ምንም ነገር የለም ። በዚህም መለየትና መጠላትን ያስተናግዳሉ ። ቅድስና በምድር ላይ የሚያሸልም ሳይሆን መቀደስ ባልቻሉ ሰዎች የመጠላት ርእስ ነው ። አቤል ከአዳምና ከሔዋን እንዲሁም ከቃየን ተለይቶ ተቀደሰ ። ቅድስና ከቤተሰብ እንማረዋለን እንጂ አንወርሰውም ። ሕይወት ምርጫ መሆንዋን የሚነግረን ቅድስና ነው ። የአዳም ልጅ አቤል ቅዱስ ፣ የቅዱሱ የዳዊት ልጆች ርኵስ የሆኑት ሕይወት ምርጫ ስለሆነ ነው ።

ድንግል ማርያም ቅድስት የምትባለው ስለ ተመረጠች ብቻ ሳይሆን ቅድስናንም ስለ መረጠች ነው ። ሕይወትዋን ለእግዚአብሔር ለይታለች ። እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ወላጆች የተገኘች ስትሆን የእነርሱንም ሃይማኖት ተቀብላለች ። እነርሱም ለእግዚአብሔር የሰጡአት ስትሆን እርስዋም ራስዋን ለእግዚአብሔር ሰጥታ የምትኖር ናት ። ቅድስት ማለት የተለየች ማለት ነው ። በብሉይ ኪዳን መቅደስ “ቅድስት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ከቅድስተ ቅዱሳኑ በፊት የምናገኘው ክፍል ነው ። በዚህ ክፍል ውስጥ ዕለታዊና ሳምንታዊ አገልግሎት ነበረ ። በዚህ ክፍል ውስጥ መቅረዝ ፣ የገበታ ኅብስትና የዕጣን መሠዊያ ነበረ ። ማርያም እናታችን ቅድስት ናት ስንል እነዚህ ነገሮች በውስጥዋ አሉ ። እርስዋ የብርሃን ኢየሱስ መቅረዝ ናት ። እርስዋ የኅብስተ ሕይወት ኢየሱስ ገበታ ናት ። እርስዋ የንጹሕ ዕጣን የኢየሱስ ሙዳይ ናት ። መቅረዙ ዘይት ፣ ክርና መብራት ነበረበት ። እርስዋም መንፈስ ቅዱስ የሚኖርባት ፣ እንደ ክሩ የሚነደው የሚሠዋው የኢየሱስ እናትና የመስቀል ተባባሪ ፣ አዛኝቱ ማርያም ናት ። መስቀሉን ከሐዋርያት በፊት ተሸክማለች ። ከፅንሰትዋ ጀምሮ ብዙ መከራ ተቀብላለች ። ቤዛ የሚሆን ልጅዋን እያሰበች በሰቆቃ አሳልፋለች ። የኀዘን እናት ሁና ኖራለች ። በዚህም የስምዖን አረጋዊ ትንቢት ተፈጽሟል ። “በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት” የሚለው ትንቢት ሲፈጸም አይተናል ። (ሉቃ. 2 ፡ 35) ።

በጨለማው ዓለም ያበራው የክርስቶስ እናት ናት ። የዓለምን ረሀብ ያራቀው ፣ የድሆች የጠኔአቸው መድኃኒት የሆነው ፣ የነፍስ ወደብ ተብሎ የሚጠራው ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ ከድንግል ተገኘ ። በዚህም በአማን ቅድስት ናት ። ኢየሱስ ዕጣን ነው ። ዕጣን በተጤሰ ቍጥር በቤት ውስጥ ያሉ አየሩ ላይ የተንሰራፉ በሽታዎች ይሞታሉ ። ዕጣን ኢየሱስ የኃጢአትን በሽታ የገደለ ነው ። ዕጣን አድራሻው ወደ ላይ ነው ፣ ኢየሱስም የሰማይን መንገድ በደሙ የመረቀ ነው ። ዕጣን ጣፋጭ ነው ፣ ኢየሱስም መዓዛ ነፍስ ነው ። ዕጣን እሳት ይፈልጋል ፣ ክርስቶስም እሳት መከራን ተቀብሎ ዓለሙን አውዶታል ። ዕጣን የቤትን መዓዛ ይለውጣል ፣ ክርስቶስም ቤተሰብን ይባርካል ። ዕጣን ደስታን ይሰጣል ፣ ክርስቶስም ለነፍስ መብረሪያ ክንፍ ይሆናል ። ዕጣን ያረጋጋል ፣ ክርስቶስም ልብን ያሳርፋል ። ዕጣን ተመሥጦ ያመጣል ፣ ክርስቶስም ሰማያዊ ሠረገላ ይሆናል ። ዕጣን ለሁሉ ይሸታል ፣ ክርስቶስም ለዓለም ሁሉ ተሠውቷል ። ዕጣን ካልጤሰ አይሸትም ፣ ክርስቶስም ባይሞት ኑሮ መዳን አይመጣም ነበር ። ዕጣኑ የተገኘባት ሙዳይ እመቤታችን ማርያም ናት ። በዚህም በአማን ቅድስት ናት ።

ለእግዚአብሔር የተለየ ሰው በብሉይ ኪዳን ናዝራዊ ይባላል ። ናዝራዊ የሆነ ሰው ወይን ጠጅ አይጠጣም ፣ ራሱን አይላጭም ፣ በድን አይነካም ። እመቤታችን ቅድስት ናትና ራስዋን ለእግዚአብሔር የለየች ናትና ናዝራዊነት ይታይባታል ። ከእግዚአብሔር ውጭ ደስታ የላትምና የወይን ጠጅ አትጠጣም ። ክብርዋ አይገፈፍምና ራስዋን ያልተላጨች ናት ። በድን ኃጢአትን ያልነካች ቅድስት ናት ።

አንድ ዕቃ ለእግዚአብሔር ሲለይ በእግዚአብሔር ቤት ይኖራል ። ያ ንዋየ ቅዱስ የተቀደሰ ቅባት ይታተምበታል ። ለእግዚአብሔር የተቆጠረ ነውና አይጠፋም ፣ ለሌላ አገልግሎት መዋል አይችልም ። እመቤታችንም ቅድስት ናትና መኖሪያዋ የእግዚአብሔር ቤት ነው ። የሚገርመው ራስዋ መቅደሰ ወልድ ሆነች ። ለእግዚአብሔር የተሰጠ ዘመንዋም ለዓለም ውሎ አያውቅም ። ሥጋዊና መናኛ ድርሻም በእርስዋ ዘንድ የለም ። ሕይወትዋ የመማሪያ መጽሐፍ ነውና በቅድስና መኖርን ፣ ለእግዚአብሔር የመለየት ዋጋን ከእርስዋ እንማራለን ።

የቅድስት ማርያም በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን !

ይቀጥላል
ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ