መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ቅድስት ማርያም » ቅድስት ማርያም -6

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ማርያም -6

3. ቅድስተ ቅዱሳን

በብሉይ ኪዳን ታላቅ ክብርና መፈራት የነበራት ቅድስተ ቅዱሳን ናት ። የምትወክለው መንበረ ሥላሴን ነው ። ቅዱስተ ቅዱሳን በዓመት አንድ ገዚ ሊቀ ካህኑ ስርየትን ለሕዝብ ለማምጣት የመሥዋዕቱን ደም ይዞባት ይገባል ። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ በብርቱ መጋረጃ የተዘጋ ነበር ። ይህ መጋረጃ ዛሬ በተግባር ላይ እንዳሉ መጋረጃዎች ለመለየትና ለጌጥ የሚያገለግል ሳይሆን ከቅድስቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ የሚወስደው መንገድ ዝግ መሆኑን የሚገልጥ ነው ። ሊቀ ካህኑም የሚገባው በአንደኛው ጫፍ ላይ ገለጥ አድርጎ እንጂ በመካከል ክፍተት አልነበረውም ። መጋረጃው 820 ሺህ የወርቅ ዲናር ይገመት ነበር ። መጋረጃውንም 300 ካህናት የሚሸከሙት ነበር ። ርዝመቱ 40 ክንድ ፣ ስፋቱ 20 ክንድ ውፍረቱ አንድ የእጅ መዳፍ ያህል እንደ ነበረ የረቢዎች ማስታወሻ በሚሽና ተመዝግቧል ። ጌታችን በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ ከላይ እስከ ታች የተቀደደው ይህ መጋረጃ ሲሆን መንገደ ሰማይ ከዚህ በኋላ መከፈቱን የሚገልጥ ነበር (ማቴ. 27፡51 ፤ ዕብ. 10፡19-20)። ቅድስተ ቅዱሳን የእግዚአብሔር መኖሪያን በምሳሌነት የሚገልጥ ሲሆን ወደዚህ ስፍራ የሚገባው ሊቀ ካህኑ ብቻ ነው ። እርሱም በዓመት አንድ ጊዜ በሚደረገው በስርየት ቀን (በዮም ኪፑር) ነው (ዘሌዋ. 16፡2 ፣29-34)። ሊቀ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባው በታላቅ ፍርሃት ሲሆን በእግሩ ላይ ገመድ ይታሰር ነበር ። ምናልባት ተቀስፎ ቢሞት በድኑን ለማውጣት ሌላ ሊቀ ካህን እስኪነሣ መጠበቅ ያስፈልጋል ። ይህ ስፍራ እጅግ የሚያስፈራ ስፍራ ነበረ ።

በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የእግዚአብሔር ታቦት ነበረ ። በታቦቱ ላይ በደመና እግዚአብሔር ይገለጥ ነበር ። በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ አንድ ንዋየ ቅዱስ ብቻ ሲኖር እርሱም ታቦት ነው ። በታቦቱ ውስጥም ጽላት አለ ። ይህም ዐሥርቱ ትእዛዛት በእግዚአብሔር ጣት የተጻፉበት የድንጋይ ሰሌዳ ነው ። ጽላት የብዛት ስም ሲሆን ጽሌ የሚባለው ነጠላው ገጽ ነው ። ዐሠርቱ ትእዛዛት በሁለት ይከፈላሉ ፣ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ይባላሉ ። ፍቅረ እግዚአብሔር የሰፈረው በአንደኛው ሰሌዳ ፣ ፍቅረ ቢጽ የሰፈረው በሁለተኛው ሰሌዳ ነውና ጽላት ይባላል ። አንድ ገጽ ብቻ ቢሆን ጽሌ ወይም ሰሌዳ ይባል ነበር ። ከአንድ በላይ በመሆኑ ጽላት የሚል ስም አግኝቷል ። በታቦቱ ውስጥ ሦስት ነገሮች ነበሩ ። ጽላት ፣ የለመለመች የአሮን በትርና የመናው መሶበ ወርቅ ።

ቅድስተ ቅዱሳን ማለት የተለዩ የተለየች ማለት ነው ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስተ ቅዱሳን ትባላለች ። ከተለዩ የተለየች ናትና ። መላእክት በማመን እንጂ በማየት የማያገለግሉትን ጌታ አይታዋለች ፤ ኪሩቤል የተሸከሙትን በክንድዋ አቅፋዋለች ። መጋቤ ዓለማትን በድንግልናዊ ሀሊብ /ወተት አሳድጋዋለች ። ባሕርያዊ በሆነ ልደት ልጄ ብላ ጠርታዋለች ። ይህም ሰዎች በእምነት ልጄ እንደሚሉት ሳይሆን በርግጥም ፈጣሪ ልጅዋ ሁኖ ፣ የፈጠራትን ወልዳ ከቅዱሳን ሁሉ የተለየች ሁናለች ። ሰዎች በየጊዜው ጸጋቸው እያደገ ይመጣል ። የድንግል ማርያም ጸጋ ግን ራሱ ባለ ጸጋው በመሆኑ ፣ መጉደልና መጨመር ያለበት አይደለም ። የእርስዋ ክብሯ ራሱ እግዚአብሔር ነው ። መድኃኒትዋና አምላክዋ ነው ። ነገረ ማርያም በተነገረ ቍጥር እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ክብር እናስባለን ። ምክንያቱም ትምክሕተ ዘመድነ የተባለላት የወገን መመኪያ ናት ። አገራቸውን ያስጠሩ ጀግኖች ክብራቸው የራሳቸው ሳይሆን የወገናቸው ነው ። እኛም እንኮራባቸዋለን ። ድንግል ማርያምም አምላክ ሰው ለመሆን የመረጣት ድልድይ ናትና መመኪያችን ትባላለች ። እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው ፣ ሰው በሆነ ጊዜ ግን ሰውን አምላክ አደረገው ።

የቅድስተ ቅዱሳን መንገድ በጥብቅ መጋረጃ የተዘጋ ነበር ፣ ቅድስት ማርያም በኅቱም ድንግልና ወልዳለች ። ከወለደችም በኋላ ለዘላለም ድንግል ሁና ኖራለች ። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሊቀ ካህኑ ብቻ እንዲገባ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በድንግል ማኅፀን አድሯል ። በቅዱስተ ቅዱሳን ውስጥ ቃሉ የሰፈረበት ጽላት ነበረ ፣ በድንግል ማኅፀንም የአብ ቃሉ አደረ ። እንዲሁም የለመለመች የአሮን በትር ነበረች ። የደረቀች በትር መለምለሟ የሞተው ክርስቶስ መነሣቱን የሚገልጥ ነው ። ሥልጣኑም ሁልጊዜ ትኩስና ለምለም ነው ። በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የበረሃው መና ነበረ ፣ በድንግል ማኅፀንም የዓለም ጥጋብ ክርስቶስ አደረ ። ከእርስዋ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ በመንሣት ፍጹም ሰው ሆነ ። የወደቀው ማንነታችንንም አነሣው ። ያዳነን ተዋሕዶን ነው ። ዛሬም ሌሎችን ለማዳን እነርሱን መዋሐድ ፣ መስማትና መቅረብ ፣ እንደ ዘመድ መቍጠር ይገባል ። የጌታችን ተዋሕዶ ለሥነ መንግሥትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ። መግደል ሲችል ያዳነን ፣ ራሱ መጥቶ የታረቀን ፣ ዓለምን የምንገዛበት ሕለተ ወርቅ ፍቅር መሆኑን ሊነግረን ነው ።

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል፡- “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” አላት ። (ሉቃ. 1 ፡ 28) ። ድንግል ማርያም የጌጥ አምልኮ ካለባቸው ከመላው ዓለም ሴቶች ጋር የተወዳደረች ከመሰለን ስህተት ነው ። ከተቀደሱት ፣ ሰማይ ካከበራቸው ቅዱሳን ሴቶች ከነ ሣራ ፣ ከነ ርብቃ ፣ ከነ ራሔል ፣ ከነ ሃና ፣ ከነ ኤልሳቤጥ ተወዳድራ የተለየች ናት ። ከተቀደሱት የተቀደሰች ናት ። ሴቶች ጳጳስ ንጉሥ ቢወልዱ ይከበራሉ ፤ እርስዋ ግን አምላክን ወልዳለችና እናከብራታለን ። ብዙ መታደሎችና መባረኮች አሉ ። አምላክን ከመውለድ የበለጠ መታደል ግን እስካሁን አልተሰማም ። ወደፊትም አይሰማም ።

እግዚአብሔር ሰውን እንዴት እንደ ወደደው ፣ ስደተኛውን አዳም እንዴት እንዳከበረው ነገረ ተዋሕዶ ያስረዳናል ። ለዚህ ጌታ እንኳን መኖር ብንሞትለትም የሚያንሰው ነው !

ይቀጥላል
ነሐሴ 12 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ