እንኳን ለ2018 የደብረ ታቦር በዓል በሰላም አደረሳችሁ !
“ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።” ማቴ. 17፡1
ሦስቱ የምሥጢር ደቀ መዛሙርት ናቸው ። ጌታችን ኢያኢሮስን ልጅ ከሞት ሲያስነሣ ፣ በደብረ ታቦር ክብሩን ሲገልጥ ፣ በጌቴሴማኒ የጭንቅ ሰዓት አብረውት ነበሩ ። በተአምራትና በክብር መገለጥ ሰዓት ብቻ ሳይሆን በጌቴሴማኒ የጭንቅ ሰዓትም አልተለዩም ። የወዳጅ ማስመስከሪያው የጭንቅ ሰዓት ነው ። ደስታን ሁሉም ይካፈለዋል ፣ መከራን የሚካፈል ግን ጥቂት ነው ። ጌታ በዚያች ሰዓት ሦስት ሰዎች ብቻ አጠገቡ ከተገኙ እኛ በመከራችን ሰዓት አንድ ሰው ካገኘንም በቂ ነው ። መከራና ጭንቅ ወዳጅን በመቀነስ የታወቁ ናቸው ። ተደልለን ልንኖር እንችላለን ፣ ከማን ጋር እንደ ነበርን ለማወቅም እንቸገራለን ። የመከራ ሰዓት ግን እንደ ወርቅ አንጥሮ ፣ እንደ እህል አበጥሮ ፣ እንደ ወንፊት አንዘርዝሮ ወዳጅን ይለይልናል ። ሰዎች በጭንቃችን ሰዓት የሄዱት ልካቸው ይህ ስለ ነበር ነው ። ሳናውቃቸው ተደስተን ከመኖር አውቀናቸው ማዘን ይሻላል ። በአካላችን ላይ የበቀለ እባጭ ሲወጣ ሕመም አለው ፣ ቢቆይ ግን ሞትን ያመጣል ። ከሞት እንድን ዘንድ ለሕመም የምንተውበት ጊዜ አለ ። እግዚአብሔር ትልቁን መከራ በሚያንስ መከራ ያሳልፋል ።
ያ እባጭ ቢወጣም የተሰራጨ ነገር ሊኖረው ይችላል ። አንዳንድ ሰዎች ሲሄዱ ተክተው የሚሄዱት ሰው አለ ። ቀጥሎ በአዲስ ገራፊ መላጥ እንጀምራለን ። ችግርን ከነ ሰንኮፉ መገላገል ብዙ ጊዜ አይገጥምም ። በጊዜ የተለዩን የወዳጅ ያህል ናቸው ፣ ከዚህ በላይ ለማስመሰል ስላልቻሉ ሄደዋልና ልናመሰግናቸው ይገባል ። ቢሆንም እግዚአብሔር ለቀኑ አንድ ሰው ያዝልናል ። ያ ሰውም አገልግሎቱን ሲፈጽም ሊሄድ ይችላል ። አምላክ ብዙ ሰው አለውና ሌላ ረዳት ደግሞ ያዛል ። ዘላለም ከእኛ ጋር የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው ። እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ያለው እርሱ ብቻ ነው ። ፍጡር እንዲህ ሊል አይችልም ። ፍጡር ሊለን የሚችለው እስከ ውበት ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ፤ እስከ ገንዘብ ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብቻ ነው ። ሰዎች ለእኛ የተሰጡን የጨለማ መብራት ሊሆኑ ይችላሉ ፣ ለሰዎች ብርሃን ለመሆን ግን ራሳችንን መስጠትና ዛሬ መወሰን አለብን ።
ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው ። ጴጥሮስ የእምነት ምሳሌ ነው ። እምነቱንም በአደባባይ ገልጧል ። በደብረ ታቦር የተገለጠው ክብርም የጴጥሮስን እምነት ለማጽናትም ነው ። ጴጥሮስ ብዙ ጊዜ ድካምና ውድቀት ቢገኝበትም እግዚአብሔር እንደሚምረው ጽኑ እምነት ነበረው ። እምነት ማለት በእግዚአብሔር ፍጹም መሐሪነት በእኛ ፍጹም ኃጢአተኝነት ማመን ነው ። እንደ አምላኬ ብርቱ ፣ እንደ እኔ ደካማ የለም ብሎ መቀበል እርሱ እምነት ይባላል ። ብዙ ሰው እኔንማ ይቅር አይለኝም ብሎ ርቋል ። ሰይጣናዊ ትዕቢት ብቻ ሳይሆን ሰይጣናዊ ትሕትና እንዳለ እንዘነጋለን ። እውነተኛ ትሕትና ቢገለኝም ከአምላኬ አልለይም የሚል ነው ። ቅዱስ ያዕቆብ ሁለተኛው የምሥጢር ደቀ መዝሙር ነው ። ከሐዋርያት በመጀመሪያ በሰማዕትነት የሞተው እርሱ ነው ። በመሥዋዕትነቱ ምሳሌ የሚሆን ነው ። የመሥዋዕትነት ልብ ሰውን በነፍሱ እንዲጠግብ ያደርገዋል ። ላመነበት ነገር የሚኖርና የሚሞት ራሱ በራሱ ፊት ክብር አለው ። የራሱ መንፈስ ማን መሆኑን ይመሰክርለታልና ራሱን ከውጭ አይፈልግም ። የመሥዋዕትነት ልብ የሌለው ተገለባባጭ ፣ ዘመን መሳይ ፣ ለከፈለው የሚዘፍን ፣ ሆዱን የሚያመልክ ፣ ተቸግሮ ሳይሆን ለአመሉ የሚልከሰከስ ነው ። ሞት አይቀርምና ቆራጥ መሆን አስፈላጊ ነው ። በዚህ ሞት ሰይፍ ይዞ በወጣበት ዘመን ፣ የመሞቻው ምክንያት በበረከተበት ጊዜ ለእውነት ኖሮ መሥዋዕት መሆን ሞትን ማሸነፍ ነው ። ሞትን የምንበቀለው በመሥዋዕትነት ነው ። መሥዋዕትነት ከመቃብር በላይ የሚኖር ስም ነው ። ሰይጣን ተከታዮቹን ለገዳይነት ያሰለጥናል ፣ ገዳዮች ፍርሃታቸው ልክ የለውም ። እግዚአብሔር ግን አስፈላጊ ከሆነ ስለ ሌሎች እንድንሞት ያዘናል ። ይህንንም ራሱ ሰው ሁኖ ፣ የሚሞትበትን ሥጋ ለብሶ አሳይቶናል ።
ቅዱስ ዮሐንስ ሦስተኛው የምሥጢር ደቀ መዝሙር ነው ። ወንድሙ ያዕቆብ በጊዜ ሞተ ፣ ባልንጀራው ጴጥሮስ በ67 ዓ.ም. ተሠዋ ። ዮሐንስ ግን እስከ 92 ዓ.ም ገደማ የነበረ የመጨረሻው በሕይወት የቆየ ሐዋርያ ነው ። ዮሐንስ በሽምግልናው ዕድሜ በሸክም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲያመጡት ፣ አንደበቱ ተያይዞ ሳለ ለኤፌሶን ምእመናን “ልጆቼ እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ” እያለ ይህን ቃል ደጋግሞ ይናገር እንደ ነበር ታሪክ መዝግቦልናል ። መልእክታቱም ስለ ፍቅር የሚናገሩ ናቸው ። በወንጌሉ ላይ ስለ ራሱ ሲገልጥ “ጌታ ይወደው የነበረ” እያለ ነበር ። መልእክታቱም እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን የሚናገሩ ፣ ወንድሙን የማይወድ ነፍሰ ገዳይ ነው እያሉ የሚመሰክሩ ናቸው ። ዮሐንስ የፍቅር ሐዋርያ ይባላል ። ጌታ ብርሃነ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን የገለጠው እምነት ፣ መሥዋዕትነትና ፍቅር ለነበራቸው ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ነው ።
ምሥጢር ጠባቂ በሰማይም ይፈለጋል ። ሁሉን አደባባይ የማይዘራ ፣ ቤተ ክርስቲያንን የማያራቁት ፣ በወንድሙ መለወጥ ተስፋ የሚያደርግ ፣ እኔ ቆንጆ ነኝ ለማለት እገሌ አስቀያሚ ነው ብሎ የማይጀምር ፣ ልበ ሰፊ የሆነ የምሥጢር ሰውን እግዚአብሔር ይፈልጋል ። እምነት ያለውን ሰማይ እየፈለገው ነው ። የእምነት ቃል የሚናገሩ ግን ሃይማኖት የሌላቸውን ሰዎች እያየን ነው ። መሥዋዕትነትን የሚወዱ ለሌላው መኖር የሚያስደስታቸው ፣ በፍቅር ነፍሳቸው የተቃኘች በመብራት እየተፈለጉ ነው ። ደብረ ታቦርን ስናስብ በእነዚህ ቱንቢዎች ራሳችንን መለካት አለብን።
ብዙ እንዳንተነትን ጊዜ ያጥረናል።
የደብረ ታቦር ክብር በልባችን ያብራ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 13 ቀን 2018 ዓ.ም.