አንዳንዴ ገና ከእንቅልፋችን ስንነሣ እንባ እንባ ይለናል ። ማልደን ስንወጣ ከተማይቱን ስናይ አልቅሱ አልቅሱ የሚል ስሜት ይጋፋናል ። የሚገርመው ግን ይህ ልውጣ ልውጣ የሚለው የእንባ ትግል ስለ ራሳችንና ስላልተሳኩ ጉዳዮቻችን ነው ። ስለ ራሳችን ኃጢአት ስለ ወገኖቻችንም ስህተት እንባ እንባ አይለንም ። ለራሳችን ስህተት ብዙ ሰበብና አመክንዮ እናቀርባለን ። “መሆን ስለ ነበረበት ሆነ ፣ የተሰማኝ ስሜት ነው ምንም ማድረግ አልችልም” ብለን ለራሳችን ይቅርታ እናደርግለታለን ። ያንን ስህተት ስንፈጽም ሰዎች ነበርን ፣ አሁን ለራሳችን ይቅርታ ስናደርግ ግን አምላክ ነኝ እያልን ነው ። ስለ ወገኖቻችንም ኃጢአት ማልቀስ ተገቢ ነበር ። እኛ ግን በምናውቀውም በማናውቀውም መንገድ እንፈርዳለን ። ሥልጣን የተሰጠው ፍርድ ቤት እንኳ ጥፋተኛ ነው ለማለት ዓመታት ይወስዱበታል ፣ ሥልጣን የሌለን እኛ ግን ሰምተን ሳንጨርስ እንፈርዳለን ።
ዛሬ ላይ የምናጭደው መከራ በአብዛኛው የዘራነውን ፍርድ ነው ። እገሌ ይህ በሽታ መጣበት ፣ ጨዋ ይመስል ነበር ብለናል ፣ ዛሬ የሚበዛው በሽተኛ ሆኗል ። እገሌ ሃይማኖቱን ለውጧል ፣ ኑሮም ቀብርም አይገባውም ብለን ነበር ፣ ዛሬ የገዛ ቤተሰባችን ላይ ሲደርስ አቅፈን ተቀምጠናል ። እገሌ ይህ ነውር አለበት በእሳት መቃጠል ይገባዋል ብለናል ፣ ያ ነውር ልጆቻችን ላይ ሲመጣ አፍረን ተቀምጠናል ፣ አፍ እያለን ዱዳ ሆነናል ፤ የጽድቅ ጠበቃ ነኝ ስንል ነበር አሁን የራሳችን ሰው ጋ ሲደርስ ጭምት ሆነናል ። እነ እገሌ መወገድ አለባቸው ብለን ለጦርነት ሆ ብለናል ፣ ሞት ዛሬ በየቤታችን ሲያንኳኳ ደንግጠናል ። ሩቅ ሲያጠፋ ጎበዝ ያልነው የቅርብ በር እየመታ ነው ። ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ሱስ በሚወስዱ ወጣቶች ላይ ብዙ ጥቆማ አድርገናል ፣ የገዛ ልጆቻችን አልጋቸው ላይ ሆነው አደንዛዥ ዕፅ ሲስቡ ግን ጸሎት ይዘናል ። ትላንት የዘራነውን መራራ ዘር እያጨድን ነው ፣ የእኛ የፍርድ ኃጢአት ለልጆቻችንና ለቅርቦቻችንም ተርፎአል ። ቃሪያ የዘራ ብርቱካን አይለቅምም ። የዘራነውን የሚመስል እናጭዳለን ፣ ከዘራነው በላይ እናጭዳለን ።
ጌታችን ከተማይቱን ባያት ጊዜ ያለቀሰው ስለ ኃጢአተኞች ነው ። በመስቀል ላይም ስለ ሰቀሉት ወገኖች ማለደ ። በዚህ በሆሳዕና ዕለት ይቃወሙታል ፣ ኃጢአት ያድጋልና በዕለተ ዓርብ ደግሞ ይሰቅሉታል ። እግዚአብሔር ራሱ በሥጋ እንግድነት መጥቶ ሲጎበኛቸው ላላወቁ ሕዝቦች አለቀሰ ። ኢየሩሳሌም የቀራት አንድ ዓይንዋ እግዚአብሔር ነበረ ። ዓለም ሁሉ ተባብሮ ጠልቷት ነበር ። አንድ ዓይንዋን ለምታጠፋው ከተማ አለቀሰ ። የከተማው ኑሮ ማስመሰል ያለበት ነው ። ከተማው ብዙ ቤቶች አሉበት ፣ በትክክል የሚኖር ግን ጥቂት ነው ። ብዙ ሰው አለበት ፣ ብቸኝነት ግን እንደ ጥቅምት ውርጭ የሚገርፍበት ነው ። ረሀብ አለ ፣ በነጭ ልብስ የተሸፈነ ነው ። ዛሬም ከዚህች ከተማ ቢመጣ ጌታ ያለቅሳል ። ድሆችዋ መድረሻ የላቸውም ። ቤት አጦች እልፍ ናቸው ። ልጆቻቸው ያመፁባቸው ወላጆች ልክ የላቸውም ። ሥራ አጦች ማለዳ በባዶ አንጀታቸው ወጥተው ሲዞሩ ይውላሉ ። ውኃ ስጡኝ እንዳይባል በሮች ሁሉ ዝግ ናቸው ። በጫካ ከመጥፋት በላይ በአርማታ ጫካዎች በፎቁ መሐል የጠፋ ፣ የሕይወት ውሉ የተሰወረበት ብዙ ሰው አለ ። አግኝተው ደስታ ላጡ ፣ ኖረው መኖሪያ ለተቸገሩ ከተሜዎች ጌታ ዛሬም ያለቅሳል ። መኖርም መሞትም በማይቻልባት ከተማ ፣ ያልሰማ በሚጎርፍባት ደማቅ ቀዬ ብዙ ድብቅ እንባ አለ ። ነጠላ የለበሰ ወንበዴና ፀጉሩን ያጎፈረ ጻድቅ በከተማ አለ ። ነጭ ለብሶ የሚራብና ድሪቶ ለብሶ የሚጠግብ በከተማ አለ ። ጌታ ዛሬ ቢመጣ ለብዙ ደማቅ የዓለማችን ከተሞች ያለቅሳል ። የውሸት እየሳቁ የእውነት የሚያለቅሱ በከተማው ሞልተዋልና ። ባለጠጋ ዘመድ እያላቸው በረሀብ የሚገረፉ ፣ በራስ ወዳድነት መተያየት ያቃታቸው የከተማው ምንዱባን አያሌ ናቸው ።
ጌታችን ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው ፍርድ ከመጣ የቍጣውን ጽዋ እስከ መጨረሻው መጨለጥ ግድ ስለሆነ ነው ። ከቀኑ በፊት አለቀሰ ። በቀኑ ለማልቀስም ኢየሩሳሌም ጊዜ አላገኘችም ። እዬዬ ለማለትም ድሎት ያስፈልጋል ። ድል አድራጊ ነህ ሲሉት ዘንባባ እያነጠፉለት ነበር ። ጌታችን ግን በሆሳዕና በአርያም ዝማሬ መካከል አለቀሰ ። በምድር ላይ ሰፊ ሀብት የፈሰሰበት መቅደሱ ነው ። ያ መቅደስ አስቀድሞ በዳዊት ሊሠራ ሲል ዳዊት ተከለከለ ። ቅዱስ ዳዊት ያልቻለውን የእግዚአብሔር ቤት መሥራት ፣ ወንጌልን ማስፋፋት ዕድሉ መጥቶለት የሚዘገይ ያልታደለ ሰው ነው ። የመቅደሱ ንድፍ በራሱ በእግዚአብሔር የተቀረጸ ነው ። ይህ መቅደስ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚፈርስ ባሰበ ጊዜ ጌታ አለቀሰ ።
የመጀመሪያው መቅደስ የሰሎሞን መቅደስ ይባላል ። ሁለተኛው መቅደስ የዘሩባቤል መቅደስ ይባላል ። ይህ መቅደስ በጌጠኛነቱ ከመጀመሪያው በላይ አይደለም ። የመቅደሱ ምርቃት ቀን የተሰጠ ተስፋ ነበር ። “ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።” (ሐጌ. 2 ፡ 9)። ከፊተኛው መቅደስ ይልቅ የሁለተኛው ቤት በክብር የበለጠው ክርስቶስ ቆሞ ስላስተማረበት ነው ። ይህ መቅደስ እንደሚፈርስ ባሰበ ጊዜ ጌታ አለቀሰ ። ብዙ ሞኝ ሰው አለ ። አገሬ አትፈርስም ይላል ። ቤተ ክርስቲያኔ ምንም አትሆንም እያለ ተኝቶ የሚፎክር ቍጥር የለውም ። ኢትዮጵያ የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ አርባ ጊዜ ያህል ስለ ተጠቀሰ ኢትዮጵያ ምንም አትሆንም ብሎ የሚያስብ ምስኪን አለ ። ከኢትዮጵያ በላይ ሶርያ ተጠቅሳለች ፣ ግን ፈርሳለች ። ኢየሩሳሌምን ኃጢአትና ግፍ ፣ አለማመንና መከፋፈል ካፈረሳት እኛ የተለየን አይደለንም ። ዛሬም ጌታ ቢመጣ ለአገራችን ያለቅስላታል ። ምንም እርግጠኛ ነገር የለንም ። ገደል አፋፍ ላይ ቆመን እየታገልን ነው ። ገደል አፋፍ ላይ እንኳን ጠቡ ፍቅሩም አያስደስትም ። ፈጥነን ራሳችንን ማየት የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ ነን ።
ይቀጥላል
ጳጉሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም.