ከእውቀትም ከዕድሜም ድሀ ለሆነው ፣ ለአገርህ ዝመት እንጂ ከአገርህ ብላ ለማይባለው ፣ መኖር ርቆት ለጥቂቶች አኗኗሪ ለሆነው ፣ እንኳን ለነገ ለዛሬ እርግጠኛ መሆን ላቃተው ፣ ያልተማረ አስተማሪ ሰይፍ ይዞ ለሚነዳው ለዚያ ምስኪን እዘንለት ። የተባረከ ቀንን ለናፈቀው ፣ ፈልጎ ፈልጎ ላጣው ፣ አዲስ ዘመንን መጠበቅ ለደከመው ፣ ዛሬ እንደ ትላንቱ ለሆነበት ፣ የሚለው ጠፍቶት አፍ እያለው ዱዳ ለሆነው ፣ ከአገሩ ሲርቅ የዘመድ ፍቅር ላከሳው ፣ ወደ አገሩ ሲያስብ የተዘጋው በር ለሚመልሰው ለዚያ ጎበዝ እባክህ እዘንለት ። መንኩሶ ጋብቻ ፣ አግብቶ ምንኵስና ለሚያምረው ፣ የያዘው ነገር በእጁ ላይ ቶሎ ለሚያረጅበት ለዚያ ላንተ ሥራ እባክህ እዘንለት ።
ከራሱም ፣ ከሰውም ፣ ከዘመንም ፣ ካንተም ተጣልቶ ላኮረፈው ፣ ሁለት ተስፋ ይዞ ፍርሃት ለሚንጠው ፣ ሁለት ዓለም ከጅሎ ሁሉም ባዶ ለሆነበት ፣ ራሱን ሸቀጥ አድርጎ ገበያ ላወጣው ፣ በሚፈርስ አካሉ ለሚመካው ለዚያ ወጣት እባክህ እዘንለት ። ውርስን ሲጠብቅ ሞት ለገጠመው ፣ ሽማግሌን እቀብራለሁ ሲል ለራሱ ቶሎ ለመሸበት ፣ መሰሉን ለሚገፋው ፣ ባዕድ ቢዘገይ እርስ በርሱ ለሚተላለቀው ፣ ድል በሌለው በወንድማማች እልቂት ለሚውለው ለዚያ ፈርሶ አፍራሽ እባክህ እዘንለት ።
ተስፋ ቆርጦ ስለ መብል ብቻ ለሚያስበው ፣ በልቼ ልሙት ብሎ ለጨከነው ፣ መጽሐፍ ንቆ ጌጥ ለሚገዛው ፣ አሳብ አጥቶ መሣሪያ ለሚያነሣው ፣ ዓይን እያለው ማንበብ ለፈራው ፣ አእምሮ እያለው ማወቅን ለጠላው ፣ እረኛ ተኝቶበት አውሬ ለበላው ፣ ላልኖረላት ቤተ ክርስቲያን መሞት ለሚያምረው ፣ እረኛ አያስፈልገኝም ብሎ ብቻውን ለሚሮጠው ፣ በእባብ ጉድጓድ ላይ እጁን ለሚሰደው ፣ ከደከመው ገራፊ ለአዲስ ገራፊ ተላልፎ ለተሰጠው ፣ ሳያውቅ ያወቀ ለመሰለው ፣ ካልደረስኩበት ብሎ ሽበትን ለናቀው ፣ ክብርና ውርደት ቦታ ተለዋውጠውበት ሽሜ እያለ ለሚሳደበው ለዚያ ሞኝ እባክህ እዘንለት ።
ከሚያሳርፈው ቃልህ የሚያሳብድ አልኮል ለመረጠው ፣ ከሚያውል ድምፅህ የሚያታልል ሱስ ለፈለገው ፣ ከራሱ ጋር ድብብቆሽ መጫወት አልደክምህ ላለው ፣ ትምህርት ብሎ ወጥቶ ለሚባልገው ፣ እያታለለ የገዛ ወላጁን ለሚያራቁተው ፣ ማዘን ለተለየው ፣ ቸርን ለሚያጠቃው ፣ ቀልቡ ለከዳው ለዚያ ትውልድ እባክህ እዘንለት ። እናት አቀልባ ላላወረደችለት ፣ ሁልጊዜ ማሙሽ ለሆነው ፣ በወላጅ ሞት ለመኖር ለሚያቅደው ፣ እየሸነገለ ገንዘብ ለሚለምነው ፣ ልቡ እያወቀው ስህተትን ለተዛመደው ፣ ራሱን ችሎ መቆም ለማይፈልገው ፣ ፣ በምክንያት ታጥሮ ለተቀመጠው ለዚያ ጅምር እባክህ እዘንለት ።
መለኪያው ለጠፋበት ፣ ሌላውን ለመምሰል ለሚከጅለው ፣ የልብስ ሥልጣኔ ብቻ ለሚፈልገው ፣ የገዛ ፀጉሩን ማስተዳደር ላቃተው ፣ አልሰማም ብሎ ሁለት ጆሮው ላይ ድምፅ ሰክቶ ለሚራመደው ፣ ተሸፋፍኖና አቀርቅሮ ለሚሄደው ፣ እኔ ብቻ ሰልጥኜ ሌላው እንኩሮ ሆኖ ቀረ እያለ ለራሱ ለሚነግረው ለዚያ ተላላ እባክህ እዘንለት ። ነጻውን በዋጋ ለሚገዛው ፣ የቃላት ድህነት የክብር መራቆት ለገጠመው ፣ አበላል እንጂ አነጋገር ለማያውቀው ፣ ወሰን አጥቶ ሁሉ የእኔ ነው ለሚለው ፣ ሥራን ጠልቶ መከጀልን ሥራ ላደረገው ፣ በምኞት ብቻ ሳይሠራ ለደከመው ፣ ዘመናዊነትና ጽኑ አስተዳደር ተባብረው ለሚገድሉት ለዚያ ለጋ እባክህ እዘንለት ።
እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው ባየህ ጊዜ ያዘንህ ፣ የእረኛ ስም እንጂ ተግባር ላጣው ትውልድም ዛሬም እዘንለት ። የት ልሂድ ብሎ ትውልድ አይጨነቅ ፣ የት ልደብቀው ብሎ ወላጅ ስለ ልጁ አያምጥ ። ምድር ሰፊ ናት ተብሏል ፣ ትውልድ ዓለም አይጥበብበት ። ዋጋ የለህም የሚልን ድምፅ ወጣት አይስማ ። ዋጋው የሆንከው መድኃኔ ዓለም እባክህ እዘንለት ። ከራሱ ሞኝነት ፣ ከዘመን ማዳለጥ አድነው ። የሚመሩትን አራራለት ፣ የሚወዱትን አሰንብትለት ። ዘመኑን የትውልድን በጎነት የምናይበት አድርግልን ። እባክህን እዘንለት !
መስከረም 2 ቀን 2019 ዓ.ም.