ስለ ፍቅር ሦስት አስደናቂ ገለጻዎች አሉ ፤ እነርሱም፡- እግዚአብሔር ፍቅር ነው ፣ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም ፣ ፍቅር የነፍስ ጨው ነው የሚሉት ናቸው (1ዮሐ. 4፡8 ፣ ቁ. 16 ፤ 1ቆሮ. 13፡8 ፤ ማር. 9፡50)። እግዚአብሔር ፍቅር ነው ስንል እግዚአብሔር ፍቅርን አልተለማመደም ፣ ለዘላለም ፍቅር ነው ። እገዚአብሔር ፍቅር አለው አይልም ፣ ፍቅር የእግዚአብሔር አንዱ መገለጫ ሳይሆን ሌሎች ጠባያቱ ሁሉ የሚወጡት ከፍቅሩ መሆኑን የሚገልጥ ነው ። እግዚአብሔር ፍቅር ነው ተብሎ የተገለጠበት “አጋፔ” የሚለው ቃል ያለ ምክንያት ፣ ጥቅምን ታሳቢ ባለማድረግ የሚወድ ፍቅር መሆኑን የሚያሳይ ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር በመስቀል ላይ በዋለው ልጁ የተገለጠ ሲሆን ፍቅሩ ቃላት ሳይሆን ተግባርና መሥዋዕትነት ያለው መሆኑን ያስረዳል ። ብዙ ሥልጣኔዎች ተነሥተዋል ፣ እንደ ሰናዖር ግንብ መልሰው ፈርሰዋል ። ብዙ ግዛቶች ተመሥርተዋል ፣ እንደ እስክንድር ዘመናቸው ጥቂት ሆኗል ። ብዙ ባለጠጎች ከፍ ብለዋል ፣ ሲወድቁ ቁራሽ አጥተው ሞተዋል ። ለዘወትር የማይወድቅ ነገር በምድር ላይ ማግኘት ከባድ ነው ። ፍቅር ግን ለዘወትር አይወድቅም ተብሎ ተጽፎአል ። (1ቆሮ. 13፡8)። አፍቃሪም ዋጋው አይወድቅም ። ላለመውደቅ ብለን ሀብትን እንሰበስባለን ፣ ሥልጣንን እናደላድላለን ፣ ሠራዊት እናደራጃለን ፣ የትምህርት ወረቀቶችን እናበዛለን ። የነጋው ቀን ለመምሸቱ እርግጠኛ ባልሆነ በዚህ ዓለም ላይ የማይወድቅ ነገር አንድ ብቻ ነው ። እርሱም ፍቅር ነው ።
ምግብን የሚያጣፍጠው ቅመም ነው ። ቅመሞች ከማጣፈጥ ባሻገር መድኃኒትነት አላቸው ። ከቅመሞች አንዱ ጨው ነው ። ጨው ማዳበሪያ ነው ። ፍቅር ጨው ነው ፣ ሰዎችን በመውደድ ብዙ እንዲያፈሩ ማድረግ እንችላለን ። ፍቅር ስንሰጣቸው ደስታና ኃይል ፣ የመቻል ስሜት ያገኛሉ ። የፍቅር ሠራተኛ አይደክመውምና ብዙ ይሮጣሉ ። ሰው የሚደርሰው በእግሩ ሳይሆን በፍቅሩና በተስፋው ነው ። የተስፋ ምንጩ ፍቅር ነው ። የሚወደን ሰው ካለ ብቻ እንሮጣለን ፣ የምንኖርለት ከሌለ መኖር ባዶ እየሆነ ይመጣል ። ዓላማ ማለትም የምንኖርለት ነገር ማለት ነው ። ማዳበሪያ ዘሩ ብዙ እንዲያፈራ ፣ እንዲፋፋ ያደርገዋል ። ፍቅር ካለን ብዙ እንሠራለን ። ጥላቻ የሞላብን ቀን መጀመሪያ አቅም ያንሰናል ፣ ቀጥሎ መንፈሳችን መረበሽና መኖርን መጥላት እንጀምራለን ። ፍቅር ግን ለምድራዊ ሥራ ለሰማያዊ አገልግሎት ሞተር ነው ። ፍቅር ብርሃን ነውና በፍቅር ውስጥ ስንሆን የሚታየን ብዙ መልካም ነገር አለ ። ጨው ማጣፈጫ ነው ፣ ጣዕም ያለው ነገር ተወዳጅ ነው ። ፍቅር ሕይወትን ያጣፍጣል ። ከዛሬው ስኬት ላይ ለመድረሳችን ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው የሚወዱን ሰዎች ናቸው ። ፍቅር ኑሮን አስደሳች ያደርጋል ። ፍቅር ያለው ሰው አካባቢውን ሁሉ ይለውጠዋል ፣ ኮቴው ሲሰማ ሰዎች መዝለል ይጀምራሉ ። ወደ ሞት የሚሄደውን ሰው የፍቅር ድምፅ ይመልሰዋል ። ጨው መድኃኒት ነው ፣ ፍቅርም ብዙ ሰባሮችን የሚጠግን ፣ የቆሰሉ ልቦችን የሚፈውስ ነው ። ጨው ምግቦች ሳይበላሹ ረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ያደርጋል ፣ ፍቅርም ያለንን መልካም ነገር ይጠብቃል ። የጥንት ተዋጊዎች ጨውን በተሸነፈ ከተማ ላይ ይነሰንሱታል ፣ ፍቅርም በተሸነፈው በሰይጣን ከተማ ላይ የሚነሰነስ ፣ የድል ምልክት ነው ። አፍቃሪ አሸናፊ ነው !
ይቀጥላል
መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም.