ማፍቀር ማለት መኖር ማለት ነው ። ፍቅር የሌለው ሕይወት የተዘጋ ቤት ነው ፣ የተዘጋ ቤት ይሸታል ፣ ያዘምማል ። ፍቅር የሌለው ቤት ምንም ቢያምር የተዋበ የመቃብር ስፍራ ነው ። ፍቅር የሌለው ተቋም ምንም ቢደራጅ ፈራሽ ነው ። ብዙ ሰው ሌላውን ማፍቀሩን እንደ ውለታ ይቆጥረዋል ፣ ፍቅር ከሌለው ግን መኖር እያቃተው እንደሚመጣ አይገነዘብም ። የምንወደው ለራሳችን ብለን ነው ። ፍቅራችንን የምንገልጥለት ስምንት ቢሊየን ሕዝብ አለ ። ፍቅር እንደ ዕቁብ ጣልና ልጣል የሚባል አይደለም ። ፍቅር እንደ ጅብ ጉዞ መጠባበቅ ያለበት አይደለም ። ፍቅር ሲያዘን መታዘዝ ተገቢ ነው ። መልካም መዓዛ ባለበት ንቦች ይታያሉ ። ፍቅር ሲኖረን መንፈሰ እግዚአብሔር ይቀርበናል ። መላእክት ሊያዩን ይጓጓሉ ። ምነው የእርሱ ጠባቂ ባደረገኝ ይላሉ ። ሕይወት ያለ ፍቅር ትርጉም የላትም ። ብዙ ሰዎች ገንዘብን ብቻ ሲያሳድዱ ፍቅርን ያጡታል ። ከልጆቻቸው ጋር ያላሳለፉ ወላጆች በመጨረሻ የማጣት ስሜት ያሰቃያቸዋል ። ልጆቹም የወላጅን ፍቅር ስላላገኙ ቢሳካላቸው እንኳ ትልቅ ጉድለት ይሰማቸዋል ። የሰው ልጅ ትልቅ ማንነቱ ረቂቅ ነው ። ሥጋው ማደሪያ ፣ ሳጥን ፣ ቤት ነው ፣ አዳሪው ግን ነፍሱ ናት ። ስለ አዳሪው ማኅደሩን ማክበር ይገባል ፣ ስለ ነፍስ ሥጋ የተከበረች ናት ። የሰው ልጅ ግን የሚበዛው ማንነቱ መንፈሳዊ ወይም ረቂቅ ነው ። ለመንፈሳዊ ማንነቱ ፍቅር አስፈላጊው ነው ።
ብዙ ፍለጋዎች ይሳካሉ ፣ የሚወደንን ሰው ብንፈልግ ግን አይሳካልንም ። ምክንያቱም ካልወደድነው በቀር የሚወደን ማንም የለም ። መወደድ ዕዳ ነው ፣ መውደድ ግን ማትረፊያ ነው ። ሁሉ ወዳጅ ሊሆን አይችልም ፣ ሁሉን መውደድ ግን እንችላለን ። ፍቅር ሞተርዋ ያለው ሰማይ ስለሆነ ከሰው ፈጽማ እንስሳትንና እጽዋትንም መውደድ ትችላለች ። ፍቅር ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ነው ። የሁለት ነፍሶች በሰማያዊ መዓዛ መተሳሰር ነው ። በአጭር ቃል ማፍቀር መኖር ፣ መኖርም ማፍቀር ነው ። በዘመናችን ፍቅር የሚለው ቃል ትክክለኛ ፍቺውን አላገኘም ። ቅዱሱ ፍቅር የርኵስ ምኞት መግለጫ ሆኗል ። ሰዎች ፍቅርን ሲያስቡ በተቃራኒ ጾታ መካከል ያለውን ግንኙነት ብቻ ያስባሉ ። እግዚአብሔር እኛን የወደደበትን ፍቅር ስናስበው ቃላት ሊገልጡት የማይቻላቸው ፣ የምንኖርበት ምሥጢር ነው ። ፍቅር ቅዱስ ነው ። እውነተኛ ፍቅርም የሚመነጨው ከእግዚአብሔር ዙፋን ሥር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ እንደ ፍቅር የተጻፈለት ፣ የተሰበከ ፣ የተተነተነ ፣ የአደባባይ የጥናት ርእስ የሆነ ፣ የተዘመረለት አይገኝም ። ፍቅር ግን አሳብ ሳይሆን ተግባር ፣ ቃል ሳይሆን ኑሮ ነው ።
ሰዎች ይወዱኛል ብሎ የሚያስብ በዚያም የሚደሰት አለ ። መቼም እገሌ ይወደኛል ከማለት እወደዋለሁ ማለት እርግጠኝነት ይሰጣል ። ፍቅር ማለት እኛ ሌሎችን መውደዳችን እንጂ ሌሎች እኛን መውደዳቸው አይደለም ። ብዙዎቻችን መወደድ እንጂ መውደድ አንፈልግም ። ራሳችንን እንደ ተወዳጅ ብቻ የምናይበት ጊዜ ብዙ ነው ። ምላሽ የማይሰጥ ነገር ሁሉ ጣዖት ነው ። ጣዖት ማለት የአምላክን ስሙን የያዘ ግብሩ የሌለው ማለት ነው ። እውነተኛው አምላክ ግን የሚሰማ የሚመልስ ነው ። በሌላው መወደዱ ደስ እያለው የፍቅር ምላሽ የሌለው እርሱ ጣዖት ነው ። ደግሞም ቃሉ “የፍቅር ዕዳ አይኑርባችሁ” ይለናል (ሮሜ 13፡8) ። ዕዳ ዕረፍት አይሰጥም ፣ ዕዳ አያስሞትም ። ጣር የያዘው ሰው የእገሌ ዕዳ አለብኝ መልሱልኝ ይላል ። ዕዳ በሰላም አያስሞትም ። የፍቅር ዕዳ ያለበትም ዕረፍት የለውም ፣ ሞቱም የሰላም አይደለም ። ሌላውን የሚወድ ጀግና ነው ። ጀግንነት ጥላቻን ተዋግቶ ማሸነፍ ነው ። ጀግና በሰላም ያርፋል ። በዓለም ታሪክ እንዳየነው ጀግኖች ሁሉ የፍቅር ሰው ናቸው ። ፍቅር የሌለው ግን ጨካኝ እንጂ አፍቃሪ አይባልም ።
ፍቅር ቀኑን በሙሉ እንሰማዋለን ፣ ትክክለኛ ትርጉሙን ግን አላወቅነውም ። ፍቅር ማስታወቂያ ሲሠራለት እናያለን ። የፍቅር ፍቺ ግን ያለው ቀራንዮ ላይ ነው ። እንደ ብራና በተወጠረው በቅዱሱ በኢየሱስ ሥጋ “እስከዚህ እወዳችኋለሁ” የሚል ጽሑፍ ይነበባል ። ስለ ፍቅር በየሰዓቱ ብንሰማም እውነተኛው ፍቅር የቱ መሆኑን ገና አለየንም ። ፍቅር የቃላት ትንታኔ ፣ የስሜት ድምቀት መስሎአቸው በዚያ ብቻ የሚፈጽሙ አሉ ። ፍቅር ግን ፍጻሜው ሰማይ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ማንንም ለመጥላት አልኖርኩም ብለን ለራሳችን ስንናገር ያን ጊዜ በሰላም እናርፋለን ። ፍቅር ለመኖር ብቻ ሳይሆን በሰላም ለማረፍም ያስፈልጋል ። ፍቅር ማሰብ ብቻ ከሆነ አሳብ ተቆጣጥሮት ተግባር ያጣል ። ከብዙ ሰው የምላስ ጫፍ ላይ ፍቅር አለ ። ፍቅርን አብዛኛው ሰው አጣጥሞ ያወራታል ፣ ጥቂቶች ግን ያዩአታል ። ዘመናዊው ዓለም ፍቅርን የአድናቆት ቃል ፣ የአበባ ልውውጥ ፣ የስሜት እብደት ፣ የፈቃደ ሥጋ ድግስ አድርጎታል ። ፍቅርን ቃላት ተክተውታል ።
የፍቅርን ትርጉም በዚህ መንገድ የተረዳ ትውልድ የፈረሰ ትዳር ፣ የተበተኑ ልጆች ባለቤት ሆኗል ። ትውልዱ በመለያየትና በመከፋፋት ጉዳት ውስጥ ይገኛል ። ፍቅር መቀመጫው ልብ ነው ። ፍቅር ስሜት ቢኖረውም ስሜት ብቻ አይደለም ። አንዳንድ ምግቦችን ላንወድ እንችላለን ፣ መብታችን ነው ። አንዳንድ መኪናዎችን ላንወድ እንችላለን ፣ ተገቢ ነው ። ሕያው የሆነውን ፍጥረት አለመውደድ ግን አንችልም ። ፍቅር አማራጭ አይደለምና ። መላው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ስለ ፍቅር ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቃል ይገለጥ ከተባለ “ፍቅር” ይባላል ። እግዚአብሔር ዓለምን የሠራበት መሠረቱ ፍቅር ነው ። እኛም ሥራችንን መሥራት የሚገባን በፍቅር ተነሣሽነት ብቻ ነው ።
ይቀጥላል
መስከረም 7 ቀን 2019 ዓ.ም.