መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -3

የትምህርቱ ርዕስ | ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -3

ጌታችን በኢየሩሌም ውስጥ ካለው የበዓል ሁካታ ፣ በከተማዋ ውስጥ ከሚፈጸመው ግፍ አልፎ የሚመጣውን ሮማዊ የጦር ጀነራል ቲቶስን አሰበ ። ጌታችን፡- “ይህን ሁሉ ታያላችሁን ? እውነት እላችኋለሁ ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” ያለው ትንቢት የተፈጸመው በቲቶስ ነበር ። (ማቴ. 24 ፡ 2) ። ጌታችን ይህን ትንቢት ሲናገር ቤተ መቅደሱ በልዩ ጌጥ እየታደሰ ነበር ። ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ የመቅደሱን ውበት ማየት ይቻል ነበረ ። ጌታችን ከዛሬው ውበት የሚመጣውን ጥፋት አየ ። የመጨረሻው ዘመን የሚናበበው በሦስት ነገሮች ነው ። በእስራኤል ፣ በኢየሩሳሌምና በመቅደሱ ነው ። የእስራኤል መፍረስና መመለስ ፣ የኢየሩሳሌም ጥፋትና የስበት ማዕከል መሆን ፣ የመቅደሱ መፍረስና ለሦስተኛ ጊዜ መሠራት የመጨረሻው ዘመን ማሳያ ነው ። ጌታችን ስለ ኢየሩሳሌም ሲናገር ስለ መላው ዓለም ጥፋትም አብሮ ተናግሯል ። ሁለተኛውን መቅደስ ያደሰውና ያፈረሰው ሮማዊ ሲሆን ሦስተኛውን መቅደስ የሚሠራውና የሚያፈርሰውም ሐሣዊ መሢሕ ሮማዊ ነው ። ይህም፡- “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ ፥ አንባቢው ያስተውል” የተባለው ትንቢት ነው (ማቴ. 24 ፡ 15) ።

የሰባ ዓ.ም. ጥፋትና የመጨረሻው ቀን በጣም ይመሳሰላሉ ። ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ እየመጣ ስላለው መከራ ሲናገር ክርስቲያኖች ምልክቱን አይተው እንዲሸሹ አስጠንቅቆ ነበር ። “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ” ብሎ ነበር ። (ሉቃ. 21 ፡ 20) ። በ66 ዓ.ም ከተማዋ ስትከበብ የጌታን ቃል ያስታወሱት ክርስቲያኖች በዮርዳኖስ ምሥራቅ ወደምትገኝ ፔላ ወደ ተባለች ከተማ ሸሹ ። በዚህም ከጥፋት ዳኑ ። በመጨረሻው ቀንም የመጨረሻው ጽዋ ሊደፋ ሲቃረብ ክርስቲያኖች ይነጠቃሉ ። ከመከራውም ይድናሉ ። በዚህም የጌታን ስም የሚጠራ ይድናል የሚለው ቃል ኪዳን ይፈጸማል ።

የሰባ ዓ.ም ጥፋት እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ተጽእኖ አለው ። እስራኤል መሥዋዕተ ኦሪትን ማቅረብ ያቆሙበት ነው ። አሁንም መቅደሱ አልተሠራምና መሥዋዕትን ማሳረግ ቢፈልጉም አይቻላቸውም ። መቅደሱን ለሦስተኛ ጊዜ ሲሠሩ ግን የዓለም ፍጻሜ እየተቃረበ ይመጣል ። የሚገርመው መቅደሱን በአንድ ቀን ውስጥ ለመሥራት ዝግጅቱና ቁሳቁሱ አልቋል ። መቅደሱ የሚሠራው በቀድሞ ቦታው አሁን አል-አቅሳ መስኪድ በተሠራበት ላይ በመሆኑ ታላቅ ሁከት በዓለም ላይ የሚያስነሣ ርእስ ነው ። የመጀመሪያው የሰሎሞን መቅደስ የፈረሰው በነሐሴ አካባቢ ነው ። ከ400 ዓመታት አገልግሎት በኋላ በ586 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በባቢሎናውያን ፈረሰ ። በአስገራሚ ሁኔታ ሁለተኛው መቅደስም የፈረሰው በነሐሴ ወር ነው ። በዚህ ጥፋት ከአንድ ሚሊየን በላይ አይሁድ ሞተዋል ። ከ97 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማርከዋል ። ለባርነት ተሽጠዋል ። ገዥዎች እምቢ ሲሉ ምርቃት ይሁናችሁ ተብለው ተሰጥተዋል ። በ70 ዓ.ም. ከአገራቸው የወጡ አይሁድ 1900 ዓመታት ያህል ቆይተው የተመለሱት በ1948 እአአ ነው ። ዘመናዊት እስራኤል የሰባ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላት አገር ናት ። ሰባ ዓ.ም. ኢየሩሳሌም በሙሉነት የፈረሰችበት ነው ።

በ66 ዓ.ም. ሮማዊው አስተዳዳሪ ጌሲየስ ፍሎሩስ የመቅደሱን ገንዘብ ወሰደ ። በዚህም ታላቅ ሕዝባዊ ቍጣ ተነሣ ፣ የተዋጊ ቡድኖች ተፈጠሩ ። ዓመፁን ለማስቆም ኔሮ የሮም ንጉሠ ነገሥት የሆነው ቬስፓስያን የተባለ የጦር ጄነራልና ልጁን ቲቶስን ወደ ኢየሩሳሌም ላከ ። እስከ 69 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ምድር የቆየው ቬስፓስያን በሮም በተነሣው የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ሲመለስ ልጁን ቲቶስን ተክቶ ነበር ። ቬስፓስያን 79-81 ዓ.ም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሆኗል ። ጄነራል ቲቶስ ያመፁትን አይሁድ ዙሪያቸውን በመክበብ በረሀብ ቀጣቸው ። ከበባው ከ66 – 70 ዓ.ም ድረስ የዘለቀ ነበር ። ከረሀቡ ጽናት የተነሣ ልጆቻቸውን እስከ መብላት ደርሰው እንደ ነበር ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይገልጣል ። ከበባው ባመጣው ችግር ረሀብና በሽታ ሕዝቡን ጨረሰ ። የእርስ በርስ መከፋፈልም ተከሰተ ። ምዕራብ ኢየሩሳሌምን አንዱ ቡድን ፣ የመቅደሱን ዙሪያ ሌላው ቡድን ተቀራመተ ። ለማምለጥ የሚሞክረውን አይሁዳዊ በጭካኔ ይገድሉት ነበር ። በ70 ዓ.ም ሮማዊው የጦር ጀነራል ቲቶስ ከበባውን ሰብሮ ገባ ። ኢየሩሳሌምን አፈረሰ ። ለ600 ዓመታት ያገለገለውን የዘሩባቤል መቅደስን አቃጠለው ።

ጌታችን ከደብረ ዘይት ተራራ ቁልቁል ሲወርድ ለኢየሩሳሌም ያለቀሰው ይህን ቀን አይቶ ነው ። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቁጭ ብሎም በማቴዎስ 24 ላይ የሰፈረውን ትንቢት ተናገረ ። ይህ ትንቢትም የኢየሩሳሌም ጥፋትና የመጨረሻውን ቀን በሕብር የገለጠበት ነው ።

ኢየሩሳሌም ለምን ጠፋች ? የመጀመሪያው መሢሑን መቀበል ባለመቻልዋ ነው ። ብዙ የሃይማኖት ቡድኖች በመነሣታቸው ሕዝቡ ተከፋፈለ ። የእርስ በርስ ክፍፍልም ለውጭ ጠላቶች አቅም ሆነ ። መቼም ሞተን ካልጠበቅነው የሚገድለን የለም ። መከፋፈል ጠላትን ሞቶ መጠበቅ ነው !

ይቀጥላል

ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ