የከረመው ልቅሶ ዛሬ ለሰማው ሰው አዲስ ነው ። ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል ይባላል ። ቢሆንም ለተረሳ ኀዘን ትኩስ ዕንባን ማፍሰስ አይገባም ። ሰዎች ያለፈውን አሰቃቂ ጉዞአቸውን የነገሩን እግዚአብሔር እንዴት እንዳዳናቸው አስበን ለምስጋና እንድንቆም እንጂ ትኩስ ኀዘን እንድናቀርብ አይደለም ። ባለፈ ክረምት ቤት እንደማይሠራ ባለፈ ኀዘን ላይ መቆየት አይገባም ። ሰው ወደፊት የሚዘረጋው የትላንቱን እየተወ ነው ። መከራን በመካሪነቱ መቀበል ፣ በትምህርቱ መደሰት እንጂ ከቀዝቃዛ ስፍራ እያወጡ ማሞቅ ተገቢ አይደለም ። አንድ ሕዝብ የሚያድገው የትላንት ክፉ ገጠመኙን ለዕድገት ሲጠቀምበት ብቻ ነው ።
አንዳንድ ቀሊል ሰዎች የደረሰባቸውን አጋነው ያወራሉ ፣ ያልደረሰባቸውን ፈጥረው የቀጥታ ስርጭት ያህል አሁንነትን ሰጥተውት ይናገራሉ ። የውሸት እያለቀሱ የእውነት የማስለቀስ አቅም አላቸው ። እነዚህ ሰዎች ጉዳታቸውን የሚናገሩት የሰውን ልብ ለመያዝና ለመሄድ ቢያስብ እንኳ በይሉኝታ ታስሮ እንዲቀር ነው ። ያንን ሁሉ ነግሬህ እንዴት ጥለኸኝ ትሄዳለህ ለማለት አሳዛኝ ድርሰታቸውን ሌሎችን በጥፋተኝነት ስሜት ለማሰቃየት ይጠቀሙበታል ። ትላንትን ልንተርከው እንችላለን ፣ ልንኖረው ግን አይገባንም ። ዛሬ ላለንበት ነገር የትላንቱ መሰላል ነበረ ።
ከደረሰብን ክፉ ነገር በላይ የደረሰልን እግዚአብሔር ይበልጣል ። የልጅነት ስብራታቸውን ያልረሱ ሰዎች ዛሬ ዕረፍታቸውን ማጣጣም አልቻሉም ። ዛሬ እየበሉ የተራቡበትን ዘመን እያሰቡ ትኩስ ዕንባ የሚያፈሱ ፣ ብዙ ቤት ይዘው ጥገኛ ሆነው የኖሩበትን ዘመን እያስታወሱ የሚተክዙ አያሌ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ሌሊትን አልፈው ብርሃን ያገኙ ናቸው ። ሌሊት ያልቀደመበትን ብርሃን እየፈለጉ ነው ። በጥንተ ተፈጥሮም ሌሊት ይቀድማል ፣ ብርሃን ይከተላል ። የቀደሙት ነገሥታት በድለው አጥፍተው ይሆናል ። እንኳን በሩቅ ያሉት መሪዎች ቤተሰብ ይጎዳዳል ፣ እናትና ልጅም ይካሰሳል ። አውሮፓውያን በአፍሪካና በእስያ ፣ በደቡብ አሜሪካ የፈጸሙትን ዛሬ እንኑረው ቢባል ዲፕሎማሲ በዓለም ላይ አይኖርም ነበር ። በቅርብ ዘመናት ጥቁርና ነጭ አንድ ላይ የማይሳፈሩበት ታሪክ በአሜሪካ ነበረ ። የቆሙትና መልካም ለማድረግ አጋጣሚ ያላቸው እየበደሉ ሙታንን መውቀስ ተገቢ አይደለም ። የትላንቱን ክፉ ነገር እኛ እንዳንደግመው መማር እንጂ እርሱን ዛሬ ላይ አምጥተን መኖር አይገባም ።
ንጉሥ ሳኦል በድህነት የኖረ ነበረ ፣ ዳዊትም እረኛ ሁኖ በስቃይ አሳልፏል ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታውን ክዶ እንደገና ለአደራ በቅቷል ፣ ጳውሎስ እስጢፋኖስን አስገድሎ የቤተ ክርስቲያን አባት ሁኗል ። እግዚአብሔር ዘንድ ስንጠጋ የምናገኘው ትልቅ ጸጋ የትላንትን ክፉ ገጠመኝ መርሳት ነው ። ከመጠን በላይ ልታይ ልታይ ማለት የትላንትን ኑሮ አለመርሳትና በበታችነት ስሜት መሰቃየት ነው ። ብዙ ሰው ትልቅነትን ለራሱ ከሚፈልገው በላይ ትንሽ አድርገው ላዩት ሰዎች ለማሳየት ይከጅለዋል ።
ያለፈን ነገር መልሰን ማስተካከል ካልቻልን በዚያ ውስጥ ማለፍ ስለነበረብን ሆኗል ። ለማይመለሱ ቀኖች ራስን በትኩስ ዕንባ ማቃጠል ተገቢ አይደለም ። ንስሐ ትላንትን መካሻ ነው ። በፍቅር የፈጠረን በይቅርታ እንደገና ይቀበለናል ። የደረቀን ዕንባ በአዲስ ዕንባ ማርጠብ ላለመደሰት መጣር ነው ። ሕይወት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የምትሆንበት ጊዜ ብዙ ነው ። ጥላን አትከተለኝ ማለት አንችልም ፣ እንዲመራን ግን መፍቀድ የለብንም ። የተቀበረን ኀዘን መክፈት ቁስልን ማፋፋም ነው ። ትላንትን እያስታወሱ ሊያውኩን ከሚፈልጉ ሰዎች መራቅ ተገቢ ነው ። የተጽናናን ሰው በማወክ የሰውን ቀን እንዳንሰርቅ መጠንቀቅ ይገባል ። ቁስል ይጠግጋል ፣ ይድናል ። እንደገና ካመረቀዘ የበለጠ ይጎዳል ። እኛ የረሳነውን ጉዳት መርሳት ያቃታቸው ሰዎች አጠገባችን ካሉ ታመዋል ማለት ነው ። የዛሬው ዕንባ ትላንትን መካስ ካልቻለ ፣ በትላንት ኀዘን ዛሬን ማጣት አይገባንም ። አልኖርኩትም ብለን ስለ ትላንት እያዘንን ዛሬም እያመለጠችን ነው ። ካለፈው ኀዘን የሚመጣው ተስፋ ይበረታል ። እግዚአብሔር ሞትን በኀዘን ለውጦልን ከኖርን ዕድለኞች ነን ። ያጣነውን ሳይሆን የተቀበልነውን የምስጋና ርእስ ማድረግ ብልህነት ነው ። የዳነን ቁስል በስንጥር መቆጥቆጥ ትኩስ ዕንባን ያመጣል ።
የዛሬ አቅም ለዛሬ እንጂ ለትላንት አይሆንም ። የትላንቱን ከተማርንበት ለነገ የእውቀት ስንቅ ነው ። የራስን ጉዳት ብቻ ከማሰብ በጣም የተጎዱትን ማሰብ አስፈላጊ ነው ። ዛሬ የመጣውን ሰውና ዕድል እንዳናይ ዕንባ ሸፍኖናል ። ኀዘነተኛን ሰው ሁሉም ይርቀዋል ። ደስታ ግን እንደ ሽቱ ከሩቅ ይጠራል ። ደግሞም ኀዘን ኀዘንን ፣ ደስታ ደስታን ይጠራል ። ፈገግ ስትሉ ሰው ሁሉ ፈገግ ይላል ። የዘራችሁትን ታጭዳላችሁና ደስታን ዘርታችሁ ሐሤትን እጨዱ ።
ቀናችሁ ይባረክ !
ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም.