መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት » ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -2

የትምህርቱ ርዕስ | ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት -2

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በፋሲካ ሰሞን ነው ። በዓል ሊያከብሩ የመጡ ፣ የተስፋ አገራቸውን ናፍቀው የተሰበሰቡ አይሁድ ዘመዶቻቸውን በማግኘት በዚህ ሁሉ ደስታ ውስጥ ነበሩ ። ምንም እንኳ በሮማውያን ቅኝ ገዥነት ልባቸው ቅሬታ ቢኖረውም ጎዳናዎቹንና ሕንፃዎቹን እያዩ ይዘናጉ ነበር ። ከተማይቱ በታላቅ ምቾት ውስጥ ብትመስልም ከፊት ለፊት ግን የተደገሰላትን ሞት ነዋሪዎችዋ አልተረዱም ነበር ። ሕንፃዎች ተደጋግፈው የሚቆሙት ሰዎች ኅብረት ሲኖራቸው ብቻ ነው ። ማኅበረሰብ ሲፈርስ ሕንፃዎችም በግድ ይፈርሳሉ ። ሰው ሲፈርስ ለሰው የሆነው ሁሉ አብሮ ይፈርሳል ። መገዛዛት ፣ አንዱ የአንዱን ድርሻ በቅሚያ መብላት ፣ ገዥዎችን ተጠግቶ ሌላውን ማጥቃት በዚያች ከተማ ትልቅ ቂም አርግዞ ነበር ። ጌታችን ባሻገር ያለውን አየ ። ስለዚህም ከቀኑ በፊት ለከተማይቱ አለቀሰላት ። በቀኑ የሚያለቅሱ የቅርቡን ብቻ የሚያዩ ሰዎች ናቸው ። የሩቁን የሚያዩ ግን ቀድመው ያለቅሳሉ ። አዋቂ ሰው ችግሩን ሳይሆን የችግሩን ጥላ ቀድሞ ያያል ። ጥበብ ችግርን መፍታት ብቻ ሳይሆን መጪውን ችግር ማየትም ነው ። ዝናቡ ከመምጣቱ በፊት የሚጠለል ሰው አለ ፣ ዝናቡ ካባራበት በኋላ ጥላ የሚፈልግ አለ ። ያቺ ከተማ በጸጥታ ግድያ ውስጥ ነበረች ። በሞትዋ ላይ ተኝታ ነበርና ጌታ አለቀሰላት ። መላ አጥተው የሚሞቱ በትንሹ ያስለቅሳሉ ፣ መላ እያላቸው የሚሞቱ ግን በብዙ ያስለቅሳሉ ። አባ መላ ክርስቶስ ነው ።

ጌታችን ቁልቁል ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ሲመለከት የበጎች በር ይታየው ነበር ። ይህ በር ለዓመታት ለመሥዋዕት የሚሆኑ በሮች የሚገቡበት ነበር ። በዚህ በር ሰዎች አይገቡም ነበር ። ጌታችን ግን በዚህ በር ገብቶ እንደ ነበር እናነባለን (ዮሐ. 5 ፡ 2) ። እርሱ ለመሥዋዕትነት ስለ መጣ ፣ በሚሰብር አውሬ ሳይሆን በሚታረድ በግ መልክ ስለ መጣ በዚህ በር ገባ ። በዕለተ ሆሳዕናም የበጎችን በር ሲያይ ለዓለም የሚሠዋበት ጊዜ ቀርቦ ነበር ። ለራሱ ለማዘን ፣ ትንሽም ለመተከዝ ምክንያት ነበረው ። እርሱ ግን ዘመኑን በሙሉ መስቀሉን ተሸክሞ ኖረ ። የዚህ ሕመም ከፍ ያለ ነው ። እንደሚሞቱ የተነገራቸው ፣ ዓመት ቀራችሁ ፣ ወራት የሚባልላቸው ሰዎች ምን ያህል ጉዳት እንደሚያስተናግዱ ይታወቃል ። የሚሞትበትን ቀን ያውቀዋልና ዘመኑን በሙሉ በመስቀል ሕመም ውስጥ ኖሮአል ። ቀራንዮን ማዶ እያየ የእኛን መዳን አስቦ ይደሰት ነበር ። ዕለተ ሞቱን እንደ ሽልማት ቀን ናፈቃት ። የኢየሩሳሌምን ሞት ባሰበ ጊዜ አለቀሰ ። ከተማ ሰው ነው ፣ ሰው ከተማ ነው ። ሰው ከሌለበት ከተማው ቆንጆ የመቃብር ስፍራ ነው ። ደግሞም የአራዊት መፈንጫ ፣ ጭውታው የፍርሃት ምንጭ ነው ።

በመስቀሉ ጥላ ውስጥ ቢሆንም ለተደላደለችውና ለምትስቀው ከተማ አለቀሰ ። በርግጥም የጥፋትዋ መንስኤ አዳኙን አለመቀበል ነው ። ፍቅርን የማይቀበል ጭካኔን ይቀበላል ። ዛሬ የምናሳልፈው ችግር ምናልባት ትላንት የቀለድንበት በረከት ግፍ ይሆናል ። ዛሬ በሚጠሉን እጅ የወደቅነው የሚወዱንን አሰቃይተን ሊሆን ይችላል ። እንኳን የፍቅር የውኃም ጡር አለው ። ቀራንዮ የሞሪያ ተራራ ነው ። በዚህ ተራራ ላይ ይስሐቅ በአባቱ ሊሠዋ ነበር ። እግዚአብሔር ግን ለአብርሃም ራርቶ ነጭ በግ አዘጋጀለት ። ያ በግም የይስሐቅ ቤዛ ሆነ ። ያ በግ የአዳምን ምሳሌ የሆነው የይስሐቅ ቤዛ ነበር ። በዚያ በግ ውስጥ አብርሃም ባለ መስቀሉን ኢየሱስን አየው ። ሁለት ሺህ ዓመታት የሚጨባበጡበት ጊዜ እየደረሰ ነው ። የኦርና አውድማ በዚሁ በቀራንዮ ነበር ። የመጣው መቅሰፍት እንዲመለስ ዳዊት መሠዊያ የሠራበት ስፍራ ነው ። ይህ ስፍራ ከኦርና በገንዘብ የተገዛ ነው ። (2ዜና 3፡1፤ 2ሳሙ. 24፡18-25)። በዚህ ስፍራ ማለትም በቀራንዮ ሰሎሞን መቅደሱን ሠራ ። ለስርየተ ኃጢአት ብዙ መሥዋዕቶች በዚህ ስፍራ ላይ ቀርበዋል ። ጌታችንም በመጨረሻ ሳምንት ወደዚህ ስፍራ ገሰገሰ ። እርሱ የመሥዋዕቶች ሁሉ መደምደሚያ ነው ።

ለይስሐቅ የሰጠውን ተስፋ እያሰበ ነው ፣ ሕዝቡን በመቈጠሩ ምክንያት በዳዊት ላይ ቍጣ መጥቶ ነበር ። ይህን ያህል ወገን አለኝ ብሎ ለመመካት ባደረገው ነገር እግዚአብሔር አዝኖበት ነበር ። በኦርና አውድማ በቀረበው መሥዋዕት መዓቱን የከለከለው ጌታ ዛሬ በለቢሰ ሥጋ ያንን ስፍራ እያየ ነው ። መሥዋዕቱና መራራውን ምርጫችንን ለማጣፈጥ የሚጤሰውን ዕጣን አሰበ ። እነዚያ ወገኖች ግን መታደላቸውን አላወቁትም ። አንድን ግዙፍ ዋርካ ተሸክሞ ከግብጽ ነቅሎ ከነዓንን ላይ ተከለ ። ይህን ያህል ዘመን ተሸክሞ ሳይደርቅ በኢየሩሳሌም ላይ ተከለው ። እነርሱ ግን የመጨረሻውን ተስፋቸውን አጨለሙት ። በሰማይና በምድር ያሉትን ስጦታዎች ሁሉ የሚጠቀልል አንድ ስጦታ አለ ፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። የሚገርመው ይህን ስጦታ እምቢ ላለች ከተማ አለቀሰ ። ማልቀስ ምክርን ለናቀ ሰው ነው ።

የሚገርመው ከነዓንን ሲያወርሳቸው ጣዖታውያንን ነቅሎ ነው ። አሁን ግን እኔነታቸውን የሚወዱ ጣዖታውያን ሆነዋል ። ያ የከነናውያን ጽዋ እንደሚደርስባቸው ዘነጉ ። በነቢያት የሚያፌዙ ፣ ቅዱሳንን የሚገድሉ ሆኑ ። ይህን ሁሉ ደግሞ የሚያደርጉት እግዚአብሔርን ለማስከበር እንደሆነ ያስቡ ነበር ። ክርስቶስን በቅጽበት ራእይ ቢያዩት ፣ በሕልም ቢመለከቱት ሲነቁ ያስደነግጣል ። ደስታውም ፍርሃትን ይታገላል ። 33 ዓመት ከ3 ወር ሥጋ ለብሶ ቢያዩት አልደነገጡም ። ፍቅሩና ውለታው የማያስደነግጠን የእኛ ወኪሎች ነበሩ ። ኔሮን ቄሣር መግደል ቢታክተው ምነው የሰው ሁሉ አንገት አንድ በሆነልኝ አለ ይባላል ፣ ኢየሱስ ግን የሰውን ሁሉ ሞት ይወስዳል ። ከቁምነገር ይልቅ ዋዛን ለመረጡት አለቀሰላቸው ። ዛሬም የዘላለም ሞት እየጠበቃቸው የሳቅ ኮክቴል ለሚሹት ይህ ልቅሶ ይመለከታቸዋል ። በእውነት ወደ ክርስቶስ መጥቶ በባዶ የተመለሰ የለም ።

ይቀጥላል

ነሐሴ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች