የትምህርቱ ርዕስ | የምድር ጨው ናችሁ -3

“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤” (ማቴ. 5 ፡ 13 ) ።

ጨው የምንሆነው በምድር ላይ ነው ። ምድሩ ጣዕም አልባ አልጫ ነው ፣ ባለጠጋና ድሀ እኩል የሚያለቅሱበት ዓለም ነው ። ታዋቂ ሰዎች ያልታወቀ ኀዘን አላቸው ፣ ባለሥልጣናት ጭስ የማይታይበት ቃጠሎ ውስጥ ናቸው ። ምድር ከተደሰተባት ያዘነባት ይበዛል ፣ ጣዕም አልባ አልጫ ናት ። ይህን ሁኔታ የሚለውጥ ክርስቲያን ነው ። ጨው ከሌለ የሁሉም ምግብ ጣዕም አንድ ዓይነትና የሚገፋ ነው ። ሁሉም ምግብ የራሱን ጣዕም እንዲያወጣ ጨው ያግዘዋል ። ክርስቲያንም ሰዎች ያላቸውን ጸጋ ፣ ተሰጥኦና ሙያ እንዲያወጡት ያበረታታል ። በዚህ ዓለም ላይ ትርፍ ጸጋ የለም ፣ የማይጠቅም ተሰጥኦም አይገኝም ፣ ሁሉም ሙያውን ቢያበረክት እንኳ የምድር ጉድለት ላይሞላ ይችላል ። ጸጋ እንደ እሳት ነው ፣ የሚቆሰቁሰው ይፈልጋል ። እሳት ለራሱ ከሚጠቅመው ይልቅ ለሌሎች ይጠቅማል ፣ እግዚአብሔር ጸጋን የሚሰጠውም ለእኛ ጥቅም ነውና ጸጋ ያላቸውን ሰዎች መንከባከብ ይገባል ። ጸጋቸው ሲገለጥ ይበልጥ እየተባረክን እንመጣለን ።

አማኝ የሆነ ሰው በሌላው ጸጋ የሚቀና ሳይሆን የሚያቃና ፣ የሌላውን ጸጋ የሚያዳፍን ሳይሆን የሚያፋፍም ፣ የሚያጣጥል ሳይሆን የሚያቀጣጥል ነው ። ብዙ ሰዎች ጸጋው አላቸው አፍረውና ፈርተው ተቀምጠዋል ። ትንሽ ስንገፋቸው ብዙ ይራመዳሉ ፣ ጥቂት ስንደግፋቸው በብዙ ይገለጣሉ ። መኪና ካልሄዱበት እንደማይጠቅም ፣ መሣሪያ ካልሠሩበት ሥራን እንደማያቀል ጸጋም ካልተጠቀሙበት ተመላሽ ይሆናል ። የሚመለሰውም የምድር በረከት ነውና መጠንቀቅ ይገባል ። የሚገርመው ጸጋ የሌለው አማኝ የለም ። ተሰጥኦ የሌለው ሰው የለም ፣ ሙያ የሌለው ግለሰብ አይገኝም ።

ሁሉም የራሱ ጣዕምና ጥቅም አለው ። የምግቡን ጣዕም ጨው እንደሚያወጣው የሰዎችንም ጣዕምና ጥቅም የምናበረታታ መሆን አለብን ። ይልቁንም እንደ እኛ ያለ አገር የራሱን ምሁር እያቃለለ የፈረንጅ መሃይም ያከብራል ። የራሱን አባት እያረከሰ እነ አባ ቀዮን ቅዱስ ቅዱስ ይላል ። ለ1600 ዓመታት የግብጽ ጳጳሳትን አክብሮ የተቀበለው ፣ በወቄት ወርቅ እጅ መንሻ እየሰጠ ያመጣው ወገን የራሱ አባት ሲሾም ከመጀመሪያው ጀምሮ መጠላለፍ መጣ ። ሁለተኛው ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ በገመድ ታንቀው ተገደሉ ። የራስን መናቅና በራስ ወገን ላይ መጨከን ትልቁ በሽታችን ነው ፣ እንግዳ ተቀባይ ራሱን ግን የማይቀበል ማኅበረሰብ እንዳንሆን ያስፈራል ። የእኛ ወገን ከሆነ ገና ብቅ ሲል የምላስ ጅራፍ ፣ የነገር ደንደስ እናሳርፍበታለን ። የራሳችን ሰው ሲራቆት አበደ ፣ ካባ ሲለብስ እዩኝ እዩኝ አለ እንላለን ፣ ፈረንጅ ሲራቆት በእነርሱ ሁሉ ያምራል እንላለን ። ቀድሞን የነቃውን ሰው እብድ ነው እያልን ማንም እንዳይቀርበው አድርገን ሺህ ጊዜ እንገድለዋለን ። “እብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል” እያልን እውነት ተናጋሪውን እብድና ዘበናይ እንለዋለን ። ልጅ እየቀጣን “እውነቱን ካልነገርከኝ አለቅህም” እንለዋለን ፣ ከዱላው ብዛት የተነሣ እውነቱን ሲነግረን ዱላውን እናብሳለን ። እውነቱ ሲነገረን ዱላ የምንጨምር በመሆናችን ልጆቻችን የሚዋሹ ሆኑ ።

ከደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑትን በእስር ቤት ሳሉ ስለ ቀይ ሽብር ስጠይቃቸው የሰጡኝ ጸጸት የሞላበት መልስ እንዲህ ይላል፡- “በጎዳና የጣልነው ሰው ብቻ ሳይሆን ለአገር የሚጠቅም አእምሮ ነው” ብለውኛል ። ስለ ደራሲው በዓሉ ግርማ አሟሟት የጠየቅኋቸው አንድ የደርግ ባለሥልጣንም፡- “የሚያሳዝነው ጓድ ሊቀ መንበሩ መጽሐፉ እርሳቸውን እንደሚያወድስ ሳያውቁ ገደሉት ፣ ከሞተ በኋላ መጽሐፉን አነበቡት” ብለውኛል ። መጽሐፉን ሳናነብ ደራሲውን እናወግዛለን ። የሚጠቅመንን ጽሑፍ የጻፈውን ደራሲ ሳናነብ እንገድለዋለን ፣ የመግደል ሥልጣን ስናጣ ስሙን እንበክላለን ። የሚገርመው በቁሙ ያሰቃየነውንና ለሞት የዳረግነውን ሰው ሲሞት ቅድስናውን እናበዛለን ። የመታሰቢያ ቀናት እናውጃለን ። በቁሙ አፈር ፣ ሲሞት አበባ እንሰጠዋለን ። ሬሳ አንጋሽ ሁነን የምንቀጥለው እስከ መቼ መሆኑን ገና አልወሰንም ። የእኛ ሥራ የሚጸና የሚመስለን የሌላውን ስናጠፋ ነው ። ብቸኛ ሊቅ ፣ ብቸኛ ሠራተኛ ሁነን መታየት እንፈልጋለን ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመጨረሻው ሰዓት፡- “እኛ እስከዚህ ሠርተናል ፣ የእኛን አትንኩ የራሳችሁን ጨምሩበት ፣ ትውልድ ፍርዱን ይሰጣል” በማለት ተናግረዋል ይባላል ። የራስን መጨመር እንጂ የሌላውን ሥራ ማጥፋት ተገቢ አይደለም ። አሊያ ሁልጊዜ ጀማሪ እንሆናለን ። በአገራችን የጀመረ ሥራ እንጂ የቀጠለ ምን አለ ? በአገራችን የጀመሩ ባለሙያዎች እንጂ የቀጠሉ የታሉ?

ጨው ምግቡ ሲበስል ይጨመራል ። በጨው ውስጥ ያለው ጥቅም እንዳይጠፋና ምግቡ ጣዕሙን እንዲያወጣ መጨረሻ ላይ ይደረጋል ። ክርስቲያን ሌላውን የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ራሱም ጥቅም ሰጪ ነው ። የሚሰብክ ብቻ ሳይሆን የሰበከውን የሚኖር ነው ። ስጡ  ብሎ የሚናገር ብቻ ሳይሆን በመስጠት ያለውን ደስታና በረከት የሚለማመድ ነው ። ጨው ሥጋ ፣ ወይም አትክልት መሆን አይችልም ። ሌሎችን አብነት እናደርጋለን እንጂ እኛነታችንን ማጥፋት የለብንም ። የተመረጠልን ነገር መልካም ነው ። ጾታችን እግዚአብሔር የመረጠው ነውና ልንወደው ይገባል ። ጸጋ የሰጠን ባለንበት ስፍራ የጎደለውን አይቶ ነውና ልናከብረው ይገባል ። ጸጋና ወንበሩ መገናኘት አለባቸው ። የራሳችንን ጸጋ እየጠላን የሰውን ጸጋ መጎምዠት አይገባንም ። ከትልቁ እግዚአብሔር የምንቀበለው ትንሽ ነገር የለም ። ከሁሉ በላይ ብስል ሰዎችን ተግተን መምከር ይገባናል ። ሞኝና ሰነፍ እንዲሁም የበታችነት የሚሰማው ሰው ምክርን አይወድም ።

ይቀጥላል
ጥቅምት 26 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ