“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤” (ማቴ. 5 ፡ 13 ) ።
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመጨረሻው ሰዓት ከሥልጣን ላወረዱአቸው የደርግ አባላት የተናገሩት፡- “እናንተ ሁላችሁም ልጆች ናችሁ ፤ እንደ ልጆችም የልጅነት ድርጊት ፈጽማችኋል ። አገራችሁን አታውቋትም ። አደጋው አገራችሁን ወደ ጥፋት ትመሩአታላችሁ የሚለው ነው” ብለዋል ። ልጅ ጨዋታው ያስቃል ፣ ኃላፊነቱ ግን ልብን አያሳርፍም ። “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም” እንዲሉ ልጅነት መመጠን አይችልም ። ይበቃል ወይ ? ቀጥሎ ምን ሊከሰት ይችላል ? ብሎ አይጠይቅም ፣ ጅምር ላይ ቆሞ ፍጻሜውን መለካት አይችልም ። መሪነት አሻግሮ ማየት ፣ ላለው ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም ትውልድ ማሰብ ነው ። ለቀጣይ ትውልድ እያሉ ሀብታቸውን የማይነኩ አገራት አሉ ። መሪነት የቅርብን ማየት ብቻ ሳይሆን አሻግሮ መድረሻውን መመልከትም ነው ። ታላላቅ አገራት ተብለው የሚጠሩት ሁሉ መሪዎቻቸው በዕድሜ የበሰሉ ናቸው ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የተኩት የደርጉ ሊቀ መንበር የዕድሜቸው ቍጥር 32 ነበር ። ለብዙ ጥፋትና ለማያልቅ መከራ አገርን የሚዳርጉ በዕድሜ ጠገግ ያላሉ ወጣት መሪዎች ናቸው ። ሰው ስሜታዊነቱን ጨርሶ እውነትን እንዲይዝ ፣ በጉልበት ማሰብን አቁሞ ብልሃትን እንዲጠቀም ፣ በተበደለ መሳለቅን አቁሞ ለፍትሕ እንዲቆረቆር ዕድሜ እጅግ አስፈላጊ ነው ። ንግሥናም ጵጵስናም ከሃምሳ በኋላ ሲሆን ብስለት ፣ ራስን መግዛት ፣ መጪውን ማየት ይኖረዋል ።
ያገለገለን ሰው ጉድለት ቢኖርበትም የሠራውን መልካም ማሰብ ተገቢ ነው ። የሠራውን ሁሉ አላይም ብሎ ዓይውንን መጨፈን አይገባም ። አንድ ዓይናችን ስህተትን ሲያይ አንደኛው ዓይናችን ደግሞ በጎነቱን ማየት አለበት ። ጨርሶ ክፉ ፣ ጨርሶ ደግ በዓለም ላይ ላይኖር ይችላል ። ቅንነት የምንለውም ከብዙ ጥፋት ውስጥ ያለውን አንድ መልካም ነገር ማየት መቻል ነው ። ንጉሡ በዚያ ዕድሜአቸው ቢንከባከቡአቸው እንኳ ሟች ነበሩ ። የ80 ዓመት ሽማግሌን መግደል ታሪክ ማቆሸሽ እንጂ ጀግና የሚያሰኝ አይደለም ። ይህ እርሳቸው እንደ ተናገሩት የልጅነት ሥራ ነው ። ልጅ የልጅ ሥራን መሥራቱ የተለመደ ነው ። አለመብሰል ለራስ ጸጸት ፣ ለአገር ጉዳት ያመጣል ። አንድ ትልቅ የደርግ ባለሥልጣን ስለ ስድሳዎቹ ሚኒስትሮች በእስር ቤት ሁነው የነገሩኝን አስታውሳለሁ፡- “እነዚህን ሰዎች በነጻ ብንለቃቸው እንኳ የገዛ ስኳራቸውና የደም ግፊታቸው ፣ ደግሞም የሆነው ነገር ብስጭት ይገድላቸው ነበር ፣ እነዚህን ሰዎች መግደላችን ትልቅ ውርደት ነው” ብለውኛል ።
“ከበሮ በሰው እጅ ያምራል ፣ ሲይዙት ያደናግራል” ይባላል ። ከበሮ ቀላል የሚመስል ነው ። ሲይዙት ግን አስቸጋሪና ሙያ የሚፈልግ ነው ። ሥልጣንም በርቀት ቀላል ይመስላል ፣ ሲይዙት ግን ከባድ ነው ። የገዛ ቤተሰብን ማስተዳደር ፣ ራስን መግዛት ባቃተበት ዓለም ሥልጣን ቀላል አይደለም ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለሰዋስወ ብርሃን ደቀ መዛሙርት በምረቃ በዓል ላይ እንዲህ ብለው ተናግረው ነበር፡- “እስከ ዛሬ ድረስ ይህን ለምን አላደረጉትም ? እያላችሁ ትወቅሱን ነበር ፣ አሁን ያንን ለምን እንዳላደረግነው የምታውቁበት ቀን ደርሶአል ፣ ሠርታችሁም ወደምትሰደቡበት መድረክ እንኳን ደኅና መጣችሁ” ብለዋል ። ክርስቲያን የምድር ጨው ነው ሲባል በስሎ የሚያበስል ፣ የራሱን ጣዕም ጠብቆ ለሌላው ጣዕም የሚሰጥ ማለት ነው ። እንደ ጨው ዘር ተበትነው የሚል አባባል አለ ። ጨው ከንጉሥ ቤት እስከ ድሀዋ ቤት የሚገኝ ነው ። ክርስቲያንም በሁሉ ስፍራ ፣ በመላው ዓለም የሚገኝ ነው ። ጌታችን ጨው ትሆናላችሁ አላለም ፣ ጨው ናችሁ ብሎናል ፣ የሚያስፈልገው የራስን ዋጋ አውቆ መንቀሳቀስ ነው ። ጨው ለራሱ አይኖርም ፣ ክርስቲያንም ለወገኑ ይኖራል ፤ በምግቡ ውስጥ ካሉት ርካሹ ነገር ጨው ነው ። ጨው በትንሽነቱ ፣ በርካሽነቱ ፣ ባለ መታየቱ ፣ እዚህ ነኝ ያለሁት ብሎ እዩኝ ባለ ማለቱ ተፈላጊ ነው ። ክርስቲያንም እንደ ትንሽ ቢታይ አይከፋውም ፣ ትልቅ ሥራ አለውና ። ትልቅ ስም ያላቸው ትልቅ ሥራ የላቸውም ። ክርስቲያን ራሱን የሚያዋድድ አይደለም ። ራሱን በልኩ የሚያይ ትሑት ነው ። ካልታየሁ ብሎም መጋረጃ ሲገልጥ አይውልም ፣ መልኩንና ፎቶውንም ለሽያጭ አያቀርብም ።
ጨው የሚገኘው ከነጠፈ ባሕር ነው ። ውቅያኖሶች ቢደርቁ ትልልቅ የጨው ተራሮችን እናገኛለን ። ባሕር የዓለም ምሳሌ ነው ። ባሕር መጨረሻው አይታይም ፣ ዓለምም መጨረሻ የላትም ። ባሕር እንደ ተናወጠ የሚኖር ነው ፣ ዓለምም መልካም ዜና የላትም ። ባሕር ያሰጥማል ፣ ዓለምም ብዙዎችን ታስክዳለች ። ባሕር ያሳስቃል ፣ ዓለምም አታላይ ናት ። ባሕርን በዋና ማቋረጥ አይቻልም ፣ ዓለምን በራስ ጉልበት መካድ ከባድ ነው ። ባሕር ብዙ ጭነት ያለውን መርከብ ትሸከማለች ፣ ዓለምም ብዙ ጉድ ይዛለች ። ባሕር የዓለም ምሳሌ ነው ፣ ባሕሩ ሲነጥፍ ጨው ይገኛል ። ዓለማዊነት ከውስጣችን ሲወጣ የምድር ጨው መሆን እንጀምራለን ። ዓለሙ ጣዕም ያጣው እኛ ጨው ስላልሆንን ነው ። የምናየው ዝርክርክ ሁሉ ክርስቲያን ድርሻውን ስላልተወጣ የመጣ ነው ።
ተፈጸመ
ኅዳር 1 ቀን 2019 ዓ.ም.