መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የታይታ ጥማት » የታይታ ጥማት -1

የትምህርቱ ርዕስ | የታይታ ጥማት -1

አንዲት እኅት በጣም ከርቀት እየተጓዘች ቦሌ መድኃኔ ዓለም ታስቀድሳለች ። “ይህን ያህል ርቀት መጥተሸ የምታስቀድሽው ለምንድነው? ብሎ አጠገቤ ያለው ሰባኪ ይጠይቃታል ። ይህች እኅት ያለ ሐፍረት የሰጠችው ምላሽ፡- “ብዙ ሀብታሞች ስላሉ ከእነርሱ ጋር መተዋወቅ ለሥራዬ ይጠቅመኛል ብዬ ነው” የሚል ነበር ። ሰው እግዚአብሔር ቤት የሚሄደው ከሰው ደካማ ጥቅም ፈልጎ መሆኑ ይገርማል ። ንግዱን ለማሳለጥ የእግዚአብሔር ቤትን መንገድ ያደረገ ብዙ ሰው አለ ። እውነተኛውን ባለጠጋ እግዚአብሔርን ትቶ በሸፍጥ ባለጠጋ የሆኑትን ማሳደዱ መንፈሳዊ ክስረት ነው ። ሰማያዊ ዋጋ እየተዘነጋ ያለበት ዘመን ነው ። በሰማያዊ ዋጋ የማያምን ሰው በእግዚአብሔር መኖርም አያምንም ። እየቀደሰ ድምፁን ለሽያጭ የሚያቀርብ ዲያቆን ፣ ሥጋ አምላክን እየፈተተ በቀጥታ ስርጭት የሚገባ ካህን እያየን ነው ። እግዚአብሔርን እያሰብን አምልኮን ማቅረብ ካልቻልን ከከንቱ ጩኸት የሚያልፍ አይደለም ። መንፈሳዊ መሆን አንፈልግም ፣ መንፈሳዊ መባል ግን እንፈልጋለን ። የሰዎችን ልብ ሰርቀን ያላቸውን ነገር ለመውረስ የምንጠቀምበት የዝርፊያ መንገድ ከሆነ ያሳዝናል ። “እርስዋ እኮ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ናት” ለመባል በቀሚሳቸው መሬት እየጠረጉ የሚሄዱ ፣ በልባቸው ግን ቁምጣ የለበሱ ብዙዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች አደገኛ ማንነት አላቸው ።

ድራማ ተዋንያን ሲሠሩት ሙያ ነው ፣ ኑሮ ድራማ ሲሆን ግን ግብዝነት ነው ፣ ሃይማኖት እዩኝ እዩኝ ሲል በምድር በሰማይ ቅጣት የሚያመጣ ነው ። የእኛ ዘመን ለታይታ ራሱን የሰጠ ዘመን ነው ። ከመንግሥተ ሰማያት ይልቅ ዝናን የሚፈልግ ብዙ ሰው አለ ።

“የእኔ ልጅ ጨዋ ነው” ለማለት ልጃቸውን እየቀረጹ አደባባይ የሚያወጡ እናቶችን እያየን ነው ። ልጁ የተረጋጋ ፣ ጭምት ፣ ብዙ የማይናገር ፣ ተደብቆ መኖር የሚፈልግ ነው ። እናቲቱ ግን ካሜራ ደግና ታስጨንቀዋለች ። የአዋቂዎች ልብ ወደ ልጆች ፣ የልጆች ልብ ወደ አዋቂዎች እየተቀያየረ መጥቷል ። ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አባቶቻቸው ደግሞ ወደ መጠጥ ቤት ይሄዳሉ ። ይህ ዘመን ቦታ የተለዋወጥንበት ዘመን ይመስላል ። በቤተ ክርስቲያን ያለው ልቡ ዓለም ላይ ነው ፣ ዓለማዊው ልቡ ያለው ቤተ ክርስቲያን ነው ። ታይታን መውደድ መንፈሳዊነትን እንድንከስር አድርጎናል ። በልብስ ቢጸደቅ ኖሮ እኛ እንጸድቅ ነበር ፣ ዘመናዊ ፈሪሳዊ ሆንን እንጂ ምንም ጥቅም አላመጣንም ። ሰው ለሚያየው ነገር በጣም ተጨንቀናል ፣ እግዚአብሔር የሚያየውን ነገር ዘንግተናል ። የሰውና የእግዚአብሔር እይታ የተለያየ ነው ።

መጽሐፍ፡- “ሰው ፊትን ያያል ፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው” ይላል ። (1ሳሙ. 16 ፡ 7) ። ሰው ፊት ላይ ይቀራል ፣ እግዚአብሔር ግን ዘልቆ ልብን ያያል ። በቤተ ሙከራ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ዓይን ሊያያቸው የማይችላቸውን ነገሮች በአጉሊ መነጽር ያያሉ  ። የሥነ ፈለክ ባለሙያዎች በርቀት መመልከቻዎች የከዋክብትን ዓለምና ፕላኔቶችን ያያሉ ። የሰው ልብ ከእነዚህ የረቀቀ ነው ። ልብን ማየት አንችልም ፣ ብናይም አንኗኗርም ነበር ። አይቶ መሸፈን የሚችለው ጌታ ልብን ያያል ። ብዙ ሰው ቤቱን አዝረክርኮ ከቤቱ ሲወጣ ግን ተሸቀርቅሮ ነው ። ሰው ለሚያየው ጥለትና ካባ ሲጨነቅ ራሱ ለሚያየው የውስጥ ልብስ ግን አይጨነቅም ። ሰው የሚያየው ፊትን ነውና ፊቱን ያልኖረ ፊት ለማስመሰል ብዙ ወጪ ያወጣል ። እኛም ፊትን እናያለን ። ከልቡ ከሚወደን ፣ በተግባር ከሚቆምልን ሰው ይልቅ ፈገግ የሚልልንን ፣ አቆላምጦ የሚጠራንን ፣ አንገቱን ሰበር የሚያደርግልንን ፣ የሚስቅልንን ፣ ልክ ነህ የሚለንን እንመርጣለን ። ሸንጋይ ነንና ለሸንጋዮች ተላልፈን ተሰጥተናል ።

“የገንፎ ውኃ በገንፎ ያልቃል” ይባላል ።  የጉቦ ገንዘብ የሚያልቀው መጠጥ ቤት ነው ። ጉበኛው ልጁን ኢንተርናሽል ትምህርት ቤት በማስተማሩ ይኮራል ፣ ዓለም አቀፍ ወንጀል ተምሮ እንደሚመጣ ግን አያውቅም ። የጉቦ ገንዘብ ልጆችን ያሳብዳል ። አገሪቱን እስካሁን የመሩ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት የተማሩ አይደሉም ። እውቀት የጥልቅ ፍላጎት ውጤት እንጂ የትምህርት ቤቱ አድራሻ ጉዳይ አይደለም ። ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤቶች ችግኝ ማፊያ ናቸው ። እዚህ ይፈላል ፣ ልጁ እዚያ አገር ይተከላል ። የተማሩበት አገር ላይ ለመሄድ እየሰለጠኑ ነው ። ብቻ ጉበኛው ወደ መጠጥ ቤት ሲሄድ መሳቢያው ዘፈን ነው ። ዘፈን ከሩቅ ይጠራል ፣ መጠጥ ወንበሩ ላይ ያስቀራል ፣ ዝሙት ሕይወትን ያበላሻል ። ዓለም ጆሮን በሚማርክ ነገር እየሳበች ወደ ጉድጓድ ትከታለች ። የግፍ ገንዘብ በግፍ ያልቃል !

የታይታ ዘመን ተግሣጽን አይወድም ። በየግጥም ምሽት አስተዳዳሪዎች ሲታሙ በደስታ የሚሰማው ታዳሚ ስብከት ስማ ሲባል ያንገፈግፈዋል ። የታይታ ሕይወት ራስን ማየት አይፈልግም ። ሰዎች ስለሚሉት ነገር እንጂ እርሱ ስለሚፈልገው ነገር ምንም አያውቅም ። ቀልደኞች ከሃይማኖት አባቶች በላይ ተከታይ አላቸው ። ወንድሙ እየወደቀ ፣ ካህን በመንበር ላይ እየታረደ ባለበት ዘመን “ጨጓዬን አመመኝ” የሚል ወጣት ካገኘን የእንግሊዝ የኳስ ቡድን ተሸንፎበት ነው ። የመዝሙር ግጥም ሱባዔ ተገብቶ ፣ በጸሎት ሁኖ ሲሠራ እናውቅ ነበር ። ኳስ እያየሁ የጻፍኩት ነው የሚሉ ብዙ ገጣሚያን አሉ ። መድኃኒቱ አልፈውስ ያለው በክብሩ ስላልያዝነው ነው ። ግን በዚሁ አይቀጥልም ። በርግጠኝነት መነጋገር አለብን ። እንደ ጠፉት አብያተ ክርስቲያናት ልንጠፋ እንችላለን ። እግዚአብሔር በከንቱ ፉከራ አይገኝም ፣ በሩን የሚከፍተው ለእውነተኛ ንስሐ ነው ። ከአምልኮ መልስ የሰው ክብር የምንነካውን ፣ ትሑት የሆነልንን የምንረግጠውን ፣ በጎሣ በሽታ ተይዘን ግድያን በሥላሴ አምሳል ላይ የምናውጀውን እኛን ከተወን ሰዶምና ገሞራ ፍርድ ተዛብቶብናል ብለው ክስ ማቅረባቸው የማይቀር ነው ።

ያንተን ፈቃድ ለመምረጥ አብቃን !

ይቀጥላል
ኅዳር 2 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ