የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አልዕሉ አልባቢክሙ

ቅዳሴ ኤጲፋንዮስን የሚቀድሰው ካህን “አልዕሉ አልባቢክሙ” ማለት “ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” በማለት ወደ ሰማይ ማደሪያ ምእመናንን ሲያነቃቃ ምእመናንም እንዲህ ብለው ይመልሱለታል ፡- “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” ይሉታል ። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ባሕርይና ዘላለማዊ ብርታት ማወጅ ይጀምራል ።
እግዚአብሔር በገናንነቱ ገናና ነው ፤
በቅድስናውም የተቀደሰ ነው ፤
በምስጋናውም የተመሰገነ ነው ፤
በክብሩም የከበረ ነው ።
ከመቼ ወዲህ የማይሉት ቀዳማዊ ነው ፤
እስከ ዛሬ የማይሉት ማእከላዊ ነው ፤
እስከዚህ የማይሉት ደኃራዊ ነው ።
ለአነዋወሩ ጥንት የለውም ፤
ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም ፤
ለዘመኑ ቊጥር የለውም ፤
ለዓመታቱም ልክ ቊጥር የለውም ፤
ለውርዝውናው ማርጀት የለበትም ፤
ለኃይሉም ጽናት ፣ ድካም የለበትም ፤
ለመልኩም ጥፋት የለበትም ።
ለጥበቡ ባሕር ፣ ድንበር የለውም ፤
ለትእዛዙም ይቅርታ ፣ መስፈርት የለውም ፤
ለመንግሥቱ ስፋት ፣ አቅም ልክ የለውም ፤
ለአገዛዙም ስፋት ፣ ወሰን የለውም ።
በኅሊና የማያገኙት ሥውር ነው ፤
በልቡናም የማይረዱት ምጡቅ ነው ፤
አእዋፋት የማይደርሱበት ረጅም ነው ፤
ዓሣዎች የማይዋኙበት ጥልቅ ነው ።
ከተራሮች ራስ ይልቅ ከፍ ከፍ ያለ ነው ፤
ከባሕር ጥልቅነት ይልቅ ጥልቅ ነው ፤
ነገሥታት የማይነሣሡበት ጽኑ ነው ፤
መኳንንት የማይቃወሙት አሸናፊ ነው ።
የጥበበኞችን ምክር የሚያጠፋ ጥበበኛ ነው ፤
የሚመክሩትን ሰዎች አሳባቸውን የሚያስረሳ ዐዋቂ ነው ፤
የጸኑ ልጓሞችን የሚፈታ ኃያል ነው ፤
የኃጥአንን ጥርሶች የሚያደቅ ፣
የትዕቢተኞችንም ክንድ የሚቀጠቅጥ ብርቱ ነው ።
የግብዞችን ፊት የሚያዋርድ ክቡር ነው ።
የዝንጉዎችን ብርሃን የሚያርቅ ከሃሊ ነው ።
ባልንጀራ የሌለው አንድዬ ነው ፤
ዘመድ የሌለው ብቸኛ ነው ፤
                    /ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ቊጥር 2-10/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ