የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሐዋርያው እንድርያስ

“እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፡- መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው” /ዮሐ. 1፡42/።
እንድርያስ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት አገልግሎቱ ባይዘገብም በሦስት ታላላቅ ቦታዎች ግን አሻራውን ትቷል። የመጀመሪያው ወንድሙን ጴጥሮስን ወደ ክርስቶስ ማምጣቱ ነው። አንድ ሰባኪ ለነገ አገልግሎቱ እያሰበ ሳለ፣ ነገ ብዙ ሕዝቦች ወደ ንስሐ ይመለሳሉ፣ በአገልግሎትህ ይድናሉ የሚል ሕልም ያያል። በማግሥቱም ብዙ ሕዝብ እየጠበቀ ሳለ አንድ የ14 ዓመት ልጅ ብቻ በትምህርቱ ተማርኮ፣ በፍቅር ሰምቶ ሄደ። በዚህ ጊዜ ሰባኪው አዘነ። ተስፋው የጨለመ መሰለው። ያ ሕጻን ግን አድጎ ከእርሱ በእጥፍ ጸጋ የሚያገለግል፣ ሚሊዮኖችን የሚመልስ ሆነ። እግዚአብሔር ስለ ሚሊየኖች እየተናገረን ይሆናል። የሚመጡት ግን ሚሊየኖች አይደሉም። ሚሊየኖች ቢመጡም የምናስቀምጥበት ቦታ፣ የምናገለግልበት አቅም የለንም። እግዚአብሔር ግን ስለ ፍሬዎች የሚናገረው ዘሩን እያሳየን ነው። ዘሩ አንድ ነው፣ ፍሬው ግን ብዙ ነው። አብርሃም ዘሩ እንደ ምድር አሸዋ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዛ ሲነገረው የሚያየው አንድ ልጅ አልነበረውም። ይስሐቅ ተወልዶ ቢያይም የይስሐቅን ልጆች ግን አላየም። ነገር ግን አምኖ ሞተ።
አንድ ሰው አንድ አይደለም። እግዚአብሔር አንዱን ሰው ሳይሆን በአንዱ ሰው ውስጥ ያሉትን አእላፋት ያያል። እንድርያስም ወንድሙን ጴጥሮስን አመጣ። ጴጥሮስ ግን አንድ ሰው አልነበረም። በበዓለ ሃምሳ ዝምታንና ፍርሃትን ሰብሮ የሰበከ፣ ሦስት ሺህ ሰው በአንድ ቀን ያሳመነ ነው። በዚያ ውስጥ እንድርያስ አለበት። እንድርያስ ዛሬ ጴጥሮስን ወደ ክርስቶስ ቢያመጣው እግዚአብሔር ደግሞ በጴጥሮስ የሚመጡትን ያይ ነበር። ሰዎች የዛሬውን ቢያዩልን እግዚአብሔር ግን የወደፊቱንና የዘላለሙን ያይልናል። ስለ ጴጥሮስ ስናስብ ስለ እንድርያስ ማሰብ አለብን። ስለ ሙሴ ስናስብ ከጡት ጋር ራእይ ስለሰጠችው እናቱም ማሰብ አለብን። ብቻውን የቆመ የለም። በዚህ ዓለም ላይ ትልቁ ውሸታም ከማንም ምንም አልተቀበልኩም የሚል ነው። ያልተቀበለ የለም። የማይሰጥም የለም። አንድ ባለ ቅኔ፡- “በሁለት ነገር አዝናለሁ ሁሉንም አውቃለሁ በሚልና ሁሉንም አላውቅም በሚል። ሁሉንም አውቃለሁ የሚል ትዕቢተኛ፣ ሁሉንም አላውቅም የሚል ልግመኛ ነው” ብሏል። ትዕቢተኛ አልተቀበልኩም አልቀበልም የሚል ነው። ልግመኛም እየሰጠ ሳይሆን እየታዘበ ለመኖር የወሰነ ነው። የገንዘብ ስስት ይዞት ረሀብተኛን ያለፈ ሳይቀጣ እንደማይቀር የእውቀት ስስትም ይዞት የእውቀት ረሀብተኛን ያለፈ ከቅጣት አያመልጥም። ዛሬም ከሚታየው ኑሮአችን፣ አገልግሎታችንና ስኬታችን ጀርባ የቆሙ፣ የዛሬዋን ህልውናችንን ያገለገሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ልናስባቸው፣ ልንመርቃቸው፣ ለመልካምነታቸው እውቅና ልንሰጥ ይገባል። ተረቱ፡- “ድመት ወልዳ ትበላለች” ነው። ብዙ ጊዜ ግን የምናየው የተወለደችው እናቷን ስትበላ ነው። የአገልግሎት አባቶቻቸውን የበሉ ስንት ናቸው? የክፉ ቀን ወዳጆቻቸውን የነከሱ ስንት ናቸው? የሚታየው ነገር ሁሉ በማይታይ ነገር የቆመ ነው። ስለዚህ ከሚታየው ጴጥሮስ ጀርባ የማይታየው እንድርያስ አለ። በዓለም ላይ ትልቁ ወዳጃችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ያመጣን፣ እውነትን ያሳወቀን ነው። ልክፈለው ብንል እንኳ ውለታውን መክፈል አይቻለንም።
ለሥጋ ቤተሰቦች ገንዘብ እንጂ ወንጌልን የሚያስብ ጥቂት ነው። እንድርያስ ግን ለወንድሙ ለጴጥሮስ ያሰበለት ሰማያዊ ነገር ነው። ዛሬ ወንጌሉ ደጅ ደጁን እንጂ ወደ ቤታችን ሊገባ አልቻለም። ከሃይማኖት የራቀ ትዳር ያለው አገልጋይ፣ ዓመፀኛ ልጆች ያሉት ቄስ ስንት ይሆን? ሊቃነ ጳጳሳት ሾፌሮቻቸውን አስተምረው ይሆን? “ሸክላ ሠሪ በገል ይበላል” የሚባለው ይህ ነው። ለአገር የሚተርከው አጠገቡ ላለው ካልተረፈ አስቸጋሪ ነው።  በእርግጥ ጌታችን ነቢይ በገዛ አገሩ አይከብርም ብሏል። አያስተምርም ግን አላለም። ቤትን መማረክ ለደጁ አገልግሎት ደጋፊ ማግኘት ነው። እንድርያስ ይህን ሁሉ ጥበብ የተቀዳጀ ሰው ነው።
እንድርያስን ለሁለተኛ ጊዜ የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ ስድስት ላይ ነው። አምስት ሺህ ሰዎች የበሉት የበረከት እንጀራና ዓሣ በእንድርያስ የተገኘ ነው። ጌታ ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ይህን ዓለም ፈጥሮአል። በየዕለቱ ግን የሚሠራው ካለው ነገር ላይ በማብዛትና በመለወጥ ነው። ለዚህም ወይን ጠጅ የሆነው የቃና ዘገሊላው ውኃ ተጠቃሽ ነው። አምስት ሺህ ሰዎችን ለመመገብ እርሾ የሚሆን ጥቂት ነገር አስፈለገ። አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና እንዳለ የተናገረው እንድርያስ ነው። ሕጻንን ማንም ልብ አይለውም። ከዚያ አልፎ የያዘውን የእንጀራ ቊጥር ማንም ልብ አይልም። እንድርያስ ግን የተናቁትንና የማይታዩትን የማየት ጸጋ ነበረው። በዚህ ምክንያት አምስት ሺህ ሰው እንዲጠግብ ሆነ። እንድርያስ አሁን ደግሞ አምስት ሺህ ሰዎችን አገለገለ። ሥራው ማቅረብ ነው። የማይቆረቊር፣ ትክክለኛው ቦታ የሚያደርስ የብርሃን ሠረገላ ነው። ዛሬም የእንድርያስ ዓይን ቤተ ክርስቲያን ያስፈልጋታል። ጉባዔው ሲደረግ የባለጠጎቹ ወንበር ባዶ ከሆነ ሰባኪው ልቡ ትር ትር በሚልበት ዘመን እንድርያስ ያስፈልጋል። ቅዳሴው እየተከናወነ የመኳንንቱ መቆሚያ ባዶ ሲሆን ምን ተቀየሙ የሚለው ቀዳሽ የእንድርያስ ልብ ያስፈልገዋል። በእውነት ለአእላፋት እየሰበክን የምንሰብከው ግን ለጥቂት ባለጠጎች ነውና እግዚአብሔር ይቅር ይበለን። አገልጋዮች ሲገናኙ የሚጠያየቁት ምን ይሆን? ደህና ደህና ሰው ይዘሃል? የሚል ነው? ባለጠጎች የሚሰጡ ይመስላሉ እንጂ አይሰጡም። ግን መግደርደር ይችላሉ። ብልጥግናቸው የበረከት ሳይሆን አብዛኞቹ የብልጠትና የስልት ነው። ቢሰጡም የሚበዙት በክርስቶስ ፍቅር ተነክተው ሳይሆን ለማስታወቂያ የሚከፍሉትን አስልተው ነው። ቤተ ክርስቲያን የእንድርያስ ዓይን ያስፈልጋታል። ስትጨነቅ የባለጠጎችና የምሁራን ቦርድ ሳይሆን የምእመናንን ጸሎት ልትፈልግ ያስፈልጋታል። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ሺዎችን የሚያጠግብ ጸጋ የያዙ ሕጻናት አሉ። እነርሱን ማየትና ማገልገል አልተቻለም። አንዳንድ ምስክርነቶችን የሚናገሩ አገልጋዮችን ስንሰማ፡- “ብዙ በደል ደርሶብኝ ከስብከት ቦታዬ ታግጄ የሕጻናት አገልጋይ ተደርጌ ነበር አሁን ግን…” ይላሉ። በእውነት አንድን ሕጻን ማገልገል ቀጣዮቹን ሰባና ሰማንያ ዓመታት ማገልገል ነው። ሕጻናትን ማገልገል እንደ ቅጣት አድርጋ የምትሰድ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ትኖራለች? ሕጻናትን ማገልገል እንደ ቅጣት የሚያስብ አገልጋይ እንዴት ልናፈራ እንችላለን? በእምነት የሚሰሙን ሕጻናት ናቸው። አንዳንድ ቦታም በሽተኛ አጥማቂ እንዲሆኑ በቅጣት የሚላኩ አሉ። እዚያ ቦታ መላክ የነበረበት በጸጋም በጸሎትም የበረታ ቄስ ነበር። እንድርያስ ግን ሕጻናት የያዙትን በትክክል የሚያውቅ ሐዋርያ ነበር።
ዛሬ ሕጻናት የሚሹት ምንድነው? ቀርበን ፍላጎታቸውን ማጥናትና በዚያ መሠረት ልናሳድጋቸው ይገባል። እኛ ከምንመርጥላቸው የተሰጣቸውና ዝንባሌአቸው የሆነውን ብናይ የበለጠ በረከት ይሆኑናል።
እንድርያስን ለሦስተኛ ጊዜ የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 12 ላይ ነው። “ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን” የሚሉ የግሪክ ሰዎች ወደ ፊልጶስ መጡ። ፊልጶስም የእንድርያስን ጠባይ ያውቃልና ነገረው። ፊልጶስና እንድርያስም ለጌታችን ነገሩት። በዚህ ጊዜ ጌታ ድንቅ የሆነውንና ሁልጊዜ የምንጠቅሰውን ትምህርት ተናገረ፡- “ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች…”  አለ /ዮሐ. 12፡23-24/። የጌታችን ንግግር ለግሪክ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም በመስቀል ላይ የምታይበት ጊዜ ደርሷል በማለት ስለ መስቀሉ ተናገረ። የግሪክ ሰዎች ብዙ ኪነ ሕንጻዎችን፣ ብዙ ጥበቦችን የሚያውቁ ናቸው። አሁን ግን ኢየሱስን ለማየት ፈለጉ። ለእንዲህ ያለ ጥማት ዋጋ በመስጠት የሚታወቀው እንድርያስ ነበርና ፊልጶስ ለእንድርያስ ነገረው።
ሐዋርያትን ስናስብ ብዙ ጊዜ እውቀት የሌላቸው አላዋቂዎች የነበሩ አድርገን ነው። ከዚያ ባሻገር አንድ ታንኳ ትተው የመጡ ያን ያህል ዋጋ ያልከፈሉ አድርገን ነው። በእውነት ዛሬ ሥራህን ትተህ ተከተለኝ ቢባል ማነው እሺ የሚለው? ደቀ መዛሙርት ግን ታንኳቸውን፣ ትዳራቸውን፣ ቤተሰባቸውን ትተው ተከተሉት። እነርሱ እንደ ገለጡት ሁሉን ትተው ተከትለውታል። ሁሉን ሲባል የካበተ ነገር እንዳላቸው ያሳያል። እንድርያስም እንዲሁ ሀብቱን ትቶ የተከተለ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ከሞቀ ኑሮ ተነሥተው እንደ ተከተሉ፣ ተራ ሰዎችም እንዳልሆኑ ዮሐንስን መጥቀስ እንችላለን። ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ብንጠቅስ መልካም ነው፡-
1-  ጌታችን በተያዘበት ሌሊት እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ገብቷል። “ስምዖን ጴጥሮስም ሌላውም ደቀ መዝሙር ኢየሱስን ተከተሉ። ያም ደቀ መዝሙር በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ ነበረ፥ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ ከኢየሱስ ጋር ገባ፤ ጴጥሮስ ግን በውጭ በበሩ ቆሞ ነበር። እንግዲህ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀው ሌላው ደቀ መዝሙር ወጣ ለበረኛይቱም ነግሮ ጴጥሮስን አስገባው” /ዮሐ. 18፡15-16/። በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀውና ጴጥሮስን ያስገባው ዮሐንስ ነው።
2-  በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ቤት ነበረው፡- ጌታችን መስቀል ላይ ሳሉ እናቱን እመቤታችን ድንግል ማርያምን አደራ የሰጠው ለዮሐንስ ነው። “ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን፡- አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።/ዮሐ. 19፡26/። ዮሐንስ ታማኝ ነበረ። ታዋቂ ሰውም ነበር። ከዚያ ባሻገር በኢየሩሳሌም ቤት ነበረው። ወደ ቤቱ ወሰዳት ይላልና። በገሊላ በሰሜን፣ በኢየሩሳሌም በደቡብ ቤት ከነበረው ባለጠጋ፣ ያውም ወጣት ባለጠጋ ነበር። ስለዚህ የጌታ ደቀ መዛሙርት ሁሉን ትተው የተከተሉ ናቸው።
      ጌታችንም ለዚህ ምናኔአቸው እንዲህ ሲል ቃል ገባላቸው፡- “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ” /ማቴ. 19፡27-28/።
ጌታ ሆይ ሁሉን ትተው ትተው በተከተሉህ ፊት፣ ሁሉን ይዘን መከተላችን አሳዝኖናልና እባክህ እርዳን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ