መግቢያ » መጽሐፍ ቅዱስ » ብሉይ ኪዳን » መዝሙረ ዳዊት » በኅብረት ተቀመጡ (1)

የትምህርቱ ርዕስ | በኅብረት ተቀመጡ (1)

“ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።” መዝ. 132 ፡ 1።

እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ ካህናት ወደ ቤተ መቅደስ ሲጓዙ ከሚዘምሯቸው ዝማሬዎች አንዱ፡- “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ ፥ እነሆ ፥ መልካም ነው ፥ እነሆም ፥ ያማረ ነው” የሚለው ነው ። ሁሉም ሰው በግሉ በቤቱ መጸለይ ይችላል ። ቤተ መቅደስ ግን የተዘጋጀው በኅብረት ለመጸለይ ነው ። ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሄደው እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም ለማግኘት ነው ። አዎ ሰዎችን ለማግኘት ነው ፤ ይህ ሊሰመርበት የሚገባ አሳብ ነው ። ለመሳሳም ፣ ሰላምታ ለመሰጣጠት ፣ ለመወያየት ፣ በአንድነት የምሕረት ደጅን ለማንኳኳት ነው ። መሳሳም ፣ ሰላምታ መለዋወጥ የቅዳሴው አካል እንደሆነ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች ፣ ትፈጽማለች ። ክርስትና ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ኅብረት ማድረግ ነው ። ክርስቶስም ያስታረቀው ሕዝብና አሕዛብን ነው ።

ወንድምነት ብዙ መገናኛዎች አሉት ። ነቢዩ “ወንድሞች” የሚለው በተፈጥሮ እኛን የሚመስሉትን ሁሉ ነው ። አንድ ዓይነት ማኅተም ያረፈባቸው ንብረቶች ዋጋቸው እኩል እንደሆነ ፣ በአንዱ እግዚአብሔር እጅ የተሠሩ የሰው ልጆች እኩል ናቸው ። ወንድምነት የእኩያነት ግንኙነት ነው ። እኩያነቱን የሚያመጣው ግን መልክና ችሎታ ሳይሆን ከአንድ አባት መወለድ ነው ። ከአንድ አባት የተወለዱ ባይተዋወቁም ወንድማማች ናቸው ። ወንድምነት የተፈጥሮ ማሰሪያ ነው ። ይህን ማሰሪያ እንቁረጥህ ባልን ቍጥር አደጋዎች ይፈጠራሉ ። እግዚአብሔር የሰጠን ተፈጥሮ በኅብረት የሚከወን በመሆኑ ግለኝነት እየጎዳን ይመጣል ። የሚገርመው ብዙዎቻችን መንግሥተ ሰማያትን እንመኛለን ፣ መንግሥተ ሰማያት ግን ከእኛ ዘመን በፊትና ኋላ ያሉ አእላፋት ያሉባት ስፍራ ናት ። የምንጠላውን ሰው በመንግሥተ ሰማያት ባላገኘሁ ብለን እንፈራ ይሆናል ። የጥላቻ ሰው ግን መንግሥተ ሰማያትን መውረስ አይችልም ። የፍቅርን ዓለም የፍቅር ሰው ብቻ ይወርሳታል ።

ወንድም የሚባል ብዙ ነው ። የሥጋ ዘመድ ፣ የአገር ልጅ ፣ የመከራ ጓድ ፣ ጽኑ ወዳጅ ፣ አብሮ የኖረ ፣ አብሮ ያደገ ፣ የሃይማኖት ቤተሰብ ፣ የአሳብ ተስማሚ … ይህ ሁሉ ወንድም ይባላል ። ጌታችን አብረውት ያደጉት ወንድሞቹ ተብለው ተጠርተዋል ። እርሱ ወንድሞቼ ሲላቸው ባያፍርባቸውም እነርሱ ግን ልካቸውን አውቀው ጌታ ብለው ጠርተውታል ፣ ራሳቸውንም “የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ” ብለው ሰይመዋል ። ቅዱስነት ራስን ማወቅ ነውና ። (ያዕ. 1፡1፤ ይሁዳ ቁ. 1)። ከሥጋ ዘመድም የአሳብ ዘመድ ይበልጣል ። እመቤታችን ብዙ የሥጋ ዘመዶች ሳሉዋት ፣ መስቀሉ ሥርም እኅትዋና የእኅትዋ ባል ቀለዮጳ ሳሉ ጌታችን አደራ የሰጣት ለሚወደው ደቀ መዝሙር ለዮሐንስ ነው ። (ዮሐ. 19፡25-26)።

ይቀጥላል

ዕለተ ብርሃን 12

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም