የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐርፍ ዘንድ ተወኝ (18)

“በተግሣጽህ ስለ ኃጢአቱ ሰውን ዘለፍኸው፥ ነፍሱም እንደ ሸረሪት ድር ታልቃለች በእውነት ሰው ሁሉ ከንቱ ነው ።” (መዝ. 38 ፡ 11 ።)

ወላጆች በልጃቸው እጅ ላይ ገዳይ ነገር ሲያዩ በቍጣ ያስደነግጡታል ፣ በኃይለ ቃል ይነጥቁታል እንጂ አያባብሉትም ። ማባበል ለፈነዳ ቦምብ እንጂ ለሚፈነዳ ፈንጂ አይደለም ። አደጋው ከደረሰ በኋላ “አይዞህ” ብሎ ማባበል ተገቢ ነው ። በቦምብ የተመከረን ሰው በተግሣጽ ልምከር ማለት ቃላት ማባከን ነው ። እጁ ላይ ትልቅ ጥፋት የያዘን ሰው ግን መገሠጽ ከቀጣዩ ውድመት አይብስም ። እግዚአብሔር ሕይወታችን የሚበላሽባቸውን ነገሮች ከእጃችን ላይ በቍጣውና በተግሣጹ ያስጥለናል ። ነቢዩ ዮናስ ወደ ምሥራቅ ነነዌ ወይም ኢራቅ-ሞሱል ተልኮ ወደ ምዕራብ ተርሴስ ወይም ወደ እስፔን ጉዞ ሲያደርግ እግዚአብሔር በተግሣጹ ምርጫውን ከእጁ አስጣለው ። በተርሴስ እንዴት ሁኖ ይኖራል ? ሕይወቱንም ኑሮውንም ያበላሻል ። ስለዚህ ነቢዩን በማዕበል መከረው ። በምንሄድባቸው የግል መዳረሻዎቻችን ላይ ማዕበል ሊነሣ ይችላል ። አንዳንድ ነገሮችን ገና ስንመኛቸው ጦርነት ይፋፋምባቸዋል ። እግዚአብሔር ይህ መንገድ አይሆንም እያለን ሊሆን ይችላል ። በዚያ ስፍራ ላይ የዘመናት ድካማችንን ልናባክን ፣ የአገልግሎታችንን ክብር ልናስነጥቅ እንችላለን ። እኛ የዛሬውን እርሱ የወደፊቱን ያያል ፣ እኛ ምኞታችንን ስንከተል እርሱ እውነቱን ተመልክቶ ይነጥቀናል ። በምክር ልንመለስ ስለማንችል በከባድ ማዕበል ወደ አቅጣጫችን ይመልሰናል ።

ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች እንማረካለን ። እውነትን ከሐሰት መለየት አቅቶን ፣ የዛሬው ፍቅር የሁልጊዜ መስሎን ፣ ሀብታችንን የዘመናት ልፋታችንን ልንበትን እንነሣለን ። አንዳንድ ጊዜ “ዘመኑን ዋጁ” በሚል ጥቅስ ያለ ዐውዱ ተርጉመን ዘመኑን እንመስላለን ። ዘመን ለመማረክ በሚመስል ፉከራ ዘመን ይማርከናል ። “እሺ” ብለናቸው “እሺ እናሰኛቸዋለን” በሚል የሞኝ ፈሊጥ ነጩን ልብሳችንን እናሳድፋለን ። እግዚአብሔር በተግሣጹ ፣ በቍጣው ከእጃችን ላይ ያስጥለናል ። የተመቸን ነገር እንዲጎረብጠን ፣ የጠለለን ነገር እንዲያራቁተን ያደርጋል ። በገንዘባችን ተመክተን እግዚአብሔርን ለመደበቅ ስንሞክር ፣ እርሱ ግን ተአምራት በሚከተለው ቍጣው ይመልሰናል ። ራሳችንን እስከ ሰጠነው ፣ ልጆቹ ነን ብለን እስካወጅን ድረስ እያለቀስን ይነጥቀናል ። እኛን ለእኛ የተወን ቀን ለማጉረምረምም ዕድል አይኖረንም ። ሕፃን ልጅ ገዳዩን ነገር ሲነጥቁት መጀመሪያ ያለቅሳል ፣ ቀጥሎ ያማርራል ። የወላጆቹ ፍቅር የሚገባው ምናልባት ከሃያ ዓመት በኋላ ነው ። ወላጆቹ እስኪገባው ብለው ቢጠብቁት ፣ በራሱ ሂደት ይማር ብለው ለራሱ ቢተዉት ኖሮ እንኳን መማር መኖር አይሆንለትም ነበር ። እግዚአብሔር አንዳንድ ነገሮችን እስኪገባን ሳይጠብቅ ይነጥቀናል ። እግዚአብሔር ከስሜታችን ለእውነቱ ቅድሚያ ይሰጣል ። በእውነት ስሜታውያን ነን ። ሰውን የማያድግ ልጅ የሚያሰኘው ስሜታዊነቱ ነው ። እየካበ የሚንደው ፣ እየጨረሰ የሚጀምረው በስሜት ጉዞው ነው ።

ነቢዩ ዳዊት የአንድ ቀን ስሜቱን ቤርሳቤህን ማየቱን ቢታገሥ ኖሮ ረጅሙ የሕይወት ዘመኑ የስብራት ባልሆነ ነበር ። አዳም በገነት ፣ ዳዊት በሰገነቱ ላይ ወደቁ ። ሁለቱም ሴትን የሚቀበሉበትን መድረክ መንፈሳዊ አላደረጉትም ። አንዳንድ ጊዜ ጸልየን ስለወጣን ወደ ገደል ብንሄድም ገደሉ እንደሚቀደስ እናስብ ይሆናል ። መጸለይ ኃላፊነትን አያስጥልም ።

እኛ ሰውን ስለ መልካምነቱ አናመሰግነውም ፣ አንመርቀውም ። ስለ ጥፋቱ ግን እንዘልፈዋለን ። እግዚአብሔር ግን ሰውን ስለኃጢአቱ ይዘልፈዋል ። “ጻድቃን ሆይ ደስ ይበላችሁ” ይላል ። እኛ ሰውን ስለ መልካምነቱ እንዘልፈዋለን ። “ለዚህ ያበቃህ ደግነትህ ነው” እንለዋለን ። ፖለቲካዊ ጽድቅን እንደ እኛ እንዲለማመድ እንመክረዋለን ። እግዚአብሔር ግን የሚዘልፈው ሰውን ስለ ኃጢአቱ ነው ። የተቆጡን ፣ የገሠጹን ሰዎች ካሉ እኛን እንደ ራሳቸው ያዩን ሰዎች ናቸው ። በዚህ ዘመን ማንም ስለማንም ማሰብ አይፈልግም ።

ኃጢአት የሰውን ነፍስ እንደ ሸረሪት ድር ይጨርሰዋል ። የሸረሪት ድር በውስጡ ያለው ጥበብና ውስብስብነት መግለጥ አይቻልም ። ለእርስዋ የመጨረሻ ቤትዋ ነው ። ሌላው ግን ቆሻሻ ነውና ይጠርገዋል ። እግዚአብሔር የሌለበት ጥበብ ሁሉ ተጠርጎ የሚጣል የሸረሪት ድር ነው ። በምድር ላይ ትልቅ ጥበብ የመሰለን ከሰማይ ሲታይ ትልቅ ሞኝነት ሊሆን ይችላል ። የሸረሪት ድር ለሸረሪትዋ የማይደፈር ምሽግ መስሎ ይሰማታል ፣ ለዚህም ብዙ ደክማለች ። ሰውም ብልጠትን መኖሪያ ያደርገዋል ፣ ውስብስብ ነገሮችን ይፈጥራል ። ነገር ግን ብልጠት የሞኝነት ያህል ሁሉ ሰው ያውቀዋል ። “እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው የዝንጉም ሰው ተስፋ ይጠፋል ። ተስፋው ይቈረጣል ፥ እምነቱም እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል ። ቤቱን ይደግፈዋል ፥ አይቆምለትም ይይዘውማል ፥ አይጸናለትም ።” (ኢዮ. 8 ፡13-15 ።)

በርግጥም ሰው ከንቱ ነው ። ሥጋውን በኃጢአት ፣ ነፍሱን በውስብስብነት የሚያስጨንቅ ነው ። የቀናውን መንገድ ለመከተል ፣ ደግሞም ጥቂት ለማረፍ ነቢዩ ይለምናል ። የራስ መንገድ ያደክማል ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ያሳርፋል ።

አሜን!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ