ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ ። ገሊላ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅባት ፣ የሁሉ መኖሪያ ፣ ምቹ ስፍራ ፣ ዘረኝነት የማይታይባት ፣ ደብረ ታቦር ፣ ደብረ አርሞን ያለባት ፣ ልምላሜ ዓመት ከዓመት የማይለያት ፣ የቄሣሮች መታሰቢያ ያረፈባት ፣ የምዕራቡና የምሥራቁ ንግድ የሚተላለፍባት ፣ የአንጾኪያ ጎረቤት ፣ የሊባኖስ ቡና አጣጭ ናት ። ጌታችን ከዚህች ደማቅ ከተማ ጭው ወዳለው በረሃ ፣ አንድ የእግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ሄደ ። ስለ ዓለም ለማወቅ ዓለምን የመነኑ ሰዎችን ማነጋገር ያስፈልጋል ። ዓለምን ካልናቅን ሰደቡኝ ተፉብኝ ብለን እንቅልፍ እናጣለን ፣ አጣሁ ነጣሁ ብለን ሞትን እንመኛለን ፣ ተሻርኩ ካባ ተቀማሁ ብለን ሕይወትን እንረግማለን ። የመነኑትን ስናይ በኑሮም በቃልም እየገሠጹ ትክክለኛውን ማያ መነጽር ይሰጡናል ። ከሰው የራቁ ከእግዚአብሔር የራቁ አይደሉም ። አገርን በጸሎት የሚጠብቁ የእምነት ሠራዊት ፣ የተደናገረ ሰው ፈቃደ እግዚአብሔርን የሚጠይቅባቸው ፣ የከፋው የሚጽናናባቸው ገዳማውያን ያስፈልጋሉ ። እነርሱ ለእኛ መጽናናት ናቸው ፣ እኛም የእነርሱን ልብ እናሳርፋለን ። ስለ እግዚአብሔር ገለል ብለው ያሉትን አባቶች ፣ በጸሎት የጸኑትን እውነተኞች መፈለግ ከጌታችን የምንማረው ነው ።
ጌታችን ገና የዕለት ጽንስ ሳለ ያወቀው የዚያን ጊዜው የስድስት ወር ጽንስ ዮሐንስ አሁንም ጌታ ሲመጣ አወቀው ። በእናቱ ማኅፀን ሳለም ፣ በሠላሳ ዓመቱም ወደ ዮሐንስ የሄደው ጌታችን ነው። ወደ እርሱ እስክንመጣ አይጠብቅም ፣ ፍቅር ቀድሞ ይገኛል ፣ ፍቅር ይፈልጋል ። ፉክክር ባለበት ፣ ኩራት ባጠላበት ፣ መፈራራት በነገሠበት ፍቅር እየከሳ ይሄዳል ። ያኔም በማኅፀን ዝምታው ዛሬም በትሕትና ዝምታው ጌታን አወቀው ። ጌታን በቃል ብቻ የሚያውቁ አሉ ፣ እውነተኛ ወዳጆቹ ግን በዝምታውም ይበልጥ ያውቁታል ፣ እርሱ በዝምታም መፍጠር ይችላል ። አሜን ክብር ምስጋና ላንተ ይሁን ! ኢየሱስ ክርስቶስ መዓዛ ቅዱሳን ነው ። መዓዛው ያውዳል ። ቃል ባይናገር ከገነት ይልቅ ያሳርፋል ። ዝም ቢል ከብዙ የፍልስፍና ቃላት ይልቅ ነፍስን ያቀናል ። አሜን!
መናኙ ወደ መናኙ ሄደ ። የእውነተኛው ክርስቲያን መልክ መናኝነት ነው ። መናኝነት ሰዋዊ ክብርን መሸሽ ፣ እዩኝ እዩኝ ማለትን መናቅ ፣ ለሌሎች መቆረስ ፣ እኔ ዝቅ ብዬ ወንድሜ ከፍ ይበል ማለት ፣ የወገንን አበሳ መደበቅ ፣ ደግ ደጉን ማየት ፣ ከባቴ አበሳ መሆን ነው ። የእኔ ነው ስንል ጠብ ይፈጠራል ። ንብረቱ የእኔ ነው ካላልን ጠብ አይኖርም ። ዝናው የእኔ ነው ካላልን ግርግር አንፈጥርም ። በእኔ ሥራ ነው የታወቁት ካላልን ለበቀል አንነሣም ። መናኝነት “ሁሉ የእግዚአብሔር ነው” ብሎ ማረፍ ነው ። ፍትሐ እግዚአብሔርና ቀን የማይገልጡት ክዳን የለም ። ከስድሳ ከሰባ ዓመት በፊት ደራሲ የተባሉ ዛሬ “የእነርሱ ሥራ አይደለም ፣ ሰርቀው ነው” ሲባል እንሰማለን ። እኛ ተኝተን አይደለም ፣ ሞተንም እውነት አትተኛም ። እውነተኛ ሰው በቁሙ ይረገማል ፣ በአጽሙ ይከበራል ። እውነተኞች አጽማቸው ይቅርታ ይጠየቃል ። በዕድሜ በዘመናቸው የማይከብሩት በትዕቢት እንዳይወድቁ ነው ። በአንድ ተግባራቸው ከተደነቁ ረክተው ይቆማሉ ። ብዙ የሠሩ ሰዎች የተነቀፉ ሰዎች ናቸው ። አመስጋኞች በትንሹ እንድንረካና እንድንቆም ሊያደርጉን ይችላሉ ። ረጅም ርቀት የማይጓዙ ሠራተኞች አንደኛ በመንቀፍ ላይ የተመሠረቱ ፣ ሁለተኛ በጥቂት ሥራቸው የገነኑ ናቸው ። “ዶሮን ሲያታልሏት ፣ በመጫኛ ጣሏት” ይባላል ። መጫኛ ለበሬ እንጂ ለዶሮ አይወረወርም ። በትንሹ ተግባር ፣ ትልቅ ክብር የሚያገኙ እንደዚህ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ታዲያ የኮሰሰ ትልቅ ሰው ሲያገኙ “ጥሩ ቢሠራ ይደነቅ ነበር” ይላሉ ። ዓለም የጭቃ ጅራፏን ስታመጣባቸው ፣ ቀንበሩ ከብዷቸው ይጨነቃሉ ፣ እንኳን የሠሩትን ያልሠሩትን ኃጢአት ይናዘዛሉ ።
ሰው በድዬ ነበር አድርጌ እንደ ዋዛ ፣
ቁናውም ቁናዬ ነው ዙሩ በእኔ በዛ ።
በሰፈሩበት ሳይሠፈሩ አይቀርም ። በፈረዱበት ሳይፈረድ አይቀርም ። ያውም እጥፍ መስፈሪያ ይሰፈራል ።
የጌታችን ጥምቀት ዓለምን የናቁ አገልጋዮችን እንድናከብር ፣ የሐር ወንበር ላይ የሚቀመጡትን ሳይሆን በፍጹም ድህነት የእግዚአብሔርን ሥራ እየሠሩ ላሉት ክብር እንድንሰጥ ያስጠነቅቀናል ። ንብረት አፍቃሪ መናኝ መውደድ አይችልም ። እውነተኛ ምናኔ የልብ ነው ። የእግዚአብሔር ፈቃዱ ከዓለም እንድንወጣ ሳይሆን ዓለም ከልባችን እንድትወጣ ነው ። እኛስ ይህን በዓለ ጥምቀት ስናከብር ዝቅ ብለው የሚያገለግሉትን ፣ የኑሮ ተራራ እየገፉ ያሉትን አባቶች እያስታወስን ይሆን?
እነዚህ አባቶች ፅሙደ ጸሎት ሆነው በጉዳት የሚኖሩት ለእኛ ነው ፣ አገር ካገር እየተንከራተቱ የሚያስተምሩት ወንድሞች ለእኛ ነው ! ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ይገባናል ። አሊያ ከጅብ ሰርግ ላይ ይጥለናል !
ጌታ ሆይ በቀደምህበት እንድንከተልህ ፣ ለእውነተኛ አገልጋዮችህ ክብር እንዲኖረን እባክህ አግዘን!
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 15 ቀን 2016 ዓ.ም.