የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከነቢይ የሚበልጠው መጥምቁ ዮሐንስ

(ማቴ. 11 ፡ 9)

የዘመን መለወጫ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ ይጠራል ። ይህ በሁለት ምክንያት ነው ። የመጀመሪያው ዮሐንስ መጥምቅ በሰማዕትነት ያለፈው መስከረም ሁለት ቀን ነው ። በዚህ ምክንያት መስከረም አንድ “ቅዱስ ዮሐንስ” ተብሎ ይጠራል ። ሁለተኛው ዮሐንስ መጥምቅ የብሉይ ኪዳን መጨረሻ የአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ነው ። የነቢያት መጨረሻ ፣ የሐዋርያት መጀመሪያ ይባላል ። አሮጌው ዘመን አልፎ ወደ አዲሱ ዘመን ስንሻገር ፣ የሽግግር አገልጋይ በሆነው ነቢይ “ቅዱስ ዮሐንስ” መባሉ ተገቢ ስያሜ ነው ።

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ብዙ ስሞች አሉት ። ነቢይ ይባላል ። ስለ መሢሑ መምጣት ተናግሯል ። ሕዝብን ለንስሐ ጋብዟል ። ስለ ፍትሕ መጓደል ነገሥታትን ገሥጾአል ። ሕዝብን አጽናንቷል ። የነቢያት ተግባር የሚመጣውን ክርስቶስ መግለጥ ፣ ሕዝብን ለምጽአተ ክርስቶስ ማሰናዳት ነው ። በደለኛውን ለንስሐ መጋበዝ ፣ ነገሥታትን መንገድ መምራት ፣ ሁሉን በእኩል ዓይን አይቶ መገሠጽ ነው ። የነቢይን ስም የሚወድዱ የነቢይን ሥራ ግን የማይወድዱ ብዙ ናቸው ። ነቢይነት ጸጋም ፣ ጥሪም ነው ። የሥራ መስክ ፣ ራስን የሚቀቡበት የዘፈን ውድድር አይደለም ። ነቢይ የሕዝብ አጫዋች ፣ የቀለድ መሥሪያ ቤትም አይደለም ። ነቢይ ዓለምን የናቀ ፣ ከንብረት ውድድር የራቀ ፣ በመንፈስ የረቀቀ ፣ ወደ ሰማይ የመጠቀ ነው ። ዕድል ፈልጎ የሚቀማ ሳይሆን ዕድል እያለው እንደ ሙሴ ቤተ መንግሥትን ንቆ ምድረ በዳ የሚመሽግ ፣ እንደ ኢሳይያስ አዝማደ መንግሥትነትን ተጸይፎ የሕዝብ ወገነተኛ የሚሆን ነው ።

ክርስቶስ ስለ መጣ በዚህ ዘመን የነቢይን ተግባር ሰባኪ ይዞታል ። የመጨረሻውን መልእክት በውድ ልጁ ስለሰማን በዚህ ዘመን ነቢይ አያሻም (ዕብ. 1 ፡ 2) ። አንድም ነቢይ “እንዲህ ዓይነት ልብስ የለበስህ” እያለ የግምት ሥራ አልሠራም ። በዚህ ዘመን ክርስትናን ለማቃለል ፣ ሰውን የከሀዲነት ወዶ ገብ ለማድረግ የተነሡ አጽራረ ክርስቶሶችን እያየን ነው ። የኢየሱስን ስም እየጠሩ ሲጨፍሩ ፣ ቅዱሳንን ሲያቃልሉ ፣ ተራ ንግግር ሲናገሩ እያየን እየሰማን ነው ። የክርስቶስ ስም መቀለጃ ሲሆን ክርስቲያን ተብለን ተባባሪ ሆነን እንስቃለን ። በክርስትናው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ግን አልተገነዘብንም ። በወንጌል ስም የገባው የምዕራባውያን እንቅስቃሴ መጀመሪያ ክርስትናውን ያቃልላል ፣ ቀጥሎ ባዶ እጅን አስቀርቶ ከሀዲ ያደርጋል ። ቅዱሳንን ስለናቁ እነዚህን ሰዎች ስንነቅፍ እንውላለን ፣ ክርስቶስንም እያቃለሉት ነውና ተዉ ልንል ይገባናል ። የቤተ ክርስቲያን መሠረትም ጉልላትም ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ።

መጽሐፍ ቅዱስን ፣ አማናዊውን ክርስቶስን ለማስጠላት በዓላማ እየሠሩ ያሉ ፣ ክርስትና ላይ እንዲህ ሲቀልዱ እያየን ተግባራቸውን መሳቂያና ቀን መግፊያ እያደረግን በመሆናችን እግዚአብሔር ይጠይቀናል ። ሰውን የምኞት ዛር እንዲቆራኘው ፣ ያልሠራበትን እንዲዘርፍ ፣ የእርሱ ያልሆነውን እንዲከጅል የሚያስተምሩ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች ፣ ለምድሪቱ ጭንቀት ሆነዋል ። የአፍሪካ ወንጌል ተብሎ የሚጠራው “ታገኛለህ” የሚል ስብከት ነው ። ድሀውን ማጓጓት አገልግሎት አይደለም ። ለድሀ ለመስጠት የሚፈተኑ ፣ ድሀን ግን “እንዲሁ ታገኛለህ” በማለት በምኞት የሚያመክኑ በነቢይ ስም ራሳቸውን የሚጠሩ ናቸው ። ነቢይ ነኝ የሚል በግድ ተአምራት ያደርጋል የሚል አመለካከትም እንዲዳብር አድርገዋል ። ነገር ግን ነቢይ የሆነው ዮሐንስ መጥምቅ እንዲህ ተብሎ ተነግሮለታል ። “ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው፡- ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም ፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት ነበረ አሉ ።” ዮሐ. 10 ፡ 41 ።

ወደ እግዚአብሔር ቤት የምንመጣበት ዓላማ እቤታችን የደበቅነውን ለማወቅ አይደለም ። የምናውቀውን ሲነግሩን መደሰት ሞኝነት ነው ። የማናውቀውን መፍትሔና ነገረ እግዚአብሔር ቢነግሩን የተሻለ ነው ። ብዙዎች በሐሰተኛ ነቢይ ነን ባዮች ፣ በሐሰተኛ ፈዋሾች ትዳራቸው ፈርሷል ። ድናችኋል ተብለው በበሽታቸው ፈጥነው ሞተዋል ። አንዳንዶችም የተተነበየልኝ አልደረሰም በማለት እግዚአብሔርን ተቀይመውና ክደው ወደ ኋላ ተመልሰዋል ። “እግዚአብሔር ብሏል” አሏቸው እንጂ እርሱ ለማለቱ እርግጠኛ አይደሉም ። እግዚአብሔር በዚህ ዘመን በተጻፈው ቃሉ እንጂ በርግጠኝነት ከቃሉ ውጭ የሚናገርበት ሰው የለም ። ቢናገር እንኳ የተጻፈውን ቃል አጽድቆ እንጂ ሽሮ አይናገርም ። ክርስትና መመዘኛ አለው ። በየዘመናቱ የአቋም ለውጥ የሚያደርግ ፣ በለውጥ ላይ ያለ ሃይማኖት አይደለም ። ክርስትና ሰውን ይለውጣል ፣ ያድሳል እንጂ ትምህርቱ አይለወጥም ፣ ሃይማኖቱም አይታደስም ። የድሮ ጠንቋይ አፍሮ በሰባት መጋረጃ ተከልሎ ይጠነቁል ነበር ። ቢያንስ ሐፍረት ያለው ስልጡን ይመስላል ። ዛሬ ግን በአደባባይ ተራ ጥንቆላ ሲካሄድ ይታያል ። የሰው ገመና የገቢ ምንጭ ሆኗል ። የራስን ዝና ለመካብ የሌላውን ዝና መናድ ለሐሰተኞቹ ጭንቅ አይደለም ።

ከፈሪሀ እግዚአብሔር ይልቅ ፈሪሀ ሰይጣን በሕዝባችን ላይ ነግሦአል ። ለሁሉም ነገር ተጠያቂው ሰይጣን ነው ተብሎ ይነገራል ። የስካር ፣ የዝሙት መንፈስ ይባላል ። የሰው ተጠያቂነት ችላ ተብሏል ። ሰው ነጻ ፈቃድ ያለው ፍጡር መሆኑ ተዘንግቶ የስስት መንፈስ ፣ የመበተን መንፈስ እየተባለ ሁሉንም ነገር ማመናፈስ የዘመናችን መገለጫ ሆኗል ። በሚለብሱት ልብስ ፣ በሚሞቁት እሳት ላይ ሳይቀር አጋንንት ያርፋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ሁሉንም ነገር መገሠጽ ፣ ራስን በማሸበር መኖር እያየለ መጥቷል ። ዓለማውያንና ከሀድያን በሰላም እየተኙ አማኝ ነኝ የሚለው ግን ሲገሥጽ ፣ ሲፋለም ይውላል ፣ ያድራል ። የጦር ሜዳ ትራፊ ቃላትም የሐዋርያት ቃል እስኪመስሉ ይደመጣሉ ። ይወጋ ፣ ይውደም ፣ ይደምሰስ …. የሚሉ ቃላት የት መጡን ይተርካሉ ። በውስጥ በውጭ ትግል ውስጥ ያለች ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም እውነት የሚናገሩና የሚገሥጹ ፣ የነቢይ ሥራና ሞገስ ያላቸው አባቶች ያስፈልጉአታል ።

አቤቱ አድነን ! ፈጥረህ ላልፈጠረ አትተወን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 27 ቀን 2016 ዓ. ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ