አገልጋዩና ሴቶች
(የወጣት አገልጋይ ፈተና)
ወጣቱ አገልጋይ ከወጣትና ከመካከለኛ ዕድሜ ካሉት ሴቶች የተለያየ ፈተና ሊደርስበት ይችላል ። በትልልቅ ሰርግ ውስጥ ትንንሽ ሰርግ አለ ይባላል ። በትልቅዋ ቤተ ክርስቲያንም ትንንሽ ቡድኖች ይስተዋላሉ ። ክርስቶስ የሞተው ለቤተ ክርስቲያን እንጂ ለቡድኖች አይደለም ። ክርስቶስ ለኅብረት ሞተ ፣ ሰዎች ለቡድን ይሞታሉ ። ሁሉም ወንዶች ለአገልጋዩ ፈተና እንደማይሆኑ ሁሉ ሁሉም ሴቶች የአገልጋዩ ፈተና አይደሉም ። ኤልያስን በረሀብ ዘመን ተቀብላ ያስተናገደች የሰራፕታዋ መበለት ፣ ኤልሳዕን ላሳርፈው ብላ በቁርጥ የተነሣች የሱነም ሴት ፣ ጌታችንን በገንዘባቸው ያገለገሉ ቅዱሳን አንዕስት ፣ በቤታቸው የተቀበሉት ማርያምና ማርታ ፣ ከሁሉ በላይ አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም ታላላቅ ሴቶች ሁነው ተመዝግበዋል ። ወጣቱ አገልጋይ ወጣትነት በሚሰማቸው ሴቶች የሚደርስበት ትግል የጌጥ አምልኮን ለማስለቀቅ በሚነሣበት ጊዜ ነው ። ራስን መጠበቅ መልካም ነው ። ቁንጅናም ኃጢአት አይደለም ። ቁንጅና ትዕቢት ከሆነ ግን ዲያብሎስ በመጀመሪያ በወደቀበት ወጥመድ መያዝ ነው ። ቆንጆ የነበረው ሳጥናኤል ወደ ጥልቁ የተጣለው በቁንጅናው ትምክሕት ነው ። እግዚአብሔር እስከ ዛሬ የፈጠረውን አስቀያሚ ሰው አያውቅም ።
መንፈሳዊነት በጌጥና በልብስ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ። ክርስቲያናዊ አለባበስ እንዳለ አማኝ ሁሉ ሊያውቀው ይገባል ። የዝሙት ማስታወቂያ መሆን ፣ ዕርቃንን አደባባይ መውጣት ፣ ለአምልኮ ነው የምሄደው እያሉ መገላለጥ ተገቢ አይደለም ። የመታየት ጥማት የመደበቅ ቀንን ይጠራል ። ቁንጅና ይበላሻል ፣ መልክም ይረግፋል ። የሰው ልጅ መልክና ቁመና የሣር ልምላሜ ፣ የአበባ ፍካት ነው ። ለመርገፍ ለመጠውለግ ይቸኩላል ። አሁን የታየው ሰው አሁን ይሰወራል ። ዳግም ላይመጣ ይሄዳል ። ሴቶች በሰው ለመታየት ሳይሆን በእግዚአብሔር ለመታየት ብቻ ወደ በቤተ ክርስቲያን ስለሚመጡ መሸፋፈን አለባቸው ። ቤተ ክርስቲያን የሀብትም ፣ የጌጥም ፣ የወርቅም ማሳያ አይደለችም ። ሁላችን ፍጹም ድሆች ፣ ክርስቶስ ፍጹም ባለጠጋ መሆኑን የምናምንባት ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት ። የሌላቸውን እንዳናሳቅቅ በቤተ ክርስቲያን መሽቀርቀር ፍጹም ክልክል ነው ። ሁለት ባለጠጋ በአንድ አደባባይ አይቆምም ። ባለጠጋውን ጌታ ለማክበር ፍጹም ድሀ ሆኖ መቅረብ ያስፈልጋል ። ሁለት ቆንጆም በአንድ አደባባይ አይወዳደርም ። የሰው ሁሉ መልክ ክርስቶስ ነውና መልካችንን ብናሳይ እርሱን እንክደዋለን ። በቀራንዮ የሚታየው ያ በደም የተነከረ ገጽ የእኛ መልክ ነው ። የእኛን ፊት ለማለምለም እርሱ መልኩ ጠወለገ ።
ጌጣ ጌጦች ገንዘብን የሚጨርሱ ፣ ሰው በራሱ ተማምኖ እንዳይቆም የሚያስደነብሩ ፣ ራስህን በሸቀጥ አጉላ የሚሉ ፣ ተፈጥሮአዊ ሀብትን የሚነጥቁ ፣ ጤናን የሚጎዱ ፣ ለማንበብ የምናውለውን ጊዜ የሚሻሙ ፣ ራስን የዝሙት ንብረት የሚያደርጉ ፣ ሰው ይየኝ የሚሉ ጣዖታዊ አስተሳሰብ ውስጥ የሚከቱ ናቸው ። ወጣቱ አገልጋይ ይህን ለማስጣል ሲነሣ ብዙ ትግል ውስጥ ይገባል ። ተንኮለኛ በሆኑ ሰዎችና የአገልግሎት ትርጉም ሳይገባቸው አገልጋይ ነን በሚሉ ወገኖች ፣ እነዚህ ቆነጃጅት መጠቀሚያ በመሆን አገልጋዩን ለመጣልና ለማዋረድ መሣሪያ ይሆናሉ ። ብዙ አገልጋዮች በእነዚህ መጠቀሚያ በሆኑ ቆነጃጅት በአደባባይ በሐሰት ተከስሰዋል ።
ደግሞም ጥቂት በእውቀትና በዘመናዊነት ያደጉ ሴቶች አገልጋዩን ለመምራት ይፈልጋሉ ። ከእነርሱ መንገድ ሲወጣ ሰይፋቸውን ይመዝዛሉ ። ብዙዎችን ለማስተባበር አቅም ስላላቸው ጥቂት ተብለው የሚናቁ አይደሉም ። የትዳር አጋራቸውን ፣ ልጃቸውን ፣ የጾታ መሰሎቻቸውን ያስተባብራሉ ። ብዙ ዝርዝር ንግግር አይናገሩም ። “ይህን አገልጋይ ቀልቤ አይወደውም” ይላሉ ። አንድ ንግግር ደጋግሞ ሲነገር የሰዎችን አእምሮ እየተቆጣጠረ ይመጣል ። በዚህ ምክንያት ያ አገልጋይ እስኪነቀል ድረስ ትግል ውስጥ ይገባሉ ። ደግሞም ሌሎች ሴቶች መንፈሳዊነት ተሰማን እያሉ ትዳራቸውን ገሸሽ ማለት ይጀምራሉ ። መንፈሳዊነት ግን ቀድሞ ከሚወድዱት በላይ ትዳራቸውን ስለመውደድ የሚያስተምር ነው ። በዚህ ምክንያት ወንዶቹ ካህናትን መጥላትና መሳደብ ፣ መቃወም ይጀምራሉ ። ይህ ሁሉ ትግል አገልጋዩ ላይ ይመጣል ።
አገልጋዩ በማስተዋል መራመድ አለበት ። ርቀቱን ጠብቆ መሄድ ግዳጁ ነው ። ብዙም መቅረብ ፣ ብዙም መራቅን መከላከል አለበት ። ወጣት ሴቶችንም ሲያነጋግር በአደባባይ ፣ ሁሉም በሚያየው ስፍራ መሆን አለበት ። ቅን አገልጋዮች ሆይ ! የቤተ ክርስቲያን ጉዞ መስቀል የማይለየው ነውና ሁልጊዜ ንቁ ።
ሐዋርያው የጻፈልኝን ጦማረ ጽድቅ አስታወስኩት፡- “እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።” (1ጢሞ. 2 ፡ 9-10) ።
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 12
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም.